FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ከመሬታቸው ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው በመስከረም ወር የጋራ የመኖሪያ ቤቶችን ለማስረከብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል። ርክክቡ ገንዘብ ቆጥበው ዕጣ ደርሷቸው ሲጠባበቁ የነበሩ ዕድለኞችን በተመለከት ውሳኔ ላይ አለመደረሱንም ስምተናል።

የልማት ተነሽ ለሆኑ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካስገነባቸው የጋራ መኖርያ ቤቶች መካከል እንደሚሰጣቸው የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የካቲት ወር መጨረሻ ላይ የ40 / 60 እና የ20/80 የጋራ ቤቶች ወይንም የኮንዶሚኒየም እጣ ማውጣት ስነ ስርአት ላይ ተገኝተው መናገራቸው ይታወሳል። ሆኖም የኦሮምያ ተሟጋች ነን በሚሉ ሰዎች ገፋፊነት ከአዲስ አበባ የወሰን ይገባናል ጥያቄን ያነገበ ተቃውሞ በመነሳቱ ለባለ እጣዎቹም ሆነ ለልማት ተነሺዎችም የጋራ መኖርያ ቤቶቹ እስካሁን ሳይተላለፉ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህን ተከትሎ ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴን በሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ሰብሳቢነት አቋቁመው ለአዲስ አበባና ኦሮምያ የወሰን አከላለል ጉዳይ መፍትሄን እንዲያመጣ የቤት ስራ ሰጥተዋል።ይህ ኮሚቴ ከሚያፈተልኩ መረጃዎች ውጭ እስካሁን በትክክል ምን ላይ እንዳለ በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። ሂደቱ ግን ለበርካታ አመታት ቆጥበው የጋራ መኖርያ ቤት ሲጠባበቁ በነበሩ ዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል።

ዋዜማ ራዲዮ ከምንጮቿ ለመረዳት እንደቻለችው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለልማት ተነሽ አርሶሮች የጋራ መኖርያ ቤቶቹን ለማስተላለፍ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ቤቱ የሚተላለፍላቸው አርሶ አደሮችም እስከ ልጅ ልጆቻቸው ድረስ እንደሚሆንም ቤቱ እንዲተላለፍላቸው ከተመረጡ ግለሰቦች መካከል ያነጋገርናቸው ግለሰቦች ገልጸውልናል። የጋራ መኖርያ ቤቱ የሚሰጣቸው አርሶ አደሮች ; ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው የስም ዝርዝርም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቢሮዎች የሚገኝበት ቃሊቲ መነሐርያ አካባቢ ተለጥፎ ነበር። የቤቱ ባለቤት የሚሆኑትም አርሶ አደርና የአርሶ አደር ልጅ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ እንዲያቀርቡ እየተደረገ እንደሆነም ሰምተናል።

 ለልማት ተነሽ አርሶ አደሮችና ልጆቻቸው የሚተላለፉት የጋራ መኖርያ ቤቶች በብዛት ያሉት ኮዬ ፈጬ የሚባለው አካባቢ ላይ የተሰሩት ናቸው። በኮዬ ፈጬ አካባቢ ከተሰሩ የጋራ መኖርያ ቤቶችም አንድ ሺህ ለሚሆኑ ቤቶች ይህን ታሳቢ በማድረግ ውሃ እንደገባላቸው ከአዲስ አበባ የውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን ምንጮቻችን ሰምተናል። የቤቶቹን ርክክብ የሚጠብቁ ግለሰቦችም እስከ መስከረም ወር ኮንዶሚኒየሞቹ ይሰጣቹሀል ተብለናል ብለውናል።

በራሱ በገዥው ፓርቲ አስተዳደር መሬታቸውን በግፍ የተነጠቁት አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው የመኖሪያ ቤት እንዲያገኙ መደረጉ የሚበረታታ ቢሆንም አጠቃላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ዕድለኞችንና የኦሮሚያና አዲስ አበባ አስተዳደራዊ ድንበርን ለመወሰን የታየ እርምጃ ባለመኖሩ በጉዳዪ ላይ ውዝግቦች እንደቀጠሉ ነው።

ይህም ብቻ ሳይሆን ለአርሶ አደሮቹ መስከረም ወር ላይ ቤቶቹ ይሰጣቹሀል ተብሎ እየተነገራቸው እንደተባለው የአዲስ አበባና የኦሮምያ የወሰን ጉዳይ መስከረም ወር ላይ መቋጫ ስለማግኘቱ እስካሁን ማረጋገጫ የለም።