ኦባማ ባዲሳባ፣ የሚጠበቁ ምጸቶች
(ቸሩ ቸርችሩ)
(ሀ) ፕሬዚደንት ኦባማ ነገ እሑድ አዲስ አበባ ይገባሉ። አንዱን ቀን- እንደደንቡ ሰኞ-በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ራት እንደሚኖር ይጠበቃል። የታሪክ ምጸቱን ከዚያ ጀምረን እናደንቃለን። ራቱ ምኒልክ በሠሩት፣ ዛሬም በስማቸው በሚጠራው ቤተ መንግሥት ይሆናልና፤ መቼም ለራት ሼራተን፣ አለዚያም መቀሌ-አዳማ- ባህርዳር-አዋሳ-አሳይታ— አይወስዷቸውም ብዬ ነው። ራቱንም ቦታውንም መቃወሜ አይደልም። አገር የመሥራት ሙከራ ቀልድ አይደልም፣ የሙከራው ሒደትና ውጤት ምንም ይሁን የሞካሪዎቹ ስም ድንገት ተኖ አይጠፋምና እንዲህ ያለውን ታሪካዊ ምጸት ይጋብዘናል ለማለት ነው።(ኦባማ ከጋዜጣዊ መግለጫ በስተቀር የፖሊሲና የፖለቲካ ጉዳዮችን በስፋት የሚናገርበት መድረክ ስለመኖሩ አላወቅንም። ከኖረ ግን፣ አድዋን ማንሳቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፣ ምኒልክንም ያነሳቸው ይሆናል ማለት ነው፣ ወይም ጣይቱን)
(ለ) ኦባማ የሚናገረውን የሚያውቅና ታሪክን የሚበዘብዝ ተናጋሪ ነው። (አንዳንድ አንባቢዎች እንደሚመስላቸው መበዝበዝ ትርጉሙ አሉታዊ ብቻ አይደለም። አልገባኝም የሚል የአማርኛን ዘይቤ ማጥናት።) በዚህ ልማዱ የኦባማ የአፍሪካ ኅብረት ንግግር ቢያንስ ጥቂቶቹን የአፍሪቃ አንድነት ድርጅትን (ያሁኑ የአፍሪቃ ህብረትን) መስራቾቹ መጥራቱና ማሞገሱ አይቀር ይሆናል። ሐውልት የቆመላቸውንም ያልቆመላቸውንም። ስም መጥቀስ ከጀመረ ቀኀሥን ይዘላቸዋል ብዬ አልገምትም። በዚያ ላይ ሰውየው ለአሜሪካ የመጀመሪያው የጥቁር ንጉሥ ጎብኚ ነበሩ፣ ተወዳጁ ኬኔዲ የተቀበላቸው። ይህም የታሪክ ምጸት መሆኑ አይቀርም፣ በተለይም ለህወሃት ጸረ-ቀኀሥ ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞች። “እኛ ማርከን አመጣነው” ያሉት ሰውዬ አምርረው የሚጠሉዋቸውን መሪ ካመሰገነ ነገሩ ከምጸት ሌላ ምን ይሆናል?
(ሐ) ስለኢትዮጵያ የቅርብ ዓመታት የኢኮኖሚ እድገትም ማንሳቱ አይቀርም። መቼም ለዚህ ኀይለማርያምን አይጠቅስም፣ ሟቹን መለስ ዜናዊ እንጂ። ኢትዮጵያ ራሷንም አሜሪካንም ወክላ እነአልሻባብን ስለመዋጋቷም ያመሰግናል፣ እዚህም ላይ ቢሆን ኀይለማርያም የፕሮጀክቱ አሳቢም አስፈጻሚም አይደሉም። የኦባማ ምስጋናው በሰምም ይሁን በወርቅ የሚሔደው ወደ መለስ ነው። ይኼም የታሪክ ምጸት አያጣም፣ መለስን በሶማሊያ ዘመቻዎቹ የሚተቹ ብዙ ናቸውና።እንግዲህ የኦባማ ንግግር ሦስቱንም አወዛጋቢ መሪዎቻችንን በበጎ ገጽታቸው ሊያነሳቸው ይችላል ማለት ነው። ከውጭ ስንታይ መልካችን እኛ ከምናስበው የተለየ ሊሆን እንደሚችል ለማስታወስ ጥሩ አጋጣሚ ነው። ታሪካችንን በቁጣ ሳይሆን በትህትና መመልከትም እንደሚያስፈልግ (እንደሚቻልም ጭምር) ያስታውሰን ይሆን?
መ) የመጨርሻው ምጽት ኦባማ ጋና ላይ ያደረገው ንግግር በአዲስ አበባ ጉብኝቱ ሊለው ከሚችለው ነገር ጋራ ሊኖረው የሚችለውን ግንኙነት ይመለከታል። ኦባማ በጋና ፓርላማ “Africa needs strong institutions, not strong leaders” ብሎ ነበር። በ12ኛው ቀን የወቅቱ በኢትዮዽያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ያማሞቶ ወደ አገራቸው ከመመለሳቸው በፊት ከመለስ ጥሪ ይደርሳቸዋል። አምባሳደሩ የኦባማን ንግግር ያብራራሉ፣ ስለኢትዮጵያም የሚያሳስባቸውን የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ ጉዳይ ያነሳሉ። ዊኪሊክስ ባቀረበልን ኬብል የአምባሳደሩ ማስታወሻ የመለስን መልስ መዝግቦልና ‘Prime Minister Meles responded that he agreed with President Obama’s statement that Africa needs strong institutions, but disagreed with the president’s argument that “development depends on good governance” and democracy. Meles argued that there is “no proof that democracy and/or good governance are either necessary or sufficient for development.
‘ ያማሞቶ በመልእክታቸው መጨረሻ የሚከተለውን ትዝብት ከትበዋል ‘The Prime Minister’s frank statements confirm Embassy Addis Ababa’s consistent argument over the past two years: Ethiopia’s political strategy is fundamentally different from any sense of “democracy” as commonly understood in the United States or western countries. Despite the second word in the GoE’s prevailing ideology, “Revolutionary Democracy” reflects an approach to governance and development that, while arguably FOR the people, is neither OF, or BY, the people.’
ኦባማ ለዘላቂ ልማት፣ “መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ አስፈላጊ ናቸው” የሚለውን አቋሙን ይከላከላል ወይስ ወደጎን ብሎት ያልፋል? “ልማታችንን ለማረጋገጥ ዴሞክራሲ አያስፈልገንም” በሚል ውስጣዊ እምነት ለሚመሩት የኢትዮጵያ መሪዎች ምን ይላቸው ይሆን? መልሱ የትኛውም ቢሆን፣ ዴሞክራሲ በግልጽና በመንግሥት ፖሊሲ ደርጃ ወሳኝ ጉዳይ አይደለም በሚባልባት አገር ተገኝቶ ስለዴሞክራሲና ስለተቋማት የሚናገር ከሆነ ምጸቱ አይቀርብንም። ምጸቱ ፍጹም የሚሆነው ግን ኢትዮጵያውያንን አግኝቶ የሚናገርበት አጋጣሚ ከኖረ ነው። በአጠቃላይ ለአፍሪካ በሚያቀርበው ንግግርም ቢሆን ምጸታችን አታመልጠንም።
(ሠ) ምርቃት። ለትልቅ እንግዳ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በሚደረግ የራት ግብዣ ላይ የሚጋበዙትን ሰዎች መምረጥም ትልቅ ጉዳይ ነው። አሸርጋጅና አጫዋች፣ አላዋቂና አመለኛ ጋብዞ መገመት አለ። ጋባዥ አገሬን ይወክላሉ፣ ተከብረው ያስከብራሉ የሚላቸውን ለመምረጥ አብዝቶ ይጨነቃል። እስቲ የኢሕአዴግ ኢትዮጵያን የሚወክሉትን ለታሪካዊና ትልቅ ግብዣ የሚመጥኑ የተባሉትን ትልልቅ ሰዎች እናያቸዋለን! ለመፍረድ አንቸኩል፣ ድሮም ድግስ መጥራት ነቀፋ አያጣውም።