እነ በረከት ስምኦን ህዝባዊ ድርጅትን ያለ አግባብ መርተዋል በሚል የሙስና ወንጀል ክስ ተመሰረተባቸው፡፡
ዋዜማ ራዲዮ- የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በረከት ስምኦን እና የኮርፖሬቱ የቀድሞ ዋና ስራ አስፈፃሚ እንዲሁም ሌሎች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ግለሰቦች የተካተቱበት ክስ ባሳለፍነው ሳምንት ሚያዝያ 7 ቀን 2011 ዓም ነበር ለተከሳሾች የደረሳቸው፡፡
በቀጣዩ ቀን ደግሞ በችሎት የቀረቡ ቢሆንም የክሱ ገፅ ብዙ መሆኑን እና የህግ ድጋፍ አለማግኘታቸውን ለችሎት አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ተለዋጭ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት ዛሬ ሚያዝያ 14 ቀን 2011 ዓም ችሎት ቀርበው ነበር፡፡
የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ ሀላፊዎች እና የኢህአዴግ የቀድሞ ባለስልጣናት የሆኑት አቶ በረከት ስምኦን እና ታደሰ ካሳ ከጥር 15 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ከህግና መመርያ ውጭ ግዥ በመፈፀም የሀብት ብክነት ፈፅመዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ውለው በማረፊያ ቤት መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ጉዳያቸውንም የክልሉ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራውን በበላይነት እየመራው የባህርዳርና አካባባው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ደግሞ ሲመለከተው ቆይቷል፡፡
ሆኖም ክስ ሲመሰረት ግን ከሳሽ የአማራ ክልል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መዝገቡን ወደ ክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መርቶታል፡፡
የክስ መዝገቡ አራት ክሶችን በውስጡ የያዘ ሲሆን የወንጀለኛ መቅጫ የስነስርዓት ህጉ አንቀፅ 129 በሚያዘው መሰረት ዛሬ ጠዋት በዳኞች አማካኝነት በቁጥጥር ስር ውለው ክሳቸውን ለሚከታተሉ ተከሳሾች በዝርዝር ተነቦላቸዋል፡፡ የመጀመርያው ክስ እንደሚያስረዳው ከሆነ ተከሳሾቹ የዳሽን ቢራ ፋብሪካን አክሲዮን የአዋጭነት ጥናት ሳይደረግ እንዲሸጥ አድርገዋል የሚል ነው፡፡
ዱየት ቢቬሬጅ ለተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ባልተገባ ዋጋ ማለትም 50 ነጥብ 14 በመቶ የሚሆነውን የአክሲዮን ድርሻውን በ90 ሚልዮን ዶላር እንዲሸጥ የተደረገ ሲሆን ይህም የጥረት ኮርፖሬትን ጥቅም የሚነካ ነው በማለት የሚተነትን ክስ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎም ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ኮርፖሬቱ ማግኘት የሚገባውን የ1.8 ቢሊየን ብር በላይ ጥቅም አስቀርተውበታል ወይንም እንዲጎዳ አድርጓል በማለት አቃቤ ህግ በክሱ አጠቃሏል፡፡
በሁለተኛው ክስ ደግሞ አቃቤ ህግ በባህርዳር ከተማ ከአመታት በፊት ኮርፖሬቱ እገነባዋለው ብሎ አቅርቦት የነበረውን የኤሌትሪክ ውሀ እና ዊንድ ጄነሬተር ፕሮጀክት አንስቷል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ምንም አይነት የአዋጭነት ጥናት ሳይካሄድም ሆነ የቦርድ ውሳኔ ሳይደረግበት 1.3 ቢሊየን ብር ቢተላለፍም ፕሮጀክቱ ግን እስካሁን እንዳልተጀመረ ተገልፅዋል፡፡
ስራውን ለመስራት የተስማማው ዱቬንቱስ ዊንድ ቴክኖሎጂ ከተባለ ድርጅት ጋር ሲሆን ምንም አይነት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ባልታየበት ከ210.2 ሚሊየን ብር በላይ ክፍያ እንዲፈፀም አድርገዋል የተባለ ሲሆን ይህም በኮርፖሬቱ ላይ ከፍተኛ ብክነት እንዳደረሰ መገለፁን ምንጫችን ገልፆልናል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም የዱቬንቱስ ዊንድ ቴክኖሎጂ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት እና ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ዳንኤል ይግዛው 3ኛ ተከሳሽ ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡ አቶ ዳንኤል በግላቸው ጠበቃ አቁመው የቀረቡ ሲሆነን ሁለቱ የቀድሞ ባለስልጣናት በረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ ግን ከዚህ ቀደም የነበሯቸው ጠበቆች የደረሰባቸውን ዛቻ ተከትሎ ምንም እንኳን በጠበቃ የመወከል መብት ቢኖራቸውም በዛሬው ችሎትም ያለ ጠበቃ ነው የቀረቡት ፡፡
አቃቤህግ በሶስተኛነት እና በአራተኛነት ያቀረባቸው ክሶች ደግሞ በጥረት ኮርፖሬት ባልተገባ መልኩ የሌሎችን እዳ እንዲከፍል ሆኗል የሚል ነበር፡፡
ይህም ከላይ የተጠቀሰው ኩባንያ ያለበትን እዳ በጥረትኮርፖሬት እንዲከፍል ተደርጎ 46 ሚሊዮን ብር ገደማ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ኮርፖሬቱ የሚያስተዳደራቸው የተለያዩ የንግድ ተቋማት ደግሞ ለሚበደሩት ገንዘብ ከኮርፖሬቱ አካውንት እንዲከፈል በማድረግ የ102 ሚሊየን ብር ጉዳት አድርሰዋል በማለት የሚያብራሩ ናቸው፡፡
ይህን ብቻ አልነበረም አቃቤ ህግ ያካተተው ተከሳሾቹ ከተለያዩ የግል እና የመንግስት ባንኮች የተበደሩትን ገንዘብ ከኮርፖሬቱ የባንክ አካውንት እንዲከፈል አድርገዋል በማለትም ክሱ ላይ አክሎ ነበር፡፡ እናም ተከሳሾቹ በቀረበባቸው ክስ ላይ ያላቸውን የመጀመርያ ደረጃ መቃወሚያ ጉዳያቸውን ለሚያየው ችሎት በፅሁፍ አስገብተዋል፡፡
ሁለቱን መርምሮ ብይን ለመስጠትም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ቀጣይ ቀጠሮውን ለግንቦት 2 ቀን 2011 ዓም ይዟል፡፡
በአቃቤ ህግ አሁን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ድርሶበታል የተባለው ጥረት ኮርፖሬት በ1988ዓም ሲሆን የተመሰረተው፤ ሲመሰረት ዋና አላማውን በአማራ ክልል የተለያዩ ኢንቨስተመንቶችን ለማስፋፋት አቅዶ ነበር፡፡
እንደ አምባሰል የንግድ ስራዎች ድርጅት ፣ ዳሽን ቢራ ፋብሪካ፣ ዋሊያ ቆርኪ ፋብሪካ፣ ገንደ ውሃ የጥጥ መዳመጫ ፋብሪካ፣ ጎንደር ብቅል ፋብሪካ፣ ጣና ኮሙኒኬሽን የሞባይል መገጣጠሚያ እና ሌሎች ከ 20 ላይ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን በስሩ የያዘ ነው፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]