received_1755485837827780(ዋዜማ ራዲዮ) ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 25/2010 (ሜይ 3/2018) በመላው ዓለም የፕሬስ ነጻነት ቀን ተከብሯል፡፡ ናይሮቢ ዌስትላንድ አካባቢ በሚገኘው የ“አምነስቲ ኢንተርናሽናል ኬንያ” ቢሮ በተካሄደ ፕሮግራም በክብር እንግድነት የተጋበዘው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ “መገናኛ ብዙሀን ምን ዓይነት ዕክል ሊገጥማቸው ይችላል” በሚለው ርዕስ ዙሪያ ማብራሪያ ሠጥቷል፤ ከታዳሚዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሠጥቷል፡፡

ከተቀረው የአሕጉሪቱ ክፍል… ምስራቅ አፍሪካ በተለየ የፕሬስ መብት ረገጣና አፈና እንደሚበረታበት ያስረዳው እስክንድር ይሕ ያጋጠመው አካባቢው ከደቡብ፣ ሰሜንና ምዕራብ አፍሪካ በመለየቱ ሳይሆን፣ በቀጠናው የአመራር ቀውስና የልሂቃን ክሽፈት በማየሉ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ የተንሰራፋው ፖለቲካዊ ቀውስ የክልሉን ሁኔታ የከፋ ስላደረገው፣ ለአጠቃላይ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ የሚካሄድ ትግል የፕሬስ ነጻነትና ሌሎችም መብቶች እንዲከበሩ እንደሚያግዝ እምነቱን ገልጿል፡፡ ተሳታፊዎች ከእስክንድር አቋም በተቃራኒ ሀሳብ አንስተው ለመሞገት ቢሞክሩም፣ እሱ ግን ከኢትዮጵያ ተሞክሮ የተረዳው አጠቃላይ የዲሞክራሲ ለውጥ ሲመጣ፣ ሌሎች መብቶች እንደሚከበሩ፣ ከዚህ ውጪ መጠነኛ ለውጥ ቢታይ እንኳ ወደኋላ ሊቀለበስ የሚችልበት ዕድል ሠፊ መሆኑን ነው፡፡

ናይሮቢ የቀጠናው ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ማዕከል እንደመሆኗ፣ የፕሬስ ነጻነት ቀን ከመከበሩ ቀናት አስቀድሞ እስክንድር ወደ ከተማይቱ እንዲመጣ የተደረገው ከተለያዩ ሚዲያ ተቋማት ጋር እንዲገናኝ በመሆኑ ቃለ ምልልስ ሲሰጥ መሠንበቱን፣ ስለ ኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁናቴ፣ የዲሞክራሲ ጥያቄና ስለ ፕሬስ ነጻነት ማስረዳቱን ለዋዜማ ገልጿል፡፡ በሀገር ቤት የሕዝቡ የዲሞክራሲ ጥያቄ የማይቀለበስበት ደረጃ መድረሱን የጠቆመው እስክንድር አፈናው በበረታ ቁጥር ሕዝቡ ከሥርዓቱ ጥገናዊ ሳይሆን ሥር ነቀል ለውጥ መሻቱ መጨመሩን አስረድቷል፡፡

በናይሮቢ የሚገኙ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች በዋዜማው ሚያዝያ 25/2010 የፕሬስ ነጻነት ቀንን፣ ከስድስት ዓመት ተኩል እስር ከተፈታው ባልደረባቸው እስክንድር ነጋ ጋር አክብረውታል፡፡ ከጋዜጠኞች ባሻገር ስደተኛ የቀድሞ የአንድነትና የሰማያዊ ፓርቲ አባላት፣ አክቲቪስቶችና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በዝግጅቱ ታድመዋል፡፡

ከመንግስት እስራትና ማዋከብ ሽሽት በርካታ ጋዜጠኞች ሀገር እንደለቀቁ ቀዳሚ ማረፊያቸውን በኬንያ ያደርጋሉ፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ስድስት ጋዜጣና መጽሔቶች ሲዘጉ ከተሰደዱት ጋዜጠኞች መሐል የማራኪ መጽሔት ዋና አዘጋጅ ሚሊዮን ሹርቤ እና የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ምክትል ዋና አዘጋጅ ኢብራሒም ሻፊ አሕመድ በወጡበት ቀርተዋል፡፡ በናይሮቢ የፕሬስ ቀንን ያከበሩ ጋዜጠኞች በሞት የተነጠቁ ጓደኞቻቸውን ዘክረዋል፤ ሻማ አብርተው የሕሊና ጸሎት አድርገዋል፡፡

በዝግጀቱ “በስደት ያለፉ ወንድሞቻችንም ሆነ ባለፉት ሶስት ዓመታት ለዲሞክራሲ በተካሄደው ተጋድሎ ሕይወታቸው ያለፉ፣ አካላቸው የጎደሉ ወገኖቻችን መስዋዕትነት በከንቱ እንደማይቀር መግለጽ እፈልጋለሁ” ያለው የክብር እግዳው እስክንድር ነጋ “…እስካሁን ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል፤ ምናልባት ከዚህ በኋላም ተጨማሪ መስዋዕትነት ያስፈልገን ይሆናል፤ ስለ መጨረሻው ግን በእርግጠኛነት መናገር እንችላለን፤ በመጨረሻ በሀገራችን የምንፈልገውን የነጻነት አየር እንተነፍሳለን፤ የዲሞክራሲ መብት የሚከበርበት፣ ሀሳባችንን በነጻነት የምንገልጽበት፣ የምንደራጅበት፣ የምንፈልገውን መንግስት የምንመርጥበት፣ በሠላም የምንኖርባት ሀገር ትኖረናለች፡፡ አምባገነኖች በዚህ መንገድ ላይ ያቆሙት ተግዳሮት መጨረሻውን ፈጽሞ አያስቀይረውም፤ አምባገነን ፓርቲ በየትኛውም ሀገር ሕዝብን አሸንፎ አያውቅም፤ በእኛም ሀገር ቢሆን አምባገነን ኃይል እስከ መጨረሻው ሊያሸንፍ አይችልም፤ የመጨረሻው ድል የሕዝብ ነው፤ የመጨረሻው ድል ዕውነት ነው፤ ሕዝብም፣ ታሪክም፣ እውነትም ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈጣሪ ይሕን ያውቃል፤ ዲሞክራሲያዊ ሀገር እንገነባለን” ብሏል፡፡

“ሪፖርተርስ ዊዝ አውት ቦርደርስ” የተሰኘው መቀመጫውን በፓሪስ ፈረንሳይ ያደረገው የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም… ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት የፕሬስ መብትን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከ180 ሀገራት 150ኛ ደረጃን መያዟን አሳውቋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በ2006 ዓም የስድስት ጋዜጣና መጽሔቶችን ቢሮ ከዘጋና ከ30 በላይ ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ ካስገደደበት እርምጃው አንስቶ አሁን ድረስ በፕሬስ ነጻነት ላይ ጉልሕ ለውጥ አለመታየቱን ጠቁሟል፡፡ በሀገሪቱ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋዜጠኞችን ለማሰርና ሕዝቡም መገናኛ ብዙሀንን እንዳይከታተል ሠበብ እንደሚሆን የተቋሙ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

Source-RSF
Source-RSF

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሀዋሳ ከተማ ውይይት ባደረጉበት ወቅት “በአሜሪካን ሀገር ሚዲያ ያላቸው፣ ለኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እያሉ የሚናገሩ፣ የሚጮሁ፣ የሚቆጡ፣ የሚጨነቁ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ዋና ቢሮዋቸው አዲስ አበባ እንዲሆን እንፈልጋለን” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ገለጻ በመልካምነቱ የሚጠቅሱ በስደት የሚገኙ ጋዜጠኞች እንደሚናገሩት… ለረዥም ዓመት እስራት ምክንያት የሆነው አፋኙ የጸረ ሽብር አዋጅ ባልተቀየረበት፣ ነጻውን ሚዲያ እግር ተወርች የቀፈደደው ምሕዳር በቀጠለበት፣ ከእስር የተፈቱ ጋዜጠኞች የፕሬስ ፈቃድ እንዳያወጡ በታገዱበት ሁኔታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ብቻውን የፕሬስ ነጻነት ማረጋገጫ አይሆንም ይላሉ፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምትተዳዳር ሀገር ነጻ ፕሬስ የማይታሰብ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲታመኑ መቅደም ያለበትን እርምጃ ወስደው ማሳየት፣ ከንግግራቸው በላይ ይበልጥ ተዓማኒ እንደሚሆንም ያስረዳሉ፡፡

ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት የፕሬስ ነጻነት ሂደት ላይ የታዘበውን እንዲያብራራ ከዋዜማ ሬዲዮ ለቀረበለት ጥያቄ እስክንድር ነጋ ምላሽ ሲሰጥ “በፊት ያልገባን ነገር ነበር” ሲል ከልምድ ያገኘውን ትምሕርት እንዲህ ይገልጸዋል፡-

“ትልቁ ተሞክሯችን የፕሬስ ነጻነትን ብቻውን ልናስከብረው እንደማንችል መረዳታችን ነው፤ አጠቃላይ ነጻነት በሌለበት፣ የፕሬስ ነጻነትን ነጥለን እንደ ደሴት ልናስከብር አንችልም፤ መጀመሪያ ላይ ይሄ አልገባንም ነበር፤ ለራሳችን… በጠባቧ መብት መከበር ዙሪያ እናተኩር ነበር፤ ይሄ ፍጹም ስሕተት ነበር፡፡ የትም አላደረሰንም፤ የዲሞክራሲን ጥያቄና የፕሬስ ነጻነት ጥያቄን ነጣጥለን መሄድ አይገባም፡፡ በሙያና ሲቪክ ማሕበራትም ሆነ በማሕበረሰብ ደረጃ የሚነሱ የመብት ጥያቄዎች ሁሉ የተያያዙ ናቸው፤ ወይ አንድ ላይ ይከበራሉ አለያም አንድ ላይ አይከበሩም፤ ያለፉት ሀያ ዓመታት ተሞክሮ ያሳየን ዋነኛ ግንዱ ይሕ እንደሆነ ነው፡፡ ስለዚህም ወደን ሳይሆን የግድ ለአጠቃላዩ ነጻነት መታገል ይኖርብናል፤ የምንታገለው የፖለቲካ ዓላማና የምናስፈጽመው አጀንዳ ኖሮን ሳይሆን ሙያችንን በነጻነት ለማራመድ ከሁሉም የዲሞክራሲ ኃይሎች ጋር የመተባበር ግዴታ አለብን፡፡ ተባብረን አጠቃላዩ ነጻነት ከመጣ በኋላ ሁላችንም ወደየመስካችን እንሄዳለን፡፡”

ጋዜጠኝነትና አክቲቪስትነት እንደምን አብሮ ይራመዳል? አብሮ ማስኬዱ ምን ያሕል ያስጉዛል? ገለልተኝነትና ሚዛናዊነትን ጥያቄ ውስጥ አያስገባውምን? ለሚለው ጥያቄ እስክንድር የሚከተለውን ይላል፡

“በዲሞክራሲያዊ ሀገሮች ሁለቱ አብረው ባይሄዱ ይመረጣል፤ ሜይንስትሪም ሚዲያ ላይ ሁለቱ አብረው የሚሄዱ አይደሉም፤ እኛ የምንታገለው እነዚህን ያለያየ ሜይንስትሪም ፕሬስ የሚመጣበትን ድባብ ለመፍጠር ነው፤ ሁለቱን ለመለያየት የግድ ዲሞክራሲ መኖር አለበት፤ ዲሞክራሲ በሌለበት ሀገር ግን ሁለቱን ነጣጥሎ ለመጓዝ ሁኔታው አይፈቅድም፤ የጋዜጠኝነት ተግባር ሁኔታዎችን መዘገብ ብቻ ነው፡፡ በእንደኛ ዓይነት ሀገር ሁኔታ እንደ ጋዜጠኛ ሂደቶችን ከመዘገብ ባሻገር ጋዜጠኛው የክስተቱ፣ የኹነቱ አካል ይሆናል፡፡ የሌሎች ሰዎች ብቻ ሳይሆን የጋዜጠኛውም መብት ይደፈጠጣል፤ ስለዚህ ጋዜጠኛው የጉዳዩ ተሳታፊ ለመሆን ይገደዳል፤ ዲሞክራሲ ባለበት ግን ጋዜጠኛው የኹነቱ አካል አይሆንም፤ የጋዜጠኛው ተግባር ስለ ኹነቱ መዘገብ ይሆናል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ሁኔታዎች የግድ ገፍተው የኹነቱ አካል ያደርጉሀል፤ ስትደበደብ፣ ጋዜጦችህ ሲዘጉ የኹነቱ አካል ሆንክ ማለት ነው፤ በአምባገነናዊ አገር ውስጥ ሁለቱን ነጣጥሎ መሄድ አይቻልም፤ እኛ የምንኖረው በአምባገነን አገዛዝ ሥር እንደመሆኑ ራሳችንን ከሁኔታው ነጥለን ታዛቢዎች አለያም ስንክሳር መዝጋቢ መሆን አይቻለንም፡፡ ጋዜጠኝነትን ከአክቲቪዝም የመለያ መስመሩ የዲሞክራሲ መኖርና አለመኖር ነው፡፡ እንደ ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካና ምዕራቡ ዓለም ያለበት ዓይነት ነጻነት ስናገኝ ነጥለን ሜይንስትሪም መገንባት እንችላለን፤ ምክንያቱም የዲሞክራሲ ሥርዓት ዋልታና ማገር ነውና፡፡”

በ1984 የፕሬስ አዋጅ ከመጽደቁ ወራት አስቀድሞ ሕትመት የጀመረው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ በከፍተኛ አፈና ውስጥ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በፊት የነበረውን አንጻራዊ ነጻነት ግን ከምርጫ 97 በኋላ ተነጥቋል፡፡ በቀን ከአምስት ያላነሱ ጋዜጦች ለንባብ የሚቀርቡበት ዘመን የቅንጦት ያሕል መታየት ጀምሯል፡፡ የምርጫ 97 ፖለቲካ ግለት ጣራ በነካበት ሰሞን የጋዜጣዎች ሕትመት ብዛት 130 ሺህ ኮፒ ይደርስ ነበር፡፡ አሁን 10 ሺህ ቅጂ የሚያሳትም መገናኛ ብዙሀን መመልከት ብርቅ ነው፡፡ ዕለታዊዎቹ የኬንያ ጋዜጣዎች “ዴይሊ ኔሽን” እና “ዘ ስታንዳርድ” እንደ ቅደም ተከተላቸው በየቀኑ ከሚያሳትሙት 170 ሺህ እና 75 ሺህ አንጻር ልዩነቱ እጅግ የሰፋ ነው፡፡

100 ሚሊየን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ሶስት ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጣዎች (ሪፖርተር፣ ሠንደቅ፣ አዲስ አድማስ) እና ሶስት ሳምንታዊ የእንግሊዝኛ ጋዜጣዎች (ዘ ሪፖርተር፣ ፎርቹን፣ ካፒታል) እንዲሁም ጥቂት መጽሔቶች ብቻ ናቸው የሚታተሙት፡፡ የመንግስት ልሳን ከሆኑት አዲስ ዘመንና ኢትዮጵያን ሔራልድ በቀር አንድም ዕለታዊ ነጻ ጋዜጣ የለም፡፡

በናሚቢያ ዊንድሆክ የጸደቀውን ሠብዓዊ መብት ድንጋጌ ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ በየዓመቱ ሜይ 3 የዓለም ፕሬስ ነጻነት ቀን ተብሎ እንዲከበር ወስኗል፡፡ ዋና ዓላማውም መንግስታት ሀሳብን በነጻ የመግለጽ መብት እንዲከበር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማሳሰብ፣ እንዲሁም የፕሬስ ነጻነት መከበርን ጠቀሜታ ለማመላከት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁናቴ ግን ማሳሰቢያ ሊሰጠው የሚገባው መንግስት በዓሉን በየዓመቱ በማክበር ላይ ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ በተከታታይ ዓመታት የተከበሩትን ሠባት የፕሬስ ነጻነት በዓል ያዘጋጀው የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር መሆኑ ታላቅ ምጸት ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ የፕሬስ ነጻነት ክብረ በዓል ላይ በእንግድነት የተገኙት የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ወ/ሮ ፍሬሕይወት አያሌው “በውጪ ያሉ የሚዲያ ነጻነት ተሟጋች ነን ባዮች በሚያወጡት ሪፖርት ተነስተን ምንም አንልም፤ ፕሬስ ለአገሪቱ ዕድገት አዎንታዊ ትችቶችን ማቅረብ ይኖርበታል እንጂ አሉታዊ ትችት ሊያቀርብ አይገባውም” ያሉበት ንግግርም የመንግስትን “አልተችም” አቋም በግልጽ ያንጸባረቀ ነው፡፡