ዋዜማ ራዲዮ- ኤርትራ በኢትዮጵያ ላላት ኢምባሲ በኢምባሲው ለረጅም ጊዜ በከፍተኛ ዲፕሎማትነት ያገለገሉትን ቢንያም በርሄን ጉዳይ አስፈጻሚ አድርጋ መሾሟን ይፋ አድርጋለች።
ጉዳይ አስፈጻሚ ቢኒያም የሹመት ደብዳቤያቸውን በዚህ ሳምንት ለኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ያቀረቡ ሲሆን፣ ለአፍሪካ ኅብረት ጭምር የኤርትራ ቋሚ ተወካይ ሆነው እንደሚያገለግሉ ተገልጧል።
ኤርትራ ላለፉት ሦስት ዓመታት አምባሳደር ሠመረ ርዕሶምን በባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ወክላ የቆየች ሲሆን፣ በተያዘው ወር መግቢያ ግድም ግን አምባሳደር ሠመረ የሥራ ዘመናቸውን አጠናቀዋል ተብለው ወደ አገራቸው መመለሳቸው ይታወሳል።
ኤርትራ የዲፕሎማቲክ ውክልናዋን ለምን ከአምባሳደር ወደ ጉዳይ አስፈጻሚ ደረጃ ዝቅ እንዳደረገች ወይም የጉዳይ አስፈጻሚው ሹመት ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ የኤርትራ መንግሥት ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ያለው ነገር የለም።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ አዲሱ የኤርትራ ጉዳይ አስፈጻሚ የሹመት ደብዳቤያቸውን ከማቅረባቸው ትንሽ ቀደም ብላ ለአሥመራ አዲስ አምባሳደር መሾሟን አስታውቃ ነበር። አዲሱ ተሿሚ አምባሳደር ፈቃዱ በየነ ናቸው። ሁለቱ አገሮች ከሦስት ዓመት በፊት እንደገና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ካደሱ ወዲህ ባሉት ጊዜያት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የፖለቲካ ጉዳዮች ኦፊሰርና በኋላም ጉዳይ አስፈፃሚ የነበሩት ዘሪሁን መገርሳ በአሥመራ የኢትዮጵያ ወኪል ሆነው አገልግለዋል።
ኤርትራ የዲፕሎማሲ ውክልናዋን ወደ ጉዳይ አስፈጻሚ ዝቅ ማድረጓን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ርምጃ ትወስድ እንደሆነ የጠየቅናቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ምንጮች በጉዳዩ ላይ አስካሁን ውሳኔ እንዳልተላለፈ ነግረውናል። በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግን አንድ አገር የዲፕሎማሲ ውክልና ደረጃውን ዝቅ ሲያደርግ፣ ሌላኛው አገር ተመሳሳይ ርምጃ መውሰዱ የተለመደ ነው።
ኤርትራ ለኢትዮጵያ በጉዳይ አስፈጻሚነት የሾመቻቸው ቢንያም በርሄ፣ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደሉም። በ1980ዎቹ ሁለተኛ አጋማሽ የያኔው ወጣቱ ቢንያም የኢትዮጵያ መንግሥት ለኤርትራዊያን ተማሪዎች በሰጠው ነጻ የትምህርት ዕድል የኤርትራ መንግሥት ልኳቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርት ክፍል ተማሪ የነበሩ ናቸው። ሆኖም ግንቦት 1990 ዓ.ም የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ፣ ቢንያም ትምህርታቸውን ሳያጠናቅቁ ከሌሎች ነጻ ትምህርት ዕድል ተሰጥቷቸው ከነበሩ ኤርትራዊያን ተማሪዎች ጋር በመንግሥት ውሳኔ ወዱያውኑ ከኢትዮጵያ ተባረዋል።
በኋላ ግን ቢንያም አገራቸው ኤርትራ አዲስ አበባ በሚገኘው አፍሪካ ኅብረት ባላት የዲፕሎማቲክ ውክልና ውስጥ መድባቸው ከአስር ዓመታት በላይ በፖለቲካ ኦፊሰርነት፣ በምክትል ቋሚ መልዕክተኛነት እና በጉዳይ አስፈጻሚነት ለዓመታት አገልግለዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]