Photo credit Anadolu

ዋዜማ ራዲዮ- የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በሀገራት ኢኮኖሚ ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ እና ወረርሽኙን ለመግታት እንዲሆን የአለም ባንክ በቅርቡ በተለይ ለታዳጊ ሀገራት የማገገሚያ ድጋፍ ማድረጉ አይዘነጋም።


ከዚህ ውስጥም ኢትዮጵያ ወደ 207 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ከባንኩ አግኝታለች። ይህንን የአለም ባንክ የኮቪድ 19 ማገገሚያ የድጋፍ ገንዘብ ኢትዮጵያ ለክትባት ግዥ ልታውለው እንቅስቃሴ መጀመሯን ዋዜማ ከመንግስታዊ ምንጮች ስምታለች።


በዚህም መሰረት ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ከተሰኘው ከታዋቂው የአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ኩባንያ የኮቪድ 19 ክትባት ለመግዛት ውል እንደፈፀመችም ተነግሯል።


ኢትዮጵያ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮቪድ 19 ክትባትን ለመግዛት የፈፀመችው ውል 3 ሚሊየን ለሚጠጋ የክትባት ጠብታ (Dose) ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ወደ 4 ሚሊየን የሚጠጋ የአስትራ ዜኒካ ክትባትንም በግዥ ለማስገባት አስፈላጊው ሁሉ እንደተፈፀመ ከጤና ሚኒስቴር ምንጮች ስምተናል።


ኢትዮጵያ ኮቫክስ ከተሰኘው የኮቪድ 19 ክትባትን ለታዳጊ ሀገራት ለማዳረስ በተቋቋመው ጥምረት አማካኝነት በዚሁ አመት መጋቢት ወር ላይ ወደ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ጠብታ (Dose) የአስትራ ዜኒካ ክትባት ተረክባ የመጀመሪያ ዙር ክትባት ስታዳርስ መቆየቷ ይታወቃል።


ሁለተኛውን ዙር ክትባት ለማዳረስ የሚያስችል የአስትራ ዜኒካ ክትባት በተለይ 391 ሺህ የአስትራ ዜኒካ ክትባትን ሀገሪቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከኮቫክስ ጥምረት ትረከባለች ተብሎም እየተጠበቀ ነው። ክትባቱ ምናልባትም በቀጣዮቹ አምስት ቀናት ኢትዮጵያ እንደሚገባም ይጠበቃል።


ከዚህ በተጨማሪም ከነሃሴ እስከ መስከረም ወር ድረስ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ጠብታ የአሰትራ ዜኒካ ክትባትን ለመረከብ እየተዘጋጀች የምትገኘው ኢትዮጵያ ሰሞኑን ከሚገባው ወደ 400 ሺህ ጠብታ ከሚጠጋው ክትባት ጋር በድምሩ ወደ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ጠብታ ክትባትን እንደምታገኝ ይጠበቃል።


ይህ ደግሞ በመጀመሪያው ዙር የአስተራ ዜኒካ ክትባት የከተበቻቸውን እና አዲስ የሚከተቡ ዜጎቿን በሙሉ ሁለተኛ ዙር የአስትራ ዜኒካ ክትባት ለማዳረስ እንደሚያስችላትም ተነግሯል። [ዋዜማ ራዲዮ]