የኦሕዴድ አመራር በኦሮሞ ህዝብ መሪነት ኢትዮጵያዊ ህብረ ብሄራዊነትን ገና ሳያጠናክር ወደ ውህደት ቢገባ አጀንዳውን እንደተነጠቀ ሊያስብ ይችላል፡፡ በውህድ ፓርቲ ውስጥ ደሞ በእንጥልጥል ላይ ያሉትን የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች መመለስ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ የኦሕዴድ አመራር ሲያራምደው የከረመው ኢትዮጵያዊነትን በከፊል የማቀፍ አዝማሚያ ሕወሃትን የውህደት አጀንዳውን ባቋራጭ ለማቀላጠፍ አስቦ የሚያቀጣጥለው ስሜት ሊሆን እንደሚችል ሌላ ግምት መያዝ ይቻላል፡፡ ጉዳዩን በዝርዝር ለመመልከት ሞክረናል
ዋዜማ ራዲዮ- ወደ መጋቢቱ ጠቅላላ ጉባዔ እየተንደረደሩ ያሉት የግንባሩ ብሄራዊ ድርጅቶች ሰሞኑን በስራ አስፈጻሚ እና በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች በተጠመዱበት ሰዓት የገዥው ኢሕአዴግ ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ትናንት ወደ መድረክ ብቅ ብለው እንደዋዛ ስለ ኢሕአዴግ ወጥ እና ውህድ ፓርቲ የመሆን ጉዳይ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ሊቀመንበሩ የግንባሩን ወደ ውህድ ፓርቲ የመለወጥ ጉዳይ በጨረፍታ ጠቁመውት ያለፉት በአዲስ አበባ የኢሕአዴግ ወጣቶች ሊግ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ነበር፡፡ “የአዲስ አበባ የወጣት ሊግ አደረጃጀት ኢሕአዴግ ወደፊት ከግንባር ወደ አንድ ወጥ ድርጅት ለሚያደርገው ሽግግር ምሳሌ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ…” የሚል ዐረፍተ ነገር ነው የተጠቀሙት- አቶ ኃይለ ማርያም፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ያገኛሉ]
ጥልቅ ተሃድሶ ማስገኘት እንደቻለ የተነገረለት የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ከተጠናቀቀ ወዲህ አንድ ወጥ ውህድ ፓርቲ የመሆን ጉዳይ በአደባባይ ሲነገርለት ያሁኑ የመጀመሪያ ነው፡፡ ዋዜማ ያገኘቻቸው ምንጮችም የውህደት አጀንዳው በመጭው መጋቢት በሚደረገው የግንባሩ ጉባዔ እንደሚነሳ ጠቁመዋል፡፡ በርግጥ ፍንጩን ከሌላ ወገን በስተማማኝነት ማረጋጥ አልተቻለም፡፡
ሊቀመንበሩ ስለ ውህደት የተናገሩትን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በዜናው ሲጠቅሰው፣ የፓርቲው ልሳን እንደሆነ የሚነገርለት ፋና ብሮድካስት ግን በዜናው ጨርሶ አላነሳውም፡፡
አቶ ኃይለ ማርያም በተለይ ለህብረ ብሄራዊነት ልዩ ትኩረት ሰጥተው ነው የተናገሩት፡፡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ሊግ ህብረ ብሄራዊ አደራጃጀት ያለው መሆኑ ጠባብነት እና ትምክህት የሚያስከትሉትን አደጋ ለመለየት ልዩ ዕድል እንደሚፈጥርለት አጽንዖት ሰጥተው መናገራቸው በርግጥም በራሱ ልዩ ትርጉም ያለው ነው፡፡ በተለይ ደሞ የአዲስ አበባ ወጣት ሊግ ህብረ ብሄራዊ አደረጃጀት ለወደፊቱ የኢሕአዴግ ወጥ ፓርቲ አወቃቀር ምሳሌ እንደሚሆን ሲጠቁሙ ሞቅ ያለ ጭብጨባ ነው የተቸራቸው፡፡ እውነትም ሆነ ብለው አስበው የተናገሩት ከሆነ ገዥው ግንባር ወደ ህብረ ብሄራዊ ውህድ ፓርቲ ለመጓዝ መንገድ ለመጀመሩ ፍንጭ ሰጭ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡
በየክልሎች ያሉ የኢሕአዴግ ወጣት ሊጎች በብሄር የተደራጁ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ወጣት ሊጎች ግን ህብረ ብሄራዊ አደረጃጀት ያላቸው ናቸው፡፡ እናም የሊቀመንበሩ አነጋገር ከብሄር አደረጃጀት ይልቅ ባሁኑ ጊዜ ህብረ ብሄራዊነትን የሚያንጻባርቀው የአዲስ አበባ ሊግ አደራጃጀት ለኢሕአዴግ ተመራጭ መሆኑን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚጠቁም ነው፡፡
ሲንከባለል የቆየ አጀንዳ
ሊቀመንበሩ ኢሕአዴግ ወደ አንድ ወጥ ውህድ ድርጅት ለመሆን ራዕይ ሰንቆ የተመሰረተ ድርጅት መሆኑንም አክለው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይሄ አባባላቸው ግን በሁለት ምክንያቶች ሕጋዊ እና ፖለቲካዊ መሠረት ያለው ሆኖ አናገኘውም፡፡ ለዚህ ሁለት አብነቶችን መጥቀስ ይቻላል፤ ባንድ በኩል ኢሕአዴግ በፖለቲካ ታሪኩ የብሄር ማንነትን መሠረት ያደረገ የከፋፍለህ ግዛ አካሄድን በሙሉ ልቦና ሲከተል ኖረ እንጅ የህብረ ብሄራዊ ውህድ ፓርቲ አስፈላጊነትን በይፋ ሲሰብክ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡
በሌላ በኩል “ውህደትን እነ ራዕይ ሰንቆ የተመሰረተ ድርጅት…” የሚለው አባባል አቶ ኃይለ ማርያምን ትዝብት ላይ የሚጥል የሚሆነው ህብረ ብሄራዊ ውህደት በግንባሩ ሕገ ደንብ እንኳ እንደ መጨረሻ ግብ የተቀመጠ አለመሆኑን ስናይ ነው፡፡
ሊቀመንበሩ ባሁኑ ሰዓት እንደዚህ የተናገሩት ግንባሩን ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ የማሸጋገር ጉዳይ በሥራ አስፈጻሚው ስብሰባ ውይይት ስለተደረገበት ሊሆን እንደሚችል ግምት እንድንይዝ ያደርገናል፡፡ እንደዚያ ከሆነ ብሄራዊ ድርጅቶቹ ለሚቀጥለው መጋቢት ጉባዔ አቋም ይዘው እንዲቀርቡ ተነግሯቸዋል እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ሥራ አስፈጻሚው ታዲያ ለምን በይፋ መግለጫ ሳይሰጥበት ቀረ? ለሚለው ጥያቄ ግን ሁነኛ መልስ ማግኘት ያስቸግራል፡፡ ይህን የምንልበት ምክንያት ውህደትን ያህል ግዙፍ ጉዳይ አጥኝ ግብረ ሃይል እና ቁርጥ ያለ የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጦለት በመላ አባላቱ ሊብላላ የሚገባው ጉዳይ እንጅ በከፍተኛው አመራር ብቻ ውስጥ ለውስጥ የሚያልቅ ስላልሆነ እና መሆንም ስለማይገባው ነው፡፡
ምናልባት አቶ በረከት ስምዖን እና አባዱላ ገመዳ በሃላፊነታቸው የቀጠሉት ሕወሃት ይህንኑ የውህደት አጀንዳ ስለመጣ ሊሆን እንደሚችልም ግምት ማሳደር ይቻላል፡፡
ካሁን በፊት ባቀርብናቸው ዘገባዎች እንደጠቆምነው በግንባሩ ታሪክ የውህድ ፓርቲነት ጉዳይ አንድ ጊዜ ብቻ ነው በይፋ ትኩረት ተሰጥቶት እንቅስቃሴው ተጀምሮ የነበረው፡፡ የሰሞኑ ፍንጭ እውነት ከሆነ ግን ግንባሩ በተለይም ደሞ ሕወሃት አጀንዳውን የምር አድርገው እንዲይዙት የሚያስገድዱ ፖለቲካዊ እና ጸጥታ-ነክ ጉዳዮች አፍጥጠው መምጣታቸው አንድና ሁለት የለውም፡፡
ሥራ አስፈጻሚው በቅርቡ ባደረገው ስብሰባ እንኳ የኦሕዴድ እና ብአዴን በይነ-ድርጅታዊ መስተጋብር ለውህደት አንድ አወንታዊ ግብዓት ቢሆንም “መርህን ያልተከተለ ድርጅታዊ መሞዳሞድ…” በሚል አሸማቃቂ ሃረግ ነው ሲብጠለጠል የሰነበተው፡፡ ይህም ውህደት ቢፈጠር እንኳ ሕወሃት-መር የሆነ ውህደት እንጅ ሁሉም በእኩልነት የሚገባበት ሊሆን እንደማይችል ጠቁሞ ያለፈ ክስተት ነበር፡፡
ውህደት ለግንባሩ ምን ያተርፍላታል?
ዋናው ጥያቄ ኢሕአዴግ አጀንዳውን የሸፈነውን አቧራ አራግፎ አሁን ለምን አነሳው? የሚለው ነው፡፡ ሀገሪቱ የምትከተለው ብሄር-ተኮር ፌደራላዊ ሥርዓት ነው፡፡ ህብረ ብሄራዊ አደራጃጀት ደሞ በከፊልም ቢሆን ከዚህ አወቃቀር ጋር እንደሚቃረን ካሁን በፊት ባቀረብናቸው ሁለት ዘገባዎች ጭምር አንስተናል፡፡ ይህ ነባራዊ ሃቅ ነው እንግዲህ የውህደት ነገር በብሄር ማንነት ላይ ከተንጠለጠለው የግንባሩ ብሄር-ተኮር ድርጅታዊ ርዕዮተ ዐለም ለውጥ ይልቅ ሌላ ስውር ዐላማ ሊኖረው እንደሚችል ጥርጣሬ የሚፈጥረው፡፡
ገዥው ድርጅት እና የሚመራው መንግስት ታይቶ በማይታወቅ ውጥንቅጥ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ድሮ ኢትዮጵያዊያን ለአፋቸው ይጸየፉት የነበረው ብሄር ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭት አሁን ተደጋጋሚ ክስተት ሆኗል፡፡ የመንግሥት ባለስልጣናትም ቃሉን በይፋ ይጠቀሙታል፡፡ ግድያ፣ የንጹሃን ዜጎች መፈናቀል እና ንብረት መውደም እንዲሁ እየተደጋገሙ ነው፡፡
በሌላ በኩል በአባል ብሄራዊ ድርጅቶች መካከል መጠራጠር መስፈኑን አምኗል፡፡ ሥራ አስፈጻሚው እስረኞችን ለመልቀቅ በወሰነ ማግስት ጸጥታ ሃይሎች በተቃዋሚ ሕዝብ ላይ በሚወስዱት የሃይል ርምጃ ግጭትና ሞት በመቀጠሉ የመንግስትን የዲሞክራሲ ማስፋት እና ሀገራዊ መግባባት ተረኮች ዋጋ ቢስ እያደረጋቸው ነው፡፡
በግንባሩ አባላት መካከል ሰፍኖ እንደቆየ የተነገረለት የርስበር መጠራጠር ቀስ በቀስ ወደ ሃይል መፈታተሸ እያደገ ይመስላል፡፡ ውስጠዊ ችግሮች አጎንቁለው ወጥተዋል፡፡ ይሄ ውስጣዊ ሁኔታ ደሞ ከውህደት አጀንዳ ጋር እንደሚቃረን ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም ድርጅቶቹን ለርስበርስ አለመተማመን የዳረጓቸው መሰረታዊ ችግሮች ሳይፈቱ በጥድፊያ እውነተኛ ውህደት መፈጸም የመቻሉ ነገር አጠራጣሪ ነውና፡፡ የድርጅቶቹ አንጻራዊ ጥንካሬ እና ነጻነት በይፋ ወደ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት ቢሞከር ኖሮ እንኳ ብዙም ጥያቄ ሳይነሳበት ሊፈጸም ይችል እንደነበር መናገር ይቻላል፡፡ ያ ዕድል ግን አሁን ከሞላ ጎደል ያለፈ ይመስላል፡፡
ከዚህ አንጻር ውህደት ለምን አሁን? ለሚለው ጥያቄ አንዱ መላ ምት ብሄራዊ አባል ድርጅቶቹ በግንባርነት የነበራቸው ጉዞ በበቂ ሁኔታ ስለዳበረ ሊዋሃዱ የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል የሚለው ነው፡፡ ዳሩ በይነ-ድርጅታዊ መስተጋብሩ ገና ብቅ ብቅ ማለት ጀመረ እንጅ ከመዳበር ደረጃ ላይ ጨርሶ ያልደረሰ መሆኑን ስናስብ መላ ምቱ ብዙም ውሃ የማይቋጥር ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ይልቁንስ ከፖለቲካዊ ቀውስ ለመውጣት እና በህብረ ብሄራዊነት ሽፋን የስልጣን እድሜን ለማራዘም የተቀየሰ አጀንዳ ነው የሚለው መላ ምት ሚዛን ይደፋል፡፡
በተለይ ሕወሃት በሥልጣን እና ሃብት ክፍፍል ላይ ተገዳዳሪ አባል ድርጅቶች ስለበዙበት በሌላ ዘዴ በሥልጣን ላይ የመቆየት ዕድሉን ለማስፋት የቀየሰው አዲስ ስልት ሊሆን እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ክልላዊ መሰረት ያለቸው ብሄራዊ ድርጅቶች በተለይም ኦሕዴድ መነቃቃት እየጀመሩ ነው፡፡ እናም ብአዴንም ተመሳሳይ ቁመና ከመያዙ በፊት ሕወሃት በትንሽ መስዕዋትነት አጠቃላይ የበላይነቱ ሳይሸረሸር ወደ ውህደት ቢገባ ይጠቀም እንደሆነ እንጅ አይጎዳም፡፡ በዚህም አለ በዚያ ባሁኑ ወቅት የሚፈጸም ውህደት በምንም መልኩ ከሕወሃት የእጅ አዙር የበላይነት ሊያመልጥ አይችልም፡፡ የሆነው ሆኖ ውህደት አሁን የተቀጣጠለውን ሕዝባዊ ቁጣ አብርዶ ሀገሪቱንም ሆነ ድርጅቱን ከሁለንተናዊ ቀውስ ይታደጋቸዋል ወይ? የሚለው ጉዳይ አጠራጣሪ ቢሆንም በዋናነት ግን ወደፊት ቢታይ የሚሻል ነው የሚሆነው፡፡
ኦህዴድ የውህደት አጀንዳውን አንፃራዊ ነፃነቱን ለመንጠቅ እንደተዘጋጀ ወጥመድ ያየዋል
የውህደት አጀንዳው በተለይ በኦሕዴድ ላይ ውልውል መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ኦሕዴድ ባሁኑ ቁመናው በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኦሮሞን ህዝብ ልብ ለማግኘት የቻለበት ወቅት ላይ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ አዲሱ አመራር ሕዝባዊ ቅቡልነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገና ማጣጣም የጀመረበት ወቅት ነው፡፡ እናም ኦሕዴድ ጥያቄዎችን ማንሳቱ ይቀርም፡፡ በህብረ ብሄራዊ ውህደት ስም የብሄር ተወካይነቴን ብገፈፍ ምን አተርፋለሁ? እንደ ኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግሬስ ያሉ ተቃዋሚ ድርጅቶችስ ክፍተቱን ተጠቅመው የኦሮሞ ብሄርተኝነትን በማቀጣጠል ሕዝባዊ ድጋፌን አይወስዱትም ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች ደሞ ዋና ዋናዎቹ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የኦሮሞ ብሄርተኝነት እንደሆነ ገና መንታ መንገድ ላይ ነው፡፡ የእነ አቶ ለማ መገርሳ መስመር በኦሮሞ ህዝብ ቁልፍ ሚና ተጫዋችነት የኢትዮጵያዊነትን አጀንዳ ማራገብ መያዝ አንዱ መንገድ ነው፡፡ አሊያም አግላይ የሆነውና መገንጠልን የሚያካትተው መስመርን መከተል ነው፡፡
እናም የኦሕዴድ አመራር በኦሮሞ ህዝብ መሪነት ኢትዮጵያዊ ህብረ ብሄራዊነትን ገና ሳያጠናክር ወደ ውህደት ቢገባ አጀንዳውን እንደተነጠቀ ሊያስብ ይችላል፡፡ በውህድ ፓርቲ ውስጥ ደሞ በእንጥልጥል ላይ ያሉትን የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄዎች መመለስ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
ኦሕዴድ በርግጥም አቋም ይዞ የሚሟገት ከሆነ ሕወሃት በውህድ ፓርቲው ውስጥ አንዳንድ ቁልፍ ስልጣኖችን ለኦሕዴድ ከመስጠት ወደ ኋላ የሚል አይመስልም፡፡ ይሄ ስሌት ካለ በመጋቢቱ ድርጅታዊ ጉባዔ ግልጽ ይሆን ይሆናል፡፡
የኦህዴድ የኢትዮጵያዊነት ትርክት ሌላ ገፅ
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አዲሱ የኦሕዴድ አመራር ሲያራምደው የከረመው ኢትዮጵያዊነትን በከፊል የማቀፍ አዝማሚያ ሕወሃትን የውህደት አጀንዳውን ባቋራጭ ለማቀላጠፍ አስቦ የሚያቀጣጥለው ስሜት ሊሆን እንደሚችል ሌላ ግምት መያዝ ይቻላል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የመንግሥት ጸጥታ እና ድርጅታዊ መዋቅሩን በበላይነት የሚቆጣጠረው ሕወሃት የኦሕዴድን አንዳንድ ትርክቶች እና ርምጃዎች ሆነ ብሎ እያለፋቸው እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይሆንም፡፡
በአጋር ድርጅቶች ከሚመሩት አፋር፣ ቤንሻንጉል፣ ጋምቤላ እና ሐረሬ ክልሎች ጋር ሲነጻጸር በብሄር ፖለቲካ ተዋስዖም ሆነ በብሄር ተኮር ግጭት ዐይነተኛ ሚና እየተጫወተ ያለው የሱማሌ ክልሉ ሶህዴፓ ብቻ ነው፡፡ ሶሕዴፓ ከዐመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ያሳየው ፖለቲካዊ መነቃቃት የደቡቡ ደኢሕዴን ካሳየው እንቅስቃሴ የሚልቅ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ከአናሳ ክልሎች ጋር ይቅርና ከአራቱ ትላልቅ ክልሎች ጋር ሲነጻጸር ጠንካራ እና ድንበር ተሻጋሪ ልዩ ፖሊስ ያለው ሱማሌ ክልል ነው፡፡ ያም ሆኖ ሶሕዴፓ በቁጥር ከሕወሃት ጋር የሚቀራረብ አንድ ብሄር ቢወክልም የገዥው ግንባር አባል ግን አልሆነም፡፡ ኢሕአዴግ የአባልነት ጥያቄ አላቀረበለትም፤ ሶሕዴፓም አባል ለመሆን ስለመጠየቁ አንዳችም መረጃ የለም፡፡
በግንባሩ ማዕከላዊ አመራር እና በመከላከያ ሠራዊቱ ተጽዕኖ በሂደት አለዘቡት እንጂ ኦሕዴድ እና ሶህዴፓ በከባድ ርስበርስ መወነጃጀል እና ግጭት ውስጥ ከገቡ ቆይተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ወደ ውህድ ፓርቲ ቢቀየር እንኳ ሶሕዴፓ ድርጅታዊ ማንነቱን ይዞ ስለሚቀጥል ሁኔታው በኦሕዴድ ላይ ስጋት መፍጠሩ አይቀርም፡፡
ከዚህ አንጻር ስናየው ሶሕዴፓ ወደፊትም በተለይ ለሕወሃት እና በምስራቁ ግንባር ላሉ የጸጥታ ሃይሎች የብሄር ፖለቲካ መጫዎቻ ካርድ እና ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ሶህዴፓ ከኦሕዴድ ጋር ባለው ግንኙነት ሲጠቀማቸው የነበሩት ከረር ያሉ መግለጫዎች እና ክልሉ ጸጥታ ሃይሎች ላደረሱት ከፍጠኛ የሕዝብ መፈናቀል እና ግድያ በሕግ ሲጠየቁ አለመታየቱ ይህንኑ ያጠናክራል፡፡ ወደፊትም ቢሆን ሕወሃት ሥልጣኑ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባበት ከጀርባ ሆኖ የሱማሌ ክልል የመገንጠል ጥያቄን እንዲያነሳ በመገፋፋት የአንድነት ሃይሎችን ለማስፈራራት ወይም የኢትዮጵያ አንድት ጠበቃ ሆኖ ለመታየት ሊጠቀምበት ያስብ ይሆናል፡፡
ይህነን ሁሉ ካልን በኋላ ግን አቶ ኃይለ ማርያም የጨረፍታ ያነሱት የውህደት አጀንዳ የራሳቸው ይሁን ወይንስ ድርጅቱ እንዲታወቅ ስለፈለገ ያነሱት ስለመሆኑ በርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል፡፡ ሊቀመንበሩ ሆነ ብለው ፍንጭ ለመስጠት የተናገሩት ከሆነ ግን ውህደቱ በቅርቡ መሳካት አለመሳካቱን ለማወቅ ብሄራዊ አባል ድርጅቶቹ አሁን የያዙትን ስብሰባ እስኪያጠናቅቁመጠበቅ ግድ ይላል፡፡ ግንባሩ በሚስጢር ሊያቆየው ከፈለገ ደሞ እስከ መጋቢቱ ጉባዔ ድረስ መጠበቅ ግዴት ይሆናል፡፡[ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ያገኛሉ]
https://youtu.be/ACl4yOaoHKA