ዋዜማ ራዲዮ- በኦሮሚያ ከተሞች አዲስ የተጀመረው የኦሮሚያ አድማ ተከትሎ በርካታ የጭነት መኪኖች ሥራ ፈተው መዋላቸውን ዘጋቢዎቻችን በአካል ተገኝተው ተመልክተዋል፡፡ በመርካቶ ሲኒማ ራስ፣ ሸቀጥ ተራ፣ ጎማ ተራ፣ ሳህን ተራ፣ ቦንብ ተራና በተለይም ደግሞ ከ7ኛ አንስቶ እስከ ምዕራብ ሆቴል ተደርድረው የሚቆሙ ዕቃ ጫኝ ተሸከርካሪዎች፣ አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው በአመዛኙ ሥራ ፈተው ውለዋል፡፡
በጎጃም በረንዳ አካባቢ የችቡድ ንግድ ላይ የተሠማሩ ግለሰብ ለዋዜማ ዘጋቢ እንደነገሯት ‹‹የክፍለ አገር ደንበኞቼ በጠዋት ደውለው ዕቃቸው እንዳይጫን አስጠንቅቀውኛል፡፡ ችግር መኖሩን ያወቅኩትም ያኔ ነው›› ብለዋል፡፡ በተለምዶ ደንበኞች በባንክ ብር ካስተላለፉ በኋላ ሻጮች ዕቃቸውን በመኪና ጭነው ይልኩላቸዋል፡፡ ግብይቱ የሚካሄደውም ጋዥ፣ ሻጭና ዕቃ ጫኞች መሐል በሚፈጠር መተማመን ነው፡፡
‹‹ዕቃ ጭነው ለመውጣት የሞከሩ ነበሩ፤ ባሉካዎች (ባለቤቶች) ደውለው አስመልሰዋቸዋል›› ሲል ለዘጋቢያችን የነገራት ከአሜሪካን ግቢ ወደ ትግራይ ዕቃ በመጫን የሚተዳደር ግለሰብ ነው፡፡
የዋዜማ ዘጋቢ በመርካቶ ሸቀጥ ተራ፣ ቦንብ ተራና፣ ጆንያ ተራ ካባቢው ተዘዋውራ ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች ገበያው ድንገት በአንድ ጊዜ መቋረጡ አስደንግጧቸዋል፡፡ ‹‹ዛሬ ነው እኔ የሰማሁት፡፡ ኦሮሚያ ረብሸዋል ያለኝ ታናሽ ወንድሜ ነው›› ትላለች በደብተር ንግድ ላይ የተሰማራች ወጣት፡፡ ብዙዎቹ በተመሳሳይ ሁኔታ ስለ አመጹ የሰሙት ዘግይተው ነው፡፡
‹‹ግብር መቀነስ አለበት፤ ግን ይሄ ነገር ለተራዘመ ጊዜ የሚቆይ ከሆነ ለኛ አስቸጋሪ ነው፡፡ በቀን በቀን የምንጥለው እቁብ አለብን፡፡ ከውጭ የምናስመጣቸው ዕቃዎች በብዛት በዱቤ የሚገዙ ናቸው፡፡ ለአስመጪዎች ቀን በቀን እዳ ማቃለል አለብን፡፡ ያን የምናደርገው ሁልጊዜ ከቀን ሽያጫችን እየቀነስን ነው፡፡ አሁን እንደሚወራው ለሳምንት ሥራ ይቆማል ማለት ለኛ በጣም በጣም አስቸጋሪ ነው›› ሲሉ የተናገሩ በካልሲ ጅምላና ችርቻሮ ንግድ የተሰማሩ ግለሰብ ናቸው፡፡
በመረጃ እጦት ለሊቱን ዕቃ ጭነው በጠዋት ወደ ክፍለ ሐገር ጉዞ የጀመሩ አይሱዙ የጭነት መኪኖች ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው ከአለምገና ጉዟቸውን አቋርጠው መመለሳቸውንም ለመረዳት ችለናል፡፡
በአለምገና ነዋሪ የሆኑ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት የትራንስፖርት ችግር እንደተፈጠረባቸውም ተሰምቷል፡፡ ‹‹ጠዋት አካባቢ ከኬንቴሪ ጀሞ ታክሲ ለማግኘት ያለወትሮ ረዥም ሰልፍ ነበር፡፡ ችግር እንዳለ የገባኝ ግን ከተማ ከደረስኩ በኋላ ነው፡፡›› ብሏታል አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለዘጋቢያችን፡፡ ሆኖም አካባቢው ባልተለመደ ሁኔታ ጭር ብሎ መዋሉን፣ ሱቆች በአመዛኙ መዘጋታቸውን፣ የፖሊስ ኃይል ከፍ ባለ ቁጥር መሠማራቱን የኬንቴሪ ነዋሪዎች በስልክ ነግረውናል፡፡ በርካታ ሰዎች ከቤት ለመውጣት ስጋት ያደረባቸው ሲሆን አካባቢው ግን ከሞላ ጎደል ሰላማዊ እንደበር በስልክ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ጨምረው ገልጸውልናል፡፡
ከአዲስ አበባ ውጪ አድማው በሚደረግባቸው ከተሞች በአመዛኙ የክልሉ ፖሊስ መሰማራቱን ከተለያዩ አካባቢዎች የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የመከላከያ ሰራዊት አባላትን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ተለያየ አቅጣጫ ሲንቀሳቀሱ የታዘቡ የአይን እማኞች ሌሊቱን ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሊሰማሩ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ነግረውናል።
በመንግስት በኩል ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰአት የተባለ ነገር የለም።