ዋዜማ- በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ለኢትዮጵያዊያን የሚሠጠውን ቪዛ የቆይታ ጊዜ ወደ ሦስት ወር ማሳጠሩን ሐምሌ 2፣ 2017 ዓ፣ም በይፋዊ ገጹ ባሠራጨው መረጃ አስታውቋል።

ኢምባሲው፣ የኢትዮጵያዊያን ተጓዦች የቪዛ ቆይታ ጊዜ ያጠረው፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስደተኛ ባልሆኑ የቪዛ አመልካቾች ላይ ባደረገው የፖሊሲ ለውጥ ምክንያት መሆኑን ገልጧል።

አዲስ በወጣው የመስሪያ ቤቱ ፖሊሲ መሠረት፤ ከሐምሌ 1፣ 2017 ዓ፣ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ለኢትዮጵዊያን የሚሰጠው ቪዛ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግልና ቆይታውም ለሦስት ወር ብቻ እንደሚሆን ተገልጧል። ከሐምሌ 1፣ 2017 ዓ፣ም በፊት ለኢትዮጵያዊያን ተጓዦች የተሰጡ ቪዛዎች ግን ባሉበት ይቀጥላሉ ተብሏል።

ቪዛ “B1” እና ቪዛ “B2” በሚባለው ምድብ ውስጥ የሚገኙ ለንግድ ሥራ እና ለጉብኝት ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ኢትዮጵያዊያን ተጓዦች እስከ ፖሊሲ ለውጡ ድረስ በነበረው አሠራር የሚያገኙት ቪዛ የሁለት ዓመታት የቆይታ ጊዜ የነበረው ሲሆን፣ ተጓዦችም የሁለት ዓመት ገደቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በተደጋጋሚ ከአገሪቱ እየወጡ ተመልሰው እንዲገቡ የሚያስችል መብት ያጎናጸፈ ነበር።

ከሐምሌ 1/ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የቪዛ ፖሊሲ ግን፣ ኢትዮጵያዊያን ባንድ ቪዛ በተደጋጋሚ ወደ አሜሪካ መግባት እንዳይችሉ ይከለክላል። ይህም ማለት አንድ ቪዛ ያለው ተጓዥ፣ የቪዛ የሚያገኙ ተጓዦች የቆይታ ጊዜ ባይጠናቀቅም እንኳ ከአሜሪካ ከወጡ በኋላ በዚያው ቪዛ ተመልሰው መግባት አይችሉም።

በቪዛ ፖሊሲ ለውጡ ምክንያት፣ በአሜሪካ ጉብኝት ለማድረግ፣ ለትምህርት እና ለሥራ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ መንገደኞች ሊያገኙ የሚችሉት ቪዛ የሦስት ወር ዕድሜ ብቻ ያለው እና አንድ ጊዜ ብቻ ገብቶ መውጣት የሚያስችል ይሆናል።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ፣ ስደተኛ ያልሆኑና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አሜሪካ የሚገቡ ናይጀሪያዊያን እና ጋናዊያን በተመሳሳይ ማግኘት የሚችሉት ቪዛ የሦስት ወር ቆይታ ብቻ ያለው እና ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚያገለግል እንደሚሆን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታውቋል።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር፣ ኤርትራን፣ ሱዳንን እና ሱማሊያን ጨምሮ ለአሜሪካ ብሄራዊ ደኅንነት ስጋት ናቸው ባላቸው የ12 አገራት ዜጎች ላይ ባለፈው ግንቦት መገባደጃ ላይ መሉ የጉዞ እገዳ መጣሉ አይዘነጋም። [ዋዜማ]