አንድ የዋዜማ ዓመት
ዋዜማ ሬዲዮ ከተጀመረች እንደዋዛ አንድ ዓመት ተቆጠረ።
ካልጠፋ ስም ዋዜማ ማለትን ምን አመጣው፧ ዋዜማነቱስ ለምንድን ነው፧
ለወትሮውም ቢሆን አጥብቆ ተመራማሪ፣ አለዚያም ታሪክ ጸሐፊ ከዋዜማው በፊት ምን ነበር፣ በዋዜማውስ ምን ሆነ፣ ከዚያስ የዕለቱለት ምን ሆነ፧ በማግስቱስ፧ እያለ ከገጽ ገጽ ይዘልቃል።
ዋዜማ ሬዲዮ የበቀለችው ጭቆና ሥር እየሰደደ፣ የፍትሕ ድምጿ እየሰለለ፣ እብሪት በገነነበት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ምህዳር ውስጥ ነው። የዋዜማችን ዋዜማ ይህ አምባገነንነት በፈጠረው በተስፋና በቀቢጸ ተስፋ መካከል የመወጠር ስሜት የተሞላ ነበር። ሁኔታውን ለመለወጥ ምንም አስተዋጽኦ ማድረግ አንችልም ማለት ነው፧ የሚል የቀላል ከባድ፣ የነጠላ ውስብስብ ጥያቄ የተጋፈጥንበት ዛሬ ነበር፣ ነውም።
ከአገር መውጣት እንጂ፣ አገርን ከልብ ማውጣት አይቻልምና “አንቺ አገር እንዴት ነሽ፧” ብሎ ለመጠየቅም ቢሆን ባዶ እጅ መቅረቡ ያሳፍር የለ፧ በራሳችን ውስን አቅም፣ በትንሹ የምንጀምረው ለራስ የመታመን እዳ በራሳችን ላይ ለመጣል ተስማማን። የግልና የቡድን አቅማችን እስከፈቀደ ብቻ የመራመድ፣ በራስ ላይ የተጣለ ለራስ የመታመን እዳ። የሰሎሞን ዴሬሳን ምሳሌ አሻሽለን እንዋስና፣ ከዚህ እዳ የሚተርፈው እየወደቁ እየተነሱ እንደሚለማመዱት ብስክሌት ግልቢያ ነው። መውደቅ፣ መድከም ሊኖር ይችላል፤ ሚዛን ጠብቆ፣ ወደፈለጉበት አቅጣጫ መጓዝ ከተቻለ ግን ቀሪው ብዙ አያሳስብም።
የዋዜማ አንድ ዓመት ለአዘጋጆቹ የትምህርት፣ የሙከራ፣ እና የተስፋ ጊዜ ሆኖ አልፏል።
ዝግጅታችንን ከጀመርን አንስቶ ብዙዎች ደግፈውናል፣ በብዙ መንገድ። በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የምትገኙ አድማጮቻችን ሙከራችን የተገባ እንደሆነ የምታስታውሱን ናችሁ። በተለያየ መንገድ በዝግጅቶቻችን የምትሳተፉ ወዳጆቻችን ተባባሪዎቻችን ሳትሆኑ የሙከራው ባለቤቶች ናችሁ። ሁላችሁንም እናመሰግናለን።
አንደኛውን ዓመት የዘጋነው ሁለተኛውን ካለፈው የተሻለ እንዲሆን በመወሰን ነው። እነሆም አዳዲስ ዝግጅቶችን በዋዜማ ታገኛላችሁ። ዝግጅቶቻችን በጥራታቸውም ሆነ በዓይነታቸው የተሻሉ እንዲሆኑ እንጥራለን። ከአገር ቤትም ከውጭም የሚመጡት ዝግጅቶች ለዋዜማ ተጨማሪ ቀለማት ይሆናሉ።
ቁልፉ ነገር ከዋዜማ ጋራ የምታሳልፉት ጊዜ የሚያስቆጭ አለመሆኑ ነው።
መልካም ዋዜማ የጥሩ ነገ ዜና አብሳሪ ነው፥፥
መስፍን ነጋሽ