በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ አቃቤ ህግ በእነ እስክንድር ነጋ ጉዳይ ምስክሮች በዝግ ችሎትና ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው ይሰሙልኝ በማለት ያቀረበው አቤቱታ ከፍታኛ ተቃውሞ እና ክርክር አስነስቷል፡፡ የዋዜማ ሪፖርተር ጉዳዩን ተከታትላዋለች
ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ብሄርና ሀይማኖትን መሰረት ያደረገ ገጭት እንዲፈጠር በማነሳሳትና መንግስትን በማዳከም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስልጣንን በሀይል ለመያዝ እንዲሁም የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኦሮሞ እና በትግራይ ተወላጆች ላይ እንዲሁም በእስልምና ምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ትዕዛዝ ሰጥተዋል ባላቸው 7 ግለሰቦች ላይ የሽብር ወንጀል ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
በዚህ የክስ መዝገብ ላይ የተካተቱት እና በማረሚያ ቤት የሚገኙት አቶ እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌ ሲሆኑ ጌትነት በቀለ ደግሞ የዋስትና መብቱ ተከብሮ ጉዳዩን በውጭ እየተከራከረ ይገኛል፡፡ ቀሪ 2 ተከሳሾች ደግሞ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር አልዋሉም ፡፡
ይህን መዝገብ ለመመልከት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ በህገመንግስት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እና የፀረሽብር ወንጀል ችሎት ዛሬ ጥቅምት 12ቀን 2013 ዓም ረፋድ ላይ ተሰይሟል፡፡
በዛሬው ችሎት አቃቤ ህግ በዚህ መዝገገብ ላይ የሚቀርቡ ምስክሮች በዝግ ችሎትና ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆነው ይሰሙልኝ በማለት ያቀረበው አቤቱታ ከፍታኛ ተቃውሞ እና ክርክር አስነስቷል፡፡
“የተፈፀመው ወንጀል ሀይማኖት እና ብሄርን መሰረት ያደረገ እና ለሀገር ደህንነት አደጋ የሆነ የሽብር ወንጀል ነው” ያለው አቃቤ ህግ “ምስክሮቹ ከተከሳሾች ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ለጥቃት ይጋለጣሉ እንዲሁም በቀዳሚ ምርምራ ምስክር ማሰማት ሂደት ላይ የግድያ ዛቻ እንደደረሰባቸው የገለፁልን ምስክሮች በመኖራቸው በአዋጅ ቁጥር 699/2003 መሰረት ለምስክሮቻችን ጥበቃ ይደረግላቸው” በማለት አቤቱታ አቅርቧል፡፡
“ይህ የተከሳሾችን ፍትህ የማግኘት መብት አያጠብም” ያለው አቃቤ ህጉ እንዲሁ “እናቅርብ ቢባል እንኳ ምስክሮቻችን ጥበቃ ካልተደረገላቸው ቀርበው ለመመስከር ፍቃደኛ አይሆኑም” በማለት ተናግሯል፡፡
ተከሳሾች እና እና ጠበቆቻቸውም በዚህ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ አንስተዋል፡፡
ሰፊ ዝርዝር የያዘ ተቃውሞ በችሎት ያሰማው 1ኛ ተከሳሽ ሆኖ የቀረበው አቶ እስክንድር በበኩሉ በቀይ ሽብር ወንጀል ተከሰው የነበሩ ተከሳሾችን እንደ አብነት በማንሳት ተቃውሞውን ጀምሯል፡፡
“በቀይሽብር ወንጀል በተከሰሱት ተከሳሾች እንኳን ምስክር ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሆን አልተጠየቀም ነበር፤ እነዛ ተከሳሾች የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ ከመሰከረባቸው ማህበረሰብ ጋር ተቀላቅለው ነው ኑሯቸውን የቀጠሉት ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ምስክሮችን የመበቀል ባህል እንደሌለ ማሳያ ነው” ብሏል፡፡
አቶ እስክንድር አክሎም ይህ ክስ የተመሰረተ እለት አቃቤ ህግ ሙሉ ሂደቱን በግልፅ ችሎት ነው መደረግ ያለበት ማለቱን በማስታወስ ችሎቱ ምስክር ማስማት ሂደቱ በግልፅ ችሎት እንዲያደርግ ጠይቋል ፡፡
ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ የመገናኛ ብዙሃን የምስክሮችን ዝርዝር ቃል እዳየይገልፁ የተጣለው ገደብ ተነስቶላቸው ሂደቱን ሙሉ ለሙሉ በድምፅ መከታተል እንዲችሉ እንዲፈቀድ አማራጭ ሀሳቡን አቅርቧል፡፡
“የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ህገመንግስቱ ተከሳሾች ምስክሮቻቸውን የማየት መብት እንዳለቸው እየደነገገ በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ ማድረጉ ይጣረሳል” በማለት ተቃውሞ ያቀረቡት ደግሞ 3ኛ ተከሳሽ የሆኑት ወይዘሮ ቀለብ ናቸው፡፡
ወ/ሮ ቀለብ አክለውም “ለአቃቤ ህግ ይሄ የሚፈቀድ ከሆነ መከላከል ደረጃ ላይ ስደርስ እኔም የመከላከያ ምስክሮቼን ከመጋረጃ ጀርባ እንዳሰማ ይፈቀድልኛል ወይ?” ሲሉ ችሎቱን ጠይቀዋል፡፡
ከአንደኛ እስከ አራተኛ ላሉት ተከሳሾች ወክለው የቀረቡት ጠበቆች በበኩላቸው ተከሳሾቹ በተነናገሩት የተቃውሞ ሀሳብ ላይ ሞያዊ ድጋፋቸውን እንዲህ ሲሉ አቅርበዋል፡-
“አቃቤ ህግ በአቤቱታው ምስክሮቼ ከተከሳሾቹ ጋር ስለሚተዋወቁ ሲል ገልጿል የሚተዋወቁ ከሆነ ደግሞ ከመጋረጃ ጀርባ ማድረጉ ምን ፋይዳ አለው? ከዚህ በተቃራኒው እንደውም የመስቀለኛ ጥያቄ ስናቀርብ እኛን የሚጎዳን ነገር ነው ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አቃቤ ህግ ምስክሮቹ የግድያ ዛቻ ደረሰብን አሉ ብሎ ተናገረ እንጂ ዛቻ እንደደረሰባቸው የሚያሳይ ማስረጃ በችሎት ካቀረበው አቤቱታ ጋር አላያያዘም ይሄ ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡ በምስክር ጥበቃ አዋጁ ውስጥ የተዘረዘሩ 20 አይነት የምስክር ጥበቃዎች ቢኖሩም ከእነዛ ውስጥ ከባዱን መምረጡ ሆን ተብሎ እና የፍትህ ስርዓቱን አዳጋች ለማድረግ ነው” ብለዋል፡፡
በዋስትና ጉዳዩን ከውጭ ሆኖ የሚከራከረውን 5ኛ ተከሳሽን ወክለው የቀረቡት ጠበቆች በበኩላቸው ደግሞ ባቀረቡት የተቃውሞ ሀሳብ
“የምስክር ጥበቃ አዋጁ ላይ አንቀፅ 6 ንዑስ አንቀፅ 3 ላይ በተቀመጠው መሰረት የምስክር ጥበቃ እንዲደረግለት ከፈለገ ምስክሩ እራሱ ማመልከቻ ማቅረብ ይኖርበታል ያን ማድረግ የማይችል ከሆነ ፖሊስ ወይም አቃቤ ህግ ያቀርበለታል ነው የሚለው ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ምስክሮቹ ማልከቻ ማቅረብ ስላለመቻላቸው የቀረበም ሆነ የተያያዘ ነገር የለም፡፡” ብለዋል
አክለውም “ለመስቀለኛ ጥያቄ እንዲረዳ ምስክሩ አካላዊ ብቃቱ ምን ሁኔታ ላይ ነው የሚለውን ተከሳሾችም ሆነ ጠበቆች ማረጋጋጥ መብት አላቸው ለእነሱ ብቻ ሳይሆን በችሎቱም ያ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያክል እንዲህ ሲያደርጉ አይቻለው ብሎ ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ የሚመሰክረው ምስክር እውነትም ማየት ይችላል ወይ የሚለውን ማረጋገጥ መቻል አለብን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ የመስቀለኛ ጥያቄ ሲደረግ መስካሪው በሚናገርበት ወቅት የሚያደርጋቸውን አካለዊ እንቅስቃሴዎችንም መሰረት ተደርጎ ነው:: የአፍ ፣ የእጅ እና የእግር እንቅስቃሴ መስካሪው እየዋሸ ነው ወይ የሚለውን ለመመለየት እና መስቀለኛ ጥያቄዎችን ለማቅረብ ይረዳናል ፡፡ ይህም ሁሉ እንዳለ ሆኖ ደግሞ መስካሪው ከዚህ በፊት በሀሰተኛ ምስክርነት ወንጀል እንደሌለበት ልናረጋግጥ ይገባል፣ ከመጋረጃ ጀርባ ወረቀት እያነነበበ እንደማይመሰክር ምን ማረጋገጫ አለን ፍርድ ቤቱን ብናምነውም ከጀርባ የሚሰራው ስራ ግን አመኔታው ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችል ነው ፡፡” በማለት ከፍተኛ ተቃውሞ አንስተዋል፡፡
አቃቤ ህግ ለቀረበው ተቃውሞ የመልስ መልስ ለመስጠጥ እድል እንዲሰጠው ችሎቱን ቢጠይቅም ችሎቱ ግን አቤቱታችሁን በዝርዝር ማቅረብ ትችሉ ነበር አሁን የመልስ መልስ ለመስጠት እድል አንሰጥም በማለት ከልክሏል፡፡
በዛሬው ዕለት በተጨማሪም በቀረበባቸው ክስ ላይ ከ1-4 ያሉት ተከሳሾች ከዚህ ቀደም ባቀረቡት የመጀመርያ ደረጃ የክስ መቃወምያ ላይ አቃቤ ህግ በጸሁፍ ምላሽኑ ለችሎት አስገበቷል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ሲያደምጥ የቆየው ችሎቱ በስተመጨረሻም ትዕዛዞቹን አስተላልፏል፡፡
በዚህም ፖሊስ 6ኛ እና 7ኛ ተከሰሾችን ፈልጎ ያላቀረበበትን ወይንም የደረሰበትን ደረጃ ያላሳወቀበት ምክኒያት የፖሊስ ሀላፊው ቀርበው በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያብራሩ እንዲሁም ዛሬ በተደረገው ክርክር እና በመቃወምያውን መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለህዳር 29 ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ ለምርጫ መዘጋጀት ስላለብን የቀጠሮ ቀን አይራዘምብን በማለት ጥያቄ ቢያቀርቡም ችሎቱ ትዕዛዙን አፅንቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]