ዋዜማ ራዲዮ- አራጣ በማበደር ወንጀል ከአቶ አየለ ደበላ (አይ ኤም ኤፍ) እና ከአቶ ገብረኪዳን በየነ (ሞሮኮ) ጋር ክስ ተመስርቶባቸው ላለፉት ስምንት ዓመታት ወህኒ እንደነበሩ የተገለጸው አቶ ከበደ ተሠራ (ዎርልድ ባንክ) ከሰሞኑ ከእስር ተለቀው በአዲስ አበባ አንዳንድ ቦታዎች ሲንቀሳቀሱ ታይተዋል ፡፡
ግለሰቡ ምናልባት በአሞክሮ አልያም በምህረት ከእስር ሳይፈቱ እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡ ታማኝ የዋዜማ ምንጮች ግለሰቡን በምህረት ለማስፈታት በአንዳንድ የመንግሥት የቅርብ ሰዎች ሙከራ ተጀምሮ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ሰለጉዳዩ ዝርዝር የአቶ ከበደን ቤተሰብ ለማነጋገር ዋዜማ ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም።
አቶ ከበደ ተሠራ አራት ኪሎ ከቱሪስት ሆቴል ጎን በ2900 ካሬ ላይ ያረፈ ባለ ዘጠኝ ፎቅ ህንጻ አስገንብተው የማጠናቀቂያ ሥራዎችን በመስራት ላይ ሳሉ ነበር ከስምንት አመታት በፊት ለእስር የተዳረጉት፡፡ ያስገነቡት የነበረው ህንጻም በሕገወጥ ንግድ የተገኘ ነው በሚል እንዲወረስ የስር ፍርድ ቤት አዞ ነበር፡፡ ኾኖም ህንጻውን የገነባው ማገርኮን ኮንስትራክሽን፣ ለህንጻው ግንባታ 55 ሚሊዮን ብር በብደር መልክ ሰጥቶ የነበረው ንብ ኢንተርናሽናል ባንክና ተከሳሹ ግብር አጭበርብረውኛል የሚለው ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በሕንጻው ላይ የይገባኛል ጥያቄ በማንሳታቸው ላለፉት 8 ዓመታት በፍርድ ቤት ክርክር ሲያካሄዱ ቆይቷል፡፡
በመጨረሻም ጉዳይ ሰበር በመድረሱ ሕንጻው በሐራጅ ተሸጦ ንብ ባንክ ያበደረው 55 ሚሊዮን ብር ከነወለዱ እንዲከፈለው ዉሳኔ በመተላለፉ ባለፈው ሳምንት አርብ በፍርድ አፈጻጸም ግቢ ይኸው ተፈጽሟል፡፡ ንብ ባንክ በጨረታው እንዲሳተፍ ፍርድ ቤት ስለፈቀደለትም ለንብረቱ እጅግ የተጋነነ የተባለ ዋጋ በማቅረብ ከአቢሲኒያ ባንክ ጋር ከፍተኛ ፉክክር በማድረግ ንብረቱን የግሉ አድርጎታል፡፡
ለዚሁ ህንጻ የቀረበው ዋጋ 680 ሚሊዮን ብር መሆኑ ለብዙዎች አግራሞትን የፈጠረ ክስተት ነው፡፡ ይህን ገንዘብ ንብ ባንክ በ15 ቀናት ዉስጥ ባንክ ገቢ ማድረግ ያለበት ሲሆን ከዚህ ዉስጥ ባንኩ ለተከሳሹ አቶ ከበደ ተሠራ ያበደረው 55 ሚሊዮን ብርና የወለድ ተመን ተቀናሽ ይደረጋል፡፡ ይህም ወደ 120 ሚሊዮን ብር እንደሚጠጋ ታውቋል፡፡
በአራጣ ብድር የተከሰሱት አቶ ከበደ ተሠራ ራሳቸው በንብ ባንክ ላይ ከፍ ያለ የአክስዮን ድርሻ ያላቸው ባለሐብት ናቸው፡፡
የአቶ ከበደ ተሠራ ወዳጅ የነበረቱት ሌላው አራጣ አበዳሪ አቶ አየለ ደበላ ሰኔ 30፣2005 በማረሚያ ቤት ክሊኒክ ዉስጥ ሳሉ ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል፡፡ የ22 ዓመታት ፍርደኛ የነበሩት አቶ አየለ በፕሮስቴት ካንሰር፣ በደም ግፊትና በስኳር ህመሞች ከተሰቃዩ በኋላ ነው ለሞት የተዳረጉት፡፡ በተመሳሳይ አቶ ገብረኪነዳን በየነ (ሞሮኮ) በስኳርና በልብ በሽታ የአልጋ ቁራኛ ሆነው ቆይተው በእስር ላይ ሳሉ ሕይወታቸው ያለፈው፡፡
በተመሳሳይ የ22 አመታት ፍርደኛ የሆኑት የመከታ ሪልስቴትና የበረከት ቆርቆሮ ባለቤትና ከበርቴ አቶ ከበደ ተሠራ ላለፉት 8 ዓመታት በእስር ሲማቅቁ ቆይተዋል፡፡