ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ከሰዓታት በፊት ለአሜሪካ ዜጎች ባስተላለፈው የ“ድንገተኛ እና የጸጥታ ጉዳዮች” መልዕክቱ ነገ እና ከነገ ወዲያ ወደ ኦሮምያ ክልል የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ዕቀባ ጣለ፡፡
ኤምባሲው በመልዕክቱ እንደጠቆመው በሐምሌ 30 እና ነሐሴ 1 በመላው ኦሮምያ ሊደረጉ የታቀዱ ተቃውሞዎች እና ሰላማዊ ሰልፎችን አስመልክቶ በማህበራዊ ድረ-ገጽ በሚለቀቁ ድረ ገጾች ሲከታታል ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት የኤምባሲው ሰራተኞች እስከ ነሐሴ 1 ድረስ ወደ ኦሮምያ የሚያደርጉት የግልም ሆነ ማንኛውም ጉዞ ላይ ዕቀባ መጣሉን አሳውቋል፡፡
ኤምባሲው በዋዜማ ቀደምት ዜና ላይ እንደተጠቀሰው ሁሉ የኢንተርኔት እና ሞባይል ስልክ ግንኙነት ሊቋረጥ እንደሚችል ቅድሚያ ግምቱን ሰጥቷል፡፡ በኦሮምያ ዋና ዋና ከተሞች አቅራቢያ ወደሚገኙ ቦታዎች የሚሄዱ ተጓዦች የመንገድ መዘጋትና የትራፊክ ክልከላ ሊገጥማቸው እንደሚችል ታሳቢ አድርገው እንዲንቀሳቀሱ ይመክራል፡፡ በርካታ የሰዎች ስብስብ እና ከፍተኛ የሆነ የፌደራል ፖሊስ ክምችት በየቦታው ሊታይ እንደሚችልም ይጠቁማል፡፡
“የዩ.ኤስ ኤምባሲ ወደ ክልሉ የሚጓዙ የአሜሪካ ዜጎችን በሙሉ የግል የደህንነት እቅዳቸውን እንዲመረምሩ፣ በአካባቢያቸው ያለውን ሁኔታ በንቃት አንዲከታተሉ፣ ከሰላማዊ ሰልፎች እና ስብሰባዎች ራሳቸውን እንዲያርቁ እና የሀገር ውስጥ የዜና አውታሮች የሚያወጧቸውን መረጃዎች እንዲከታታሉ ይመክራል” ይላል የኤምባሲው የማስጠንቀቂያ መልዕክት፡፡
በኦሮምያ ክልል በርካታ ተቃውሞዎች ያለምንም ቅድመ ዕውቀት አሊያም በትንሹ በሚታወቁ ሁኔታዎች እንደሚካሄዱ ያስታወሰው ኤምባሲው በሰላማዊ ሁኔታ የተጀመሩ ሰለማዊ ሰልፎች ሳይቀር ወደ ግጭት ሊያመሩ እንደሚችሉ ያስረዳል፡፡ ከሰላማዊ ሰልፎች ጋር በድንገት የተገጣጠሙ ተጓዦችም በፍጥነት ከአካባቢው እንዲርቁ፣ እየነዱ ከሆነ መኪናቸውን አዙረው እንዲመለሱ፣ ሰላማዊ ሰልፉን ፎቶ ግራፍ እንዳያነሱ እና ወደ ሆቴላቸው ወይም መጠለያቸው እንዲያመሩ ምክር ይሰጣል፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ እንዲህ ዓይነት መልዕክቶች ለዜጎቹ ሲያስተላልፍ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ ሰባት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያዎችን ያወጣ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አምሰቱ በኦሮምያ እየተደረገ ካለው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር የተያያዙ የጉዞ ምክሮች ናቸው፡፡ ሁለቱ በጋምቤላ እና በጎንደር ተከስተው በነበሩ አለመረጋጋቶች ወቅት የወጡ ነበሩ፡፡
እንደ አሜሪካ ኤምባሲ ሁሉ በሳምንቱ መጨረሻ ሊያካሄድ በታሰበው ክልል አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እና ተቃውሞን አስመልክቶ የኖርዌይ ኤምባሲ እና የተባባሩት መንግስታት የጸጥታ ጉዳዮች ዲፓርትመንት ከቀናት በፊት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ለዜጎቻቸው እና ለሰራተኞቻቸው አስተላልፈዋል፡፡