ዋዜማ- አማራ ባንክ በዘርፈ ብዙ የአስተዳደር ቀውሶች ሲታመስ ሰንብቶ ባንኩን ከ460 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ዳርገዋል የተባሉት የባንኩን ዋና ስራ አስፈፃሚና ሌላ አንድ አመራር ከሀላፊነት ማሰናበቱን ዋዜማ አረጋግጣለች።
በባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ የተፃፈውና (ዋዜማ የተመለከተችው) ለቦርድ አባላት የተሰራጨው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው የአማራ ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዋና አቶ ኄኖክ ከበደ ታደሰና የኮርፖሬት አገልግሎት ዋና መኰንኑን አቶ ክንዴ አበበን፣ በአፈጻጸም ድክመት ከሓላፊነታቸው አንስቷቸዋል።
የባንኩ ቦርድ ውሳኔውን ያሳለፈው፣ ዐርብ፣ ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ሲኾን፣ ኹለቱም ከፍተኛ ሓላፊዎች፣ ከተሾሙበት ዕለት ጀምሮ፣ በየጊዜው በሚሳዩት የሥራ አፈጻጸም ድክመት፣ የባንኩን ስትራቴጂያዊ ግቦች እና ቁልፍ የአፈጻጸም መመዘኛዎች ለማሳካት ያልቻሉና የማያስችሉ ናቸው፤ በሚል፣ ከሓላፊነታቸው እንዲነሡና ከባንኩ እንዲሰናበቱ መወሰኑን፣ ለኹለቱም በየስማቸው በደረሳቸው ደብዳቤ አስታውቋል።
በ2014/15 ዓ.ም. ባንኩ ከ306 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ለማስመዝገብ ዐቅዶ የነበረ ቢኾንም፣ ብር ከ460 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንዲገጥመው አድርገዋል ሲል ቦርዱ ጉለቱን አመራርሮች ከሷል።
ከሓላፊነታቸው በተነሡት አቶ ኄኖክ አበበ ቦታ፣ የባንኪንግ አገልግሎቶች ከፍተኛ መኰንን አቶ ጫን ያለው ደምሴ፣ ኅዳር 29 ቀን ጀምሮ በጊዜዊነት የዋና ሥራ አስፈጻሚነቱን ደርበው እንዲይዙ እንደመደባቸው ታውቋል።
የአማራ ባንክ በ 6 ቢሊየን ብር ካፒታል ከአንድ አመት ከመንፈቅ በፊት የተቋቋመ ግዙፍ ባንክ ሲሆን 171 ሺህ ባለአክሲዮኖች አሉት። [ዋዜማ]
To contact Wazema editors, please write wazemaradio@gmail.com