ዋዜማ- ሼኽ መሐመድ አልአሙዲን፣ አቶ አብነት ገ/መስቀል ለብልጽግና ፓርቲ “ሰጥተውብኛል” ያሉትን 75 ሚሊየን ብር ጨምሮ፣ ለተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት ከዚህ ቀደም በስጦታ መልክ የተለገሰውን ገንዘብ አቶ አብነት “ይመልስልኝ” ሲሉ ፍርድ ቤት ክስ መስርተው ሲከራከሩ ነበር።

ክሱን ሲመለከት የቆየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት፣ አቶ አብነት 852 ሚሊየን ብር ከነወለዱ እንዲከፍሉ ውሳኔ መስጠቱን፣ ዋዜማ የተመለከተችው የፍርድ ቤቱ ሰነድ ያመለክታል።

ሼኽ መሃመድ ዓሊ አልአሙዲ፣ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኩባንያ ላይ፣ ከ2004 እስከ 2013 ዓ.ም. ድረስ ከነበራቸው 70 በመቶ የአክስዮን ድርሻ፣ ከስምንት መቶ ኅምሳ ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው፣ ተወካያቸው በነበሩት አቶ አብነት ገብረመስቀል የባንክ ሂሳብ ላይ ገቢ ሲደረግ ነበር ይላል የፍርድ ቤት ሰነዱ።

ይኽ የሼኽ አልአሙዲ ድርሻም፣ በአቶ አብነት በኩል ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ለበርካታ ተቋማት እና ባለሥልጣናት በስጦታ መልኩ ሲሰጥ ወጪ ሆኗል። አልአሙዲ ግን አቶ አብነትን ስጦታ ለመስጠት አልወከልኩህምና ገንዘቡን መልስልኝ ሲሉ ክስ መስርተው ሲከራከሩ ነበር። 

ዋዜማ የተመለከተችው የክስ መዝገብ እንደሚለውም፣ የናሽናል ኦይል ኢትዮጵያ ኩባንያ ከ2004 እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ ካተረፈው ትርፍ ላይ፣ ለአልአሙዲ ይደርሳቸዋል ተብሎ በኩባንያው ከተረጋገጠው አጠቃላይ የትርፍ ድርሻ ውስጥ፣ በአቶ አብነት የባንክ ሂሳብ 852 ሚሊዮን 462ሺ 650 ብር ገቢ ተደርጓል።

ሰነዱ እንደሚገልጠው፣ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ፣ ከ581 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግሥት ተቋማትን ጨምሮ ለመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በሼኽ አልአሙዲ ፍቃደኝነት ከአቶ አብነት የባንክ ሂሳብ ተከፍሏል። ከዚህ የብር መጠን ውስጥም፣ ለብልጽግና ፓርቲ 75 ሚሊዮን  ብር መከፈሉን የሚጠቅሰው ይህ የፍርድ ቤት ሰነድ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሶሻል ትረስት ፈንድ 120 ሚሊዮን ብር፣ ለፌደራል ፖሊስ 5 ሚሊዮን ብር እና ለኢንፎርሜሽን ደኅንነት መረብ ኤጀንሲ 7 ሚሊዮን ብር መሰጠቱን ያትታል።

እነዚህ እና ሌሎች በሰነዱ የተጠቀሱትን ክፍያዎች አስመልክቶም፣ ሼኽ ዓሊ አልአሙዲ፣ አቶ አብነትን የወከልኩት ስጦታ እንዲሰጥልኝ አይደለም ሲሉ፣ እነዚህን ክፍያዎች ይመልስልኝ ሲሉ ተሟግተዋል። የፍርድ ቤቱ የከሳሽ እና የተከሳሽ ሰነዶች እንደጠቆሙት፣ ተከሳሹ አቶ አብነት ገ/መስቀል፣ እነዚህን ክፍያዎች ወጪ ያደርኩት በተሰጠኝ ውክልና በመሆኑ፣ ያደረኩት የውክልና ግዴታዪን መፈፀም ብቻ በመሆኑ ልከሰስ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል።  

ክሱን ሲመለከት የነበረው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም፣ አቶ አብነት ለብልፅግና ፓርቲ የተከፈለውን 75 ሚሊዮን ብር ጨምሮ፣ በክሱ የተዘረዘሩትን ክፍያዎች ሲከፍሉ ለአልአሙዲ ጥቅም ያልተፈጸሙ በመሆናቸው፣ ተከሳሹ አቶ አብነት ገ/መስቀል የተከሰሱበትን 852,462,650 ብር ለአልአሙዲ እንዲከፍሉ ሲያዝ፣ የይግባኝ መብት እንዳላቸው ጠቅሶ መዝገቡን መዝጋቱን ዋዜማ ሰምታለች። [ዋዜማ]