• ዘመዴነህ ንጋቱ ምስረታውን እያስተባበሩ ነው
Abe Sano, Head of CBE- FILE

ዋዜማ- መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች የካፒታል ገበያ አግልግሎት በሚሰጡ ኩባንያዎች ውስጥ እንዲሳተፉ ባወጣው መመሪያ መሰረት የኢንቨስትመንት ባንክ የማቋቋም ሂደት ላይ መሆኑን ዋዜማ ከምንጮቿ ሰምታለች።

ንግድ ባንክ የኢንቨስትመንት ባንኩን እያቋቋመ ያለው በኢንቨስትመንት አማካሪ ባለሙያ በአቶ ዘመዴነህ ንጋቱ አስተባባሪነት መሆኑንም መረዳት ችለናል። ዘመዴነህ ንጋቱ ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ የተባለ አማካሪ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ናቸው።

አቶ ዘመዴነህ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እያቋቋመው ባለው የኢንቨስትመንት ባንክም ከፊት ሊመጡ እንደሚችሉ መረዳት ችለናል።ሆኖም አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚያቋቁመው የኢንቨስትመንት ባንክ ውስጥ የሚሳተፉት እንደ ግለሰብ ነው ወይንስ የሚመሩትን ፌርፋክስ አፍሪካ ባለድርሻ አድርገው የሚለውን የሚለውን ለማጣራት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም ።

የኢትዮጵያ  ንግድ ባንክ የኢንቨስትመንት ባንክን የሚያቋቁመው ብሔራዊ ባንክ ንግድ ባንኮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዳይሰማሩ ያደረገውን የ2009 ዓ.ም መመሪያን ሀምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ባወጣው መመሪያ በመሻር ባንኮች በተለያዩ ዘሮፎች ላይ እንዲሰማሩ በፈቀደው መሰረት ነው።

መመሪያው ንግድ ባንኮች ከብድር ደረጃ አውጭነት ውጭ ባሉ እንደ ኢንቨስትመንት ባንክ ባሉ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ውስጥ ሙሉ ድርሻ ኖሯቸው በባለቤትነት እንዲይዙም ተፈቅዷል። ይህም በካፒታል ገበያ አዋጁ መሰረት የሚፈጸም እንደሆነም ተብራርቷል።

የኢንቨስትመንት ባንኮች በብዛት በካፒታል ገበያ ላይ የሚሳተፉ አካላትን የማማከር ፣ ኩባንያዎችም ሆኑ ጀማሪ ነጋዴዎች መንቀሳቀሻ ገንዘብን ሲፈልጉ በካፒታል ገበያ ውስጥ ገንዘብ የማፈላለግ ስራን ይሰራሉ ፤ አገናኝ ሆነው ያገለግላሉ። እንዲሁም ኩባንያዎች አክስዮን መሸጥ ሲፈልጉም ሂደቱን የማቀላጠፍ ስራን ይሰራሉ። በጥቅሉም የተለያዩ አካላት በካፒታል ገበያ ውስጥ ለሚኖራቸው እንቅስቃሴ ወሳኝ አከናዋኝ ሆኖው ያገለግላሉ። የኢንቨስትመንት ባንኮች የገቢ ምንጭም ከዚሁ አገልግሎታቸው የሚመነጭ ነው።

ከመንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምንጮቻችን እንደሰማነው የካፒታል ገበያ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ የኢንቨስትመንት ባንኮች እንዲቋቋሙ የተፈለገ ቢሆንም ከግዙፉ የመንግስት ባንክ መጀመሩ በገበያው ላይ ይበልጥ መተማመን እንዲኖር ያስችላል ተብሎ ታምኗል።

አቶ ዘመዴነህ ንጋቱም በሂደቱ ላይ እንዲሳተፉ የተፈለገበት ምክንያትም ከኢንቨስትመንት ስራዎች ጋር ቅርበት አላቸው በሚል እንደሆነም ሰምተናል። ፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ በሚል የሚጠራው በአቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የሚመራው ኩባንያ በዋነኝነት ትኩረቱ ፈንድ ማስተዳደር ሲሆን ፤ ከተለያዩ አካላት የሚሰበሰብ ገንዘብን አዋጭ በሆነ ኢንቨስትመንት ላይ በማዋል ትርፍ የሚካፈል ነው። ሆኖም ድርጅቱ በዚህ መልኩ ስኬታማ የሆኑ ስራዎችን በኢትዮጵያ ውስጥ ስለማከናወኑ ያገኘነው መረጃ የለም።

ኤርነስት ኤንድ ያንግ ከተባለ አለማቀፍ አማካሪ ተቋም ጋር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ጥምረት የነበራቸው ሲሆን ጥምረታቸው ባለመስማማት እንደተቋጨም ይታወሳል። አቶ ዘመዴነህ ሰላም የተባለ ባንክን በማቋቋም ሂደት ውስጥ የነበሩ ሲሆን ባንኩ የሚጠበቅበትን ካፒታል ማግኘት ባለመቻሉ እውን ሳይሆን መቅረቱ አይዘነጋም። [ዋዜማ ]