ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለተፈናቃዮች እርዳታ ሲሰጥ ለክልሎች ማከፋፈል ውስጥ ባይገባ ይሻለው እንደነበር የብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ተናገሩ።
ዶክተር ይናገር ደሴ ይህን ያሉት ዛሬ መጋቢት 19 ቀን 2011 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የመስሪያ ቤታቸውን የበጀት አመቱን ስምንት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ካቀረቡ በሁዋላ ለተጠየቁት ጥያቄ ምላሽን ሲሰጡ ነው።ከምክር ቤት አባል ንግድ ባንኩ የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ሆኖ ሳለ እንዴት እርዳታን በዚህ መልኩ ያከፋፍላል የሚል ጥያቄ ተነስቶላቸዋል።
የብሄራዊ ባንኩ ገዥ ለዚህ ጥያቄ ምላሽን ሲሰጡ ” ንግድ ባንክ እርዳታ ለመስጠት እኛን ማማከር አይጠበቅበትም፣ ሆኖም ባንኩ ለተፈናቃዮች እርዳታ ቢሰጥም ራሱ ማከፋፈል አለበት ብዬ አላምንም። የገንዘብ እርዳታውን ለክልሎች የማከፋፈሉ ስራን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ነው መሆን ያለበት” ብለዋል።ንግድ ባንኩ ይህንን ማድረጉ ላልተጠበቀ ትችት ዳርጎታል የሚል የግል እይታቸውን ሰጥተዋል።እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ራሱ የገንዘብ ችግር ውስጥ ሆኖ መቶ ሚሊየን ብርን ያክል ርዳታ መስጠቱ ጥያቄን አጭሮብኛል ብለዋል።ሁሉም ግን የግል እይታቸው መሆኑን ይናገር ደሴ ገልጸዋል።
በቅርቡ የአማራ ክልል ከ100 ሚሊየን ብር ላይ የተሰጠውን 4.7 ሚሊየን ብር እርዳታ ትንሽ ስለሆነና የክልሉን ህዝብ ስለማይመጥን አልቀበልም ማለቱ ይታወሳል።
የብሄራዊ ባንኩ ገዥ ለምክር ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት በበጀት አመቱ ሀገሪቱ ከፍተኛ የንግድ ሚዛን ጉድለት ውስጥ መቀጠሏን አንስተዋል።በስምንት ወራቱ ከሸቀጦች የወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ 1.64 ቢሊየን ዶላር ሲሆን ለገቢ እቃዎች ግን በተመሳሳይ ጊዜ 10.5 ቢሊየን ዶላር መከፈሉን ጠቅሰዋል።የገቢ እቃዎችን ለመግዛትም ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ አነስተኛ በመሆኑ በሀዋላና በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት የተገኙ ምንዛሬዎች ጥቅም ላይ መዋላቸው በሪፖርቱ ተነስቷል።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች ቢኖሩሞ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት የ2.6 ወር የገቢ ምርቶችና አገልግሎቶችን እንደሚሸፍንና ይህም ከተያዘው እቅድ በላይ መሆኑን ተነስቷል።የውጭ ምንዛሬ እጥረት ግን አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑንና አጋር ሀገራት ለኢትዮጵያ የሰጡት ምንዛሬ ባይኖር ችግሩ የከፋ ይሆን እንደነበር የብሄራዊ ባንኩ ገዥ ተናግረዋል።
የሀገሪቱ የንግድ ባንኮች ጤናማ ሁኔታ ላይ መሆናቸው ልማት ባንክ ግን ችግር ውስጥ መሆኑ ተነስቷል። የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ገበያ ክፍት ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ዶክተር ይናገር ጠቁመዋል።