ዋዜማ- የትግራይ ክልል ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ 14ሺ መምህራን ወደ ስራ እንዳልተመለሱ ዋዜማ ስምታለች።
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት፣ 14ሺ መምህራኖቼን በስራ ገበታቸው ላይ ላገኛቸው አልቻልኩም ሲል ለዋዜማ የነገራት፣ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ነው። በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ፣ ክልሉ ከፍተኛ ጉዳቶችን ካስተናገደባቸው ተቋማት መካከል አንዱ የትምህርቱ ዘርፍ ሲሆን፣ በ2012 ዓ.ም.ክልሉ ከነበሩት 46ሺህ 598 መምህራን ውስጥ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 14ሺ ዎቹ ወደ ስራ እንዳልተመለሱ የቢሮው ኅላፊ ዶ/ር ኪሮስ ጉእሽ ለዋዜማ ተናግረዋል።
መምህራኑ ወደ ስራቸው ካልተመለሱባቸው ምክንያቶች መካከል፣ በመስዋዕትነት እና እርሳቸው “ወራሪ ሀይሎች” ባሏቸው ወገኖች መገደላቸው ይገኝበታል። ከዚህ ባለፈም፣ በቀላል ህክምና መዳን እየቻሉ መድኅኒት ባለማግኘታቸው የሞቱ፣ ጥቃት ደርሶባቸው የአካል ጉዳተኛ የሆኑ፣ ከጥቃት ለመሸሽ ሲሉ የተሰደዱ፣ ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ካምፕ የተጠለሉ እና ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ሌላ ስራ የቀየሩ መኖራቸው ቁጥሩን 14ሺ እንዳደረሰው ኅላፊው አስረድተዋል።
ወደ ስራ የተመለሱ መምህራንም ቢሆኑ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ጉዳት የደረሰባቸው እና የ17 ወራት ደሞዝ ያልተከፈላቸው በመሆናቸው ለኢኮኖሚያዊ ችግር የተጋለጡ ናቸው ብለዋል ኪሮስ።
ከ14 ሺዎቹ መምህራኖች መጓደል ባለፈ ትምህርት ቤቶቹም ቢሆኑ፣ ከጦርነት በፊት ከነበሩት 2492 ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ 658ቱ ምንም አይነት የመማር ማስተማር አገልግሎት መስጠት አልጀመሩም ተብሏል።
የትምህርት ቤቶቹ ውድመት አነስተኛ፣ ከፊላዊ እና ሙሉ በሙሉ በማለት መከፈላቸውን ያነሱት ኪሮስ፣ አነስተኛ ጉዳት የደረሰባቸው የትምህርት ቁሳቁስ ብቻ ቢሟላላቸው ወደ ማስተማሪያነት መመለስ የሚችሉ እና የተወሰነ ጥገና የሚፈልጉም መኖራቸውን ጠቅሰዋል። ሙሉ በሙሉ ውድመት ያጋጠማቸው ግን፣ እንደ አዲስ መገንባት የሚያስፈልጋቸው ናቸው።
የትምህርት ቁሳቁሶቹን አስመልክቶ ደግሞ፣ 12.5 ሚሊየን መጻሕፍት፣ ከ30ሺ በላይ ኮምፒውተሮች ፣ 300ሺ የትምህርት ማስተማሪያ ግብዓቶች እና የላብራቶሪ እቃዎች፣ በርካታ ብላክ ቦርዶች እና የተማሪ ወንበሮች ሙሉ በሙሉ እና በከፊል መውደማቸውን ኅላፊው ይናገራሉ።
በፌደራል ደረጃ እየተተገበረ የሚገኘውን አዲሱን የትምሕርት ካሪኩለም ለመተግበር የገንዘብ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ባለመኖሩ ለመተግበር ችግር እያጋጠመ መሆኑን ኅላፊው አስረድተዋል። በጦርነቱ የተነሳ ትምሕርታቸውን አቋርጠው፣ ዳግም ወደ ትምሕርት ቤት የሚመልሱ ታዳጊዎች፣ እንደገና ካቋረጡበት የትምሕርት ደረጃ በመጀመራቸው የተነሳ የሚፈጠሩ ችግሮች እንዳሉም ተረድተናል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም፣ ከርዕሰ መምህራን ጀምሮ ታች እስካለው የሰው ሀይል ድረስ፣የደሞዝ ችግር ያለበት፣ የሥነ-ልቦና መቃወስ የደረሰበት እና ቁጥሩም የተጓደለ መሆኑ፣ ከጦርነቱ በኋላ አገግሞ በሙሉ አቅምና ዝግጁነት ወደ ስራ ለመግባት ፈተና መሆኑን ኪሮስ ያብራራሉ።
ክልሉ በእነዚህ ችግሮች ውስጥ ቢሆንም ፣ በዳስ፣ በቆርቆሮ እና በሳር የመማሪያ ክፍሎቹን በማልበስ፣ የዚህኛው ዓመት የትምሕርት ዘመን መጀመሩን ዋዜማ ተረድታለች።[ዋዜማ]