- የፌደራሉ መንግስት የድርድር ጉዳይን የሚከታተል ኮሚቴ አቋቁሟል
ዋዜማ ራዲዮ- የትግራይ ክልል መንግስት ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለድርድር ዝግጁ መሆኑንና የኬንያው ፕሬዝዳንት አደራዳሪ እንዲሆኑ ፍላጎት እንዳለው ባሰራጨው ደብዳቤ የገለጠ ሲሆን ለክልሉ ህዝብ ግን ትግሉን ወደመጨረሻው ምዕራፍ ለማሸጋገር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።
የክልሉ ኘሬዝዳንት ደብረፅዮን ገብረሚካዔል ማክሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች በትግርኛ በሰጡት መግለጫ በቅርቡ በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች በተደረጉ ኮንፈረንሶች ትግሉ ወደ መጨረሻ ደረጃ እንዲደርስ ከመግባባት ተደርሷል ብለዋል።
ከፌደራል መንግስት ጋር እየተካሄደ ነው በሚባለው ውይይትና ድርድር ዙርያ እስከ አሁን ድረስ ምንም አይነት ድርድር አልተካሄደም ፣ ህዝባችን ከበባ ላይ እንዲሁም መሬታችን ተወሮ ባለበት ሁኔታ ወደ ድርድር የምንቀርብበት ሁኔታ የለም ሲሉ ደብረፅዮን አብራርተዋል።
በአጠቃላይ ዋና አላማችን የትግራይ ህዝብ መብትና ጥቅም ማስከበር ሲሆን የትግራይ ሉአላዊ ግዛት መከበር ፣ ሪፈረንደም ፣ የትግራይ ሰራዊት ሁኔታ ፣ በትግራይ ላይ “የዘር ማጥፋት የፈፀሙ” ተጠያቂ እንዲሆኑ መስራት እና ተገቢ ካሳ እንዲከፈል ማድረግ ለድርድር የማይቀርቡ ነጥቦች ናቸው ብለዋል ።
“የኤርትራ ሰራዊት ከትግራይ መውጣት አለበት፣ ባልወጣበት ሁኔታ አንደራደርም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ “በቅርብ ጊዜ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የትግራይ መንግስት በምዕራብ ትግራይ ላይ ያለውን አቋም ቀይሯል ተላሳልሷል የሚባለው ውሸት ነው፡፡ ይልቁንም የተያዙ መሬቶቻችንን ለማስለቀቅ ነው እየሰራን ነው” ብለዋል።
ደብረፂዮን ጨምረውም “ውይይት አይኑር አላልንም። ነገር ግን አስቀድሜ የዘረዘርኳቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ምን ነገር ይዘን ነው የምንወያየው? ሲሉ ጠይቀዋል።
በሌላ በኩል በራሳቸው በክልሉ ፕሬዝዳንት ተፅፎ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ በተሰራጨ ደብዳቤ የትግራይ ክልል በአፍሪቃ ሕብረት በኩል የሚደረገውን ድርድር ለመቀጠል እንደሚቸገርና በአደራዳሪው ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ ላይ የገለልተኝነት ጥያቄ አንስቷል። የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽነርንም በብርቱ ተችቷል።
በምትኩም የኬንያው ኘሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አደራዳሪ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ የትግራይ ክልል መንግስት በደብዳቤው አስታውቋል።
ኬንያታ ገለልተኛ መሆናቸውን ያስመሰከሩና እምነት የምንጥልባቸው መሪ ናቸው ያለው የትግራይ ክልል ደብዳቤ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና የመንግስታቱ ድርጅት በድርድሩ እንዲሳተፉ ፍላጎት እንዳለው ዘርዝሯል።
የታንዛኒያ መንግስት እያደረገ ያለውን የሰላም ጥረት ያመሰገነው የትግራይ ክልል የአፍሪቃ ህብረት አባል ሐገር የሆነችው ኬንያ ከዚህ ቀደም ያደረገችውን የማደራደር ሙከራ በዝርዝር አላብራራም።
ይህ የትግራይ ክልል ደብዳቤ በናይጄሪያው የቀድሞ ኘሬዝዳንት ኦባሳንጆ በአፍሪቃ ሕብረት በኩል ሲደረግ የነበረውን የድርድር ሙከራ ወደፊት ለመራመድ እንደሚያዳግተው ግልፅ አድርጓል።
በፌደራሉ መንግስት በኩል
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ትናንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለቀርቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አገርን ወክሎ የሚደራደር ብሄራዊ ኮሚቴ እንደተቋቋመ ገልጸዋል።
ብሄራዊ የድርድር ኮሚቴውን የሚመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደሆኑ እና ኮሚቴው በቅርቡ ለገዥው ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክረ ሃሳቡን እንደሚያቀርብ እና ያኔ ምክረ ሃሳቡ ለሕዝብ እንደሚገለጽ ተናግረዋል።
ዐቢይ ከሕወሃት ጋር እስካሁን በየትም አገር ድርድር እንዳልተጀመረም ገልጸዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]