Addis Taxiዋዜማ ራዲዮ- ትራንስፖርትና ፖለቲካ በአህጉር አፍሪቃ ልዩ ዝምድና አላቸው። በተለይ በከተሞች አካባቢ ያሉት ታክሲዎች ለተቃዋሚዎች ዋነኛ የፖለቲካ መሳሪያ ሆነው በማገልገል ለመንግስታት ራስ ምታት የሆኑባቸው አጋጣሚዎችን ማስታወስ ይቻላል። በሀገራችን በ 1997 ምርጫ ወቅት ታክሲዎች የተጫወቱት ሚና አይዘነጋም። ተከታዩ የቻላቸው ታደሰ ዘገባ ትራንስፖርትና የተቃውሞ ፖለቲካን በአዲስ መነፅር ይመለከታል። ተጨማሪ የድምፅ ዘገባችንን ከታች ይመልከቱ!

በብዙ አፍሪካዊያን ሀገሮች የከተማ ታክሲ ፖለቲካ ብዙ ውጥረት የሚታይበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ በመንግስት እና በከተማ ታክሲ ማህበራት መካከል ያለው ግንኙነት እንደሌሎች ሀገሮች የተካረረ ውጥረት ባይታይበትም ግንኙነቱ ግን የተዛባ እና ከመንግስት ፖሊሲ ጋር ፈጽሞ ባለመጣጣም ላይ የተመሰረተ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በብዙ አፍሪካዊያን ሀገሮች የከተማ ታክሲ አገልግሎት ትልቅ ፖለቲካዊ ጉዳይ የሚያስነሳ ስለሆነ የታክሲ ማህበራት አደራጃጀት እና ከመንግስት ጋር ያላቸው ግንኙነት ባጠቃላይ በመንግስት እና ህዝብ መካከል ላለው ሁለንተናዊ መስተጋብር አንድ መገለጫ ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡

የኢትዮጵያ ሙከራ ግማሽ ሙሉ

በርግጥ በኢትዮጵያም በ1966ቱ ህዝባዊ አብዮት ወቅት የታክሲ አሽከርካሪዎች አድማ አብዮቱን በማቀጣጠል እና ዘውዳዊውን መንግስት በማዳከም ከፍ ያለ ፖለቲካዊ ሚና ተጫውቷል፡፡ በዘመነ ኢሕአዴግም ቢሆን በ1997ቱ ምርጫ ዋዜማ የአዲሳባ ከተማ ታክሲ ሹፌሮች ወደ አደባባይ ለወጡ የተቃዋሚው ቅንጅት ፓርቲ ደጋፊዎች በነጻ አገልግሎት በመስጠት ገዥውን ፓርቲ ኢሕአዴግ ማስደንገጥ ችለው ነበር፡፡

ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት የከተማ ታክሲ ማህበራት የስራ ማቆም አድማ በማድረግ ወይም የተቃዋሚዎች ፖለቲካዊ መሳሪያ በመሆን እንዳያሽመደምዱት ስለሚሰጋ በተለይ ከ1997 ወዲህ የአዲሳባ ከተማ ታክሲ ማህበራትን በዐይነ ቁራኛ ነው ሲያያቸው የኖረው፡፡ የታክሲ አሽከርካሪዎችን በጥብቅ አስተዳደራዊ መመሪያዎች በማሰር እና የታክሲ ማህበራቱ ደሞ የኢኮኖሚ ጡንቻቸው እንዳይጠነክር ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ጫናዎች ሲያደርግ ነው የሚታየው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም መንግስት የተለያዩ ደንቦችን ሲያወጣ በታክሲዎቻችሁ ውስጥ ህዝብን ለአመጽ የሚያነሳሱ ጥቅሶችን ትለጥፋላችሁ በማለት ሲወንጅላቸው መስማት የተለመደ ነው፡፡ ከሁለት ዐመት በፊት የታክሲ አሽከርካሪዎች መንግስት ያወጣውን የትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ተቃውመው የሥራ መቆም አድማ ቢመቱም አድማቸው ግን ከአንድ ቀን ሊያልፍ አልቻለም፡፡ መንግስትም ደንቦቹን ለተወሰነ ጊዜ ቢያዘገያቸው እንጂ እጁን ተቆልምሞ አቋሙን ሲቀይር ማየት ግን የተለመደ አይደለም፡፡ መንግስት ደንቦችን ሲያወጣ ከታክሲ ማህበራቱ ጋር ሁነኛ ድርድር ሊያደርግ ቀርቶ በቅንነት እንደማያወያያቸው ነው የታክሲ አሽከርካሪዎች ቅሬታቸውን ሲገልጹ የሚሰሙት፡፡ መንግስትም እንደ አገልግሎት ሰጭ ሳይሆን እንደ መንግስት ተቃዋሚ እንደሚያያቸው ባለፈው ግንቦት ከመንግስት ጋር ባደረጉት ውይይት ተናግረው ነበር፡፡

ባጠቃላይ ባለፉት ዐመታት መንግስት ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ በአፍሪካ ሁለተኛ የሆነውን የአዲሳባ ከተማ ባቡር ሲዘረጋ፣ የታክሲ ማቆሚያ ወይም ፓርኪንግ ክፍያን ሲተምን እና በታክሲዎች ስምሪት እና ስነ ምግባር ላይ የተለያዩ አስገዳጅ መመሪያዎችን አውጥቶ ሲተገብር የታክሲ ማህበራቱ በተናጥል ቅሬታቸውን ቢገልጹ እንጂ በተደራጀ መልኩ መንግስትን ሊቃወሙ የሚችሉበት ተቋማዊ ጥንካሬ ግን እንደሌላቸው ግልጽ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓት መሠረት ከጣለች ሩብ ክፍለ ዘመን ቢያልፉም ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት ግን በተግባር የመደራጀት መብትን ጨፍልቆ በመያዙ መብቱ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እመርታ አላሳየም፡፡ የአዲሳባ ከተማ ታክሲ ባለንብረቶች እና አሽከርካሪዎች ማህበራትም የዚሁ ሀገራዊ ችግር ሰለባ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው የከተማዋ ታክሲ አሽከርካሪዎች እና የታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት በመንግስት ላይ ሁነኛ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ሲፈጥሩ የማይታዩት፡፡ የመንግስት አፋኝ ፖሊሲ እና ቁጥጥሩ ጠንካራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ የታክሲ ማህበራቱ አንድ ጠንካራ ብሄራዊ ማህበር የሌላቸው መሆኑ ደሞ ከመንግስት ተቋማት አንጻር ደካማ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡

ጎረቤቶቻችንስ?

ባንጻሩ ኬንያን እና ኡጋንዳን ጨምሮ በብዙ አፍሪካ ሀገሮች ግን የከተማ ታክሲ ማህበራት አይነተኛ ፖለቲካዊ ሚና ሲጫወቱ ነው የሚታዩት፡፡ በጎረቤት ሀገራት የሚታየው ስር የሰደደ የታክሲ ማህበራት አሉታዊም ሆነ አወንታዊ ተጽእኖ ፈጣሪነት በከፊል በአውሮፓዊያኑ ቅኝ ግዛት ስር ከመቆየታቸው ጋር ይያያዛል፡፡ በጎረቤት ኬንያ እና ኡጋንዳ ባሉ አንዳንድ በሙስና እና ብሄረሰብ ፖለቲካ በሚታመሱ ሀገሮች የታክሲ ማህበራቱ በሂደት ጠንክረው መንግስትን በተለይም የከተማ አስተዳደሮችን መልሰው በመቆጣጠር ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እቅስቃሴዎችን ሁሉ ሲዘውሩ የታየውም ለዚህ እንደሆነ የመንግስት እና ህዝብ መስተጋብር አጥኝዎች ይመሰክራሉ፡፡ ለምሳሌ በኬንያ ማታቱ የሚባሉት ሚኒባስ ታክሲዎች ባንድ ወቅት “ሙንጊኪ” በተባለ የተደራጀ ወንጀለኛ ቡድን ቁጥጥር ስር ውለው የሀገሪቱ ጎሳ ብጥብጥ ሁነኛ ተዋናይ መሆን ችለው ነበር፡፡ በደቡብ አፍሪካም በታክሲ መስመር ቁጥጥር በ1990ዎቹ በርካታ ቡድኖች መካከል ግጭቶች ይስተዋሉ ነበር፡፡ በሌላ በኩልም እንደ ኬንያ ባንዳንድ አፍሪካዊያን ሀገሮች ትላልቅ ፖለቲከኞች ሳይቀሩ የበርካታ ታክሲዎች ባለንብረት በመሆን እና በታክሲ ማህበራት ውስጥ ቁልፍ የወሳኝነት ሚና በመያዝ በሀገራዊ ፖለቲካው እና ኢኮኖሚው ውስጥ አይነተኛ ሚና ሲጫወቱ ይታያል፡፡

ከሌሎች አፍሪካዊያን ሀገራት የተለየ የሆነው የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ምስረታ እና እድገት ግን ከዚህ አንጻር የራሱ መለያዎች አሉት፡፡ ሀገረ መንግስቱ እንደ ተቋም ሲታይ የከተማ ታክሲ ማህበራትን ጨምሮ ባጠቃላይ መንግስታዊ ካልሆኑ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ያለው ግንኙነት የተዛባ እና በአፋኝ ፖለቲካዊ ባህል ላይ ተመስርቶ የኖረ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከሌሎች አፍሪካዊያን ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር የንጉሳዊው፣ የወታራዊውና የአሁኑ መንግስት ተቋማዊ ጥንካሬ እና በሲቪል ማህበረሰቡ ላይ ያላቸው የቁጥጥር አቅም ጠንካራ ሆኖ ነው የቆየው፡፡

ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስትም ከራሱ መንግስታዊ እና የፓርቲ መዋቅር ውጭ መፈናፈኛ የሚሆን ነጻነት መፍጠር ስለማይፈልግ የሲቪል ማህበረሰቡ አካል የሆኑት የከተማ ታክሲ ማህበራት መንግስትን መገዳደር የሚችሉበት እድልም ሆነ ጥንካሬ የላቸውም፡፡ ሀገሪቱ በብሄር ተኮር መንግስታዊ ሥርዓት የምትመራ ከመሆኗ አንጻር ፖለቲካ ፓርቲዎች እና አጠቃላይ የመንግስት እና ህዝብ ግንኙነት የብሄር ማንነትን መሠረት ያደረገ ቢሆንም እንደ ኬንያ እና ኡጋንዳ የታክሲ ማህበራት በብሄረሰብ ተደራጅተው ፖለቲካዊ ሚና የሚጫወተበት ደረጃ ላይ አልደረሱም፡፡ የብሄር ፖለቲከኞችም ዘርፉን በመንግስታዊ መዋቅር ከመቆጣጠር አልፈው የንብረት ባለድርሻ ሆነው የትቅም ግጭት ውስጥ ስለመግባታቸው የሚጠቁም መረጃ የለም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ናይሮቢን፣ ዳሬሰላምን እና አክራን ጨምሮ ከ15 በላይ አፍሪካዊያን ከተሞች በቦታ ርቀት ተመን የሚያስከፍሉ እንደ ኡበር ያሉ ዐለም ዐቀፍ የታክሲ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች መስፋፋት ጀምረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ግን ሀገሪቱ የዐለም ንግድ ድርጅት አባል ባለመሆኗ እና መንግስትም በሚከተለው ፖሊሲ ምክንያት ኢኮኖሚው ዘመናዊ የውጭ ታክሲ አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎችን ጨምሮ ለበርካታ ትላልቅ እና መካከለኛ አገልግሎት ሰጭ የውጭ ኩባንያዎች ተጠርቅሞ የተዘጋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ እና እንደ ኡበር ያሉ ኩባንያዎች በአዲሳባ በቅርቡ ፍቃድ የማግኘት እድላቸው ዝቅተኛ መሆኑ አነጋጋሪ አይሆንም፡፡ በተለይ ብዙ አውሮፓዊያን ሀገሮች በኡበር አሰራር ላይ ህጋዊ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው ደሞ መንግስት ለክልከላው ተጨማሪ መከራከሪያ አድርጎ እንደሚጠቀምበት ግልጽ ነው፡፡ የውጭ ኩባንያዎች እና ያለቀረጥ የሚገቡ ዘመናዊ ታክሲዎችም ናሮቹን ታክሲዎች ከስራ ውጭ በማድረግ ሥራ አጥነትን ያበዛሉ የሚለው ክርክርም አንዱ መሟገቻው ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ ስጋት አለው

ኢሕአዴግ-መራሹ መንግስት ከ1990ዎቹ ወዲህ በርካታ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለግል ባለሃብቶች ቢሸጥም የአዲሳባ ከተማ ያለው አንበሳ የከተማ አውቶብስ ድርጅት ግን አሁንም በመንግስት ባለቤትነት ስር እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ መንግስት ግን ዘርፉን ሊያሻሽለው ካለመቻሉም በላይ በከተማዋ ጸረ-መንግስት የተቃውሞ ሰልፎች በተካሄዱ ቁጥር አውቶብሶቹ የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ ይታያል፡፡ የግሉ ዘርፍ የከተማዋን ትራንስፖርት ፍላጎት ለማርካት ጉልህ ሚና እንዲኖረው ዘርፉን ለውድድር ከመክፈት ይልቅ መንግስት የመረጠው የጦር ሠራዊቱ ንብረት የሆነው መከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የሚያርታቸውን የጥራት ጥያቄ የሚነሳባቸውን አውቶብሶች በውድ ዋጋ መግዛት አገልግሎቱን በመንግስት ስር ማስቀጠል ነው የሆነው፡፡ ለዚህ ፖሊሲ ደሞ ከኢኮኖሚያዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ምክንያቶች እንደሚበልጡ መናገር ይቻላል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በመሃል ባለፉት ሁለት ዐመታት የኢንተርኔት አገልግሎትን ጭምር ያካተቱ እና በጉዞ ርቀት ተምነው የሚያስከፍሉ ጥቂት ሀገር በቀል የከተማ ታክሲ አገልግሎት ሰጭ ኩብንያዎች በዋና ከተማዋ አዲሳባ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡

አዲሳባ ከተማ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ትገኛለች፡፡ የነዋሪዎቿ የመጓጓዣ ፍላጎትም በፍጥነት እያደገ መሆኑን የመንግስት አሃዞች ጠቋሚ ናቸው፡፡ በታክሲ ክፍተቱ ሳቢያም የሞተር ብስክሌቶች ሳይቀሩ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ታክሲዎች የመንግስት ሠራተኞች፣ አነስተኛ እና መካከለኛ ነጋዴዎች እና ተማሪዎችን ጨምሮ የአብዛኛው ኅብረተሰብ ክፍል የዕለትተለት እንቅስቃሴ የጀርባ አጥንት መሆናቸው አሊ የማይባል ነው፡፡ በከተማዋ የዘመናዊ ሆቴሎች እና ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎች ግንባታ በጣም ፈጣን እንደሆነ በዐለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ይነገርለታል፡፡

ያም ሆኖ የታክሲ ዘርፉ በጠቅላላው በአደረጃጀቱ፣ በተቋማዊ ብቃቱ፣ በአገልግሎት ጥራቱ እና ብዛቱ በርካታ ውስንነቶች ያሉበት በመሆኑ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአህጉራዊው አፍሪካ ኅብረት እና ዐለም ዐቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ለሆነችው እና አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ነዋሪ ላላት ከተማ የማይመጥን እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ደጋግመው የገለጹት እውነታ ነው፡፡ የዐለም ባንክ መረጃ እንደሚያሳየው 65 በመቶ የሚሆኑት የአዲሳባ መንገዶች የእግረኛ መተላለፊያ መንገድ የላቸውም፡፡ አዲሳባ ተመሳሳይ ስፋት ካላቸው አፍሪካዊያን ከተሞች ጋር ስትነጻጸር የተሸከርካሪዎቿ ብዛት አነስተኛ ቢሆንም በትራፊክ ፍሰት መጨናነቅ ግን ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደምትመደብ ነው የባንኩ መረጃ የሚያሳየው፡፡ ይህንኑ ችግር ለመፍታት ባንኩ የአዲሳባን ጨምሮ የሀገሪቱን ትራንስፖርት ዘርፍ ለማዘመን ባለፈው ዐመት የ300 ሚሊዮን ዶላር ብድር አጽድቆ ነበር፡፡

እውነታው ይሄ ቢሆንም ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ግን በተለይ ከ1997ቱ ምርጫ ወዲህ ከአዲሳባ ነዋሪ ጋር ያለው ግንኙነት ሰባራ ስለሆነ የተገልጋዩም ሆነ የታክሲ ማህበራቱ እሮሮ ሁነኛ መፍትሄ ሊሰጠው አልቻለም፡፡ አሁንም በየዕለቱ የሚሰማው የከተማዋ ታክሲ እጥረት የተወላገደው የመንግስት እና ህዝብ ግንኙነት ዐይነተኛ ማሳያ ሆኖ እየቀጠለ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደሞ በከተማዋ ዙሪያዋ ያሉትን አጎራባች የኦሮሚያ ክልል ዞኖችን ያካተተው የአዲሳባ መሪ እቅድ (Master Plan) ተፈጻሚ መሆን አለመቻሉ የተቀናጀ የከተማ ታክሲ አገልግሎት መስጠት እንዳይቻል ስላደረገ ዘርፉ የመንግስት ብሄር ተኮር ፖለቲካ ሰለባ ሊሆን ችሏል፡፡

የከተማዋ ተጠሪነትም በፌደራሉ መንግስት ስር በመሆኑ የመጓጓዣ ዋጋ ተመን ማስተካከያ የሚያደርገውም የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን መሆኑ ይታወቃል፡፡ እናም ለታክሲ ማህበራቱ እና ለከተማዋ ነዋሪ ቅርብ የሆነው የከተማው አስተዳደር በታክሲ ማህበራት ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ጥርስ ያለው መምሪያ የማውጣት ሥልጣን የለውም ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ከአንድ ዐመት በፊት 65 ያህል የአዲሳባ ታክሲ ማህበራት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው ታክሲዎችን ያለቀረጥ ለማስገባት የከተማዋን አስተዳደር ጠይቀው ቢፈቀድላቸውም የመጨረሳሻውን ውሳኔ የሚሰጠው የፌደራሉ መንግስት ግን እስካሁን ምላሽ እንዳልሰጣቸው ተዳጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይሰማሉ፡፡

የታክሲ ማህበራቱ የዋጋ ተመን ማስተካከያ እንዲከለስ ሲጠይቁም መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞን በመስጋት እና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ የመፍጠር አቅማቸው ደካማ መሆኑን በማየት ጭምር ይመስላል አይቀበላቸውም፡፡ የክፍያ ጭማሪውን የሚፈቅደው የነዳጅ ዋጋን ተከትክሎ እንጂ ሌሎች ጥሬ እቃዎችን ዋጋ ግምት ውስጥ አስገብቶ ለመሆኑ የታክሲ ማህበራቱ ከመንግስት ጋር ግንኙነት አድሏዊ እና በብዝበዛ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የታክሲ አሸከርካሪዎች ማህበራት ከመንግስት ጋር ብቻ ሳይወሰን ከታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት ጋርም ነው የተዛባ ግንኙነት ያላቸው፡፡

ዘመናዊ የከተማ ታክሲ አገልግሎት ከሀገራዊ ሃብት ክምችት አለመኖር፣ ከባንኮች የማበደር ፖሊሲ ወይም አቅም ውስንነት እና ከፈጣን ኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖር ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ በተለይ በመንግስት ሙሉ ቁጥጥር ስር የተያዘው የኢንተርኔት ትይይዝ እና ፍጥነት በአፍሪካ በኋላ ቀርነቱ በመጨረሻው ደረጃ ላይ ስለሚገኝ የከተማ ታክሲ አገልግሎት ዘርፉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ለማድረግ እንቅፋት ሆኗል፡፡ መንግስት በፖሊሰው ቢፈቅድ እንኳ እንደ ኡበር ዐይነቶቹን ትላልቅ የውጭ የታክሲ ኩባንያዎች ለመሳብ የሚችል መሰረተ ልማት እንዳልዳበረ ይታወቃል፡፡

የመንግስት አካሄድ ሀገሪቷንም ሆነ ከተማዋን ሸብቦ በመያዝ ዋጋ እያስከፈለ መሆኑ አሊ የማይባል ነው፡፡ በርግጥም ምንም እንኳ ከፊሉ ታክሲ አገልግሎት ተጠቃሚ ኑሮውን በኢመደበኛው ኢኮኖሚ ላይ የመሰረተ ስለሆነ በበቂ ሁኔታ ባይጠናም የከተማ ታክሲ እጥረት እና ኋላ ቀርነት በጠቅላላው በከተማዋ ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍ ያለ እንደሆነ ነው ባለመያዎች የሚገምቱት፡፡

ባጠቃላይ የመንግስት እና ህዝብ መስተጋብር አንድ ማሳያ የሆነው የተዛባው የአዲሳባ ታክሲ አገልግሎት እና ማህበራቱ መንግስት እንደፈለገ የሚዘውራቸው እንደሆኑ አያጠያይቅም፡፡ መንግስት ለከተማ ሰላማዊ ሰልፎች እና ህዝባዊ አመጾች በእጅጉ ድንጉጥ ስለሆነ የከተማዋን ፍላጎት እና ዘመኑን ታሳቢ አድርጎ በኋላ ቀሩ ታክሲ ዘርፍ እና በታክሲ ማህበራቱ ላይ ያለውን ቁጥጥር በቅርቡ ያላላል ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ የድምፅ ዘገባ ከታች

https://youtu.be/DQiIGtLFSeg