ዋዜማ- ማክሰኞ፣ ጳጉሜ 4፣ 2017 ዓ፣ም ለኢትዮጵያ ታሪካዊ ቀን ነበር። ከዚህ ዕለት ጀምሮ፣ ጉባ፣ ፕሮጀክት ኤክስ፣ ሚለኒዬም ግድብ፣ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ ንጋት ሐይቅ የሚሉ ስያሜዎች፣ ከረጅሙ ናይል ወንዝ ጋር ታሪክ ላይ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የታተሙ ሆነዋል።
በዚህ ታሪካዊ ቀን፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ በግዙፍነቱ ተወዳዳሪ የሌለውን፣ ሊታለፉ የማይችሉ የሚመስሉ ከባድ ውጣ ውረዶችን ለ14 ዓመታት ያሳለፈችበትን፣ የበርካታ ትውልዶች ሕልም የነበረውን እና የራሷን 5 ቢሊዮን ዶላር ያፈሰሰችበትን ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ጉባ ላይ በታላቅ ስነ ሥርዓት አስመርቃለች።
በግድቡ የምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን የገነባችው፣ ለራሷ ብልጽግና፣ ለምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ እና የመላው ጥቁር ሕዝቦችን ታሪክ ለመቀየር እንጅ ፈጽሞ ወንድሞቿን ሱዳንን እና ግብጽን ለመጉዳት አይደለም በማለት ተናግረዋል።
ዐቢይ፣ ሕዳሴ ለጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ሆኖ የሚቆይ መሆኑንም ገልጸዋል። ዐቢይ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዳሴ ግድብ የሚያመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁለት ዓላማዎች እንደሚጠቀምበት ገልጸዋል። ዐቢይ በቅድሚያ የጠቀሱት ዓላማ፣ የኤሌክትሪክ ኃይሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ የኃይል ተደራሽነት ለማሻሻል ይውላል የሚለውን ሲሆን፣ ከዚህ የተረፈው ኃይል ለቀጠናው አገራት የሚሸጥ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከኢትዮጵያ ሕዝብ 46 በመቶው ባኹኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን ተደራሽነት የሌለው ስለመሆኑ፣ የመንግሥትም ሆነ የዓለም ባንክ መረጃዎች ያመለክታሉ። የኤሌክትሪክ ኃይል ቅድሚያ ለውጭ ገበያ ወይስ ለአገር ውስጥ ፍጆታ? የሚለው ጥያቄ የፖሊሲ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱ ባሁኑ ወቅት ካላት የኃይል ማሠራጫ መሠረተ ልማቶች አቅም ጋር ጭምር የሚያያዝ እንደሆነ የታወቀ ነው። በተለይ ከትላልቅ ከተሞች ውጭ የኃይል ማሰራጫ መሠረተ ልማት ያልተዘረጋ መሆኑንም ግልጽ ነው።
የመንግሥት የኢነርጂ ስትራቴጂ፣ በ2030 ዘጠና በመቶው የኢትዮጵያ ሕዝብ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን እንዲያገኝ ለማስቻል መንግሥት ግብ መያዙን ያብራራል። ይህንኑ የኃይል ማሠራጫ መሠረተ ልማት ችግር ከግምት በማስገባትም፣ አውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቶች ለማስፋፋት የሚያስችል የ156 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ መመደቡን ሰኞ፣ ጳጉሜ 3፣ 2017 ዓ፣ም አስታውቋል።
ኅብረቱ፣ የአገሪቱን የኃይል ማስተላለፊያ መሠረተ ልማቶች በማስፋፋት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የኃይል አቅርቦት እንዲያገኙ እና አገሪቱ እንደ ኬንያ እና ጅቡቲ ላሉ ጎረቤት አገራት ኃይል መሸጥ እንድትችል፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር ተጨማሪ ንግግሮች እያደረገ እንደሚገኝም ገልጧል። አውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ማሠራጫ መሰረተ ልማት አቅም ለማስፋፋት የመደበው የገንዘብ ድጋፍ፣ በአፍሪካ አገራት ውስጥ ከአየር ንብረት ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የቀረጸው “ግሎባል ጌትዌይ” የተሰኘው መርሃግብሩ አካል ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ ኢትዮጵያ ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ የሚውል የኒውኩሌር ኃይል ማመንጫ በቅርቡ የመጀመር እቅድ እንዳላትም በታላቁ ሕዳሴ ግድብ የምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ ይፋ አድርገዋል። ዐቢይ ከቀናት በፊት ከዓለማቀፉ የአቶሚክ ኃይል ኤጄንሲ ኃላፊ ጋር በጽሕፈት ቤታቸው መነጋገራቸው አይዘነጋም።
በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ኢትዮጵያ በ30 ቢሊዮን ዶላር ሜጋ ፕሮጀክቶችን እንደምትጀምርም ዐቢይ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ያስመረቀችው፣ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ወደ ተግባር ከገባ ከአስር ወራት ውስጥ ነው። ለናይል ወንዝ አጠቃቀም አዲስ ሕጋዊና ተቋማዊ ሥርዓትን የሚዘረጋውን ይሄን የትብብር ማዕቀፍ፣ ግብጽ እና ሱዳን ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል። ከቀሪዎቹ አስር የናይል ተፋሰስ አገራት መሪዎች መካከል በግድቡ ምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ የተገኙት፣ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ብቻ ናቸው።
ግብጽ፣ ከግድቡ ጋር በተያያዘ በተፋሰሱ አገራት ላይ ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ እንደምትፍጠር እና ግፋ ሲልም ማስፈራሪያ እንደምትሰነዝር የታወቀ ነው። የበርካታ የተፋሰሱ አገራት መሪዎችም በግድቡ የምረቃ ስነ ሥርዓት ላይ ያልተገኙት፣ ከዚሁ ተጽዕኖ ጋር በተያያዘ እንደሆነ ተገምቷል።
ከወንዙ ተፋሰስ ውጭ ከሆኑ ጎረቤት አገራት፣ የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኦማር ጌሌ እና የሴማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሞሃመድ በስነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል። የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ግድቡ አፍሪካ እጣ ፈንታዋን ራሷ እንደምትወስን ዓይነተኛ ማረጋገጫ መሆኑን በስነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር በበኩላቸው፣ አገራቸው ከሕዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት በቅርቡ ስምምነት እንደምትፈጽም ጠቁመዋል። ሌላኛዋ የክብር እንግዳ የባርቤዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ ሞትሊ ፣ ሕዳሴ ግድብ የታላቁ የዓድዋ ድል ተምሳሌት በምህንድስና ጥበብ ዳግም ተገልጦ የታየበት ነው በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ግድቡን የገነባው የጣሊያኑ ሳሊኒ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ፔትሮ ሳሊኒ ደሞ፣ የግድቡ ግንባታ ፕሮጀክት በዓለም በጣም ደኅንነቱ የተጠበቀ ፕሮጀክት እንደነበር ጠቅሰው፣ ሆኖም በግንባታው ሂደት ውድ የሰዎች ሕይወት እንደተከፈለበት ጠቁመዋል።
ሥራ አስኪያጁ፣ ባለፉት 15 ዓመታት ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ በመንገድ ላይ አደጋዎች እና በሌሎችም ሁኔታዎች 33 ሠራተኞች ሕይወታቸውን አጥተዋል ብለዋል። በሕዳሴ ግድብ ላይ ከተተከሉት የኃይል ማመንጫ ተርባይኖች መካከል የመጀመሪያው ተርባይን ኃይል ማመንጨት የጀመረው፣ በአውሮፓዊያኑ 2022 ነበር። በግድቡ ምረቃ ወቅት ግድቡ ማመንጨት የሚችለው ኤሌክትሪክ ኃይል 5 ሺሕ 150 ሜጋ ዋት መድረሱ ተገልጧል። [ዋዜማ]