ዋዜማ ራዲዮ- በእነ አብዲ ሞሀመድ (አብዲ ኢሌ) መዝገብ ተከሳሽ የሆኑት ወ/ሮ ዘምዘም ሀሰን በማረምያ ቤት ድብደባ እንደደረሰባቸው ለችሎት አቤቱታ አቀረቡ
እኚህን ተከሳሽ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሃኒ ሀሰን አህመዲን በሚል ስም በወንድ ፆታ 43ኛ ተከሳሽ አድርጎ አቅርቧቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሆኖም ተከሳሽ መታወቅያ እና ስለማንነታቸው የሚገልጽ የተለያዩ ማስረጃዎችን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በማቅረብ ፆታቸው ሴት ስለመሆኑ ቀርበው ከማስረዳት ባለፍ ስማቸው ዘምዘም ሀሰን መሆኑን እና ክሱ እንደማይመለከታቸው ከዚህ ቀደም በነበረው ቀጠሮ አስረድተው ነበር፡፡
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በእኚህ ተከሳሽ፣ በሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዝዳንት አብዲ ሞሀመድ እና ሌሎች 45 ግለሰቦች ላይ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ልክ የዛሬ አመት ከሰኔ 10 ጀምሮ በተለያዩ ስብሰባዎች እና heego waaheegan በሚል በፌስቡክ ድህረ ገፅ በኦሮሞ ወታደሮች ተወረናል፣ የኦሮሞ ተወላጆች መሬታችንን ለቀው መውጣት አለባቸው፣ ነዳጃችንን መሬታችንን እና ወርቃችንን በጉልበት ሊወስዱብን ነው ፣የሶማሌ ተወላጆች ዛሬ ደማችሁ ሊፈላ ይገባል የሚል ቅስቀሳ በማድረግ እና በጦር መሳርያ በመታገዝ ከሀምሌ 26-30 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለጠፋው የ59 ሰዎች ህይወት በርካታ አብያተ ክርስትያናት መቃጠል እና ለበርካታ ሴት ልጆች መደፈር ጋር ተያይዞ የተፈፀሙ ወንጀሎች ላይ እጃቸው አለበት ሲል ክስ መመስረቱ ይታወሳል፡፡
በወ/ሮ ዘምዘም ላይ ደግሞ “ተከሳሽ ሃኒ ሐሰን ሀምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በጅግጅጋ ከተማ ላይ ለጊዜው ስማቸው በውል ተለይቶ ያልታወቁ ብዛት ያላቸው የሄጎ አባላቶችን 13ኛ ተከሳሽ ከ መሀመድ አህመድ /መሀመድ ድሬ/ ጋር በመሆን እየመራ ይዞ በመምጣት በከተማው የሚገኘውን ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን በእሳት ሲያቃጥልና የሄጎ አባላቶችም እንዲያቃጥሉ እንዲሁም የተለያዩ ንብረቶች እንዲዘረፉና እንዲያወድሙ ትዕዛዝ በመስጠት የተሳተፈ” ሲል አቃቤ ህግ በክስ መዝገቡ ገልፆ ነበር፡፡
የተከሳሽን ማንነት የሚገልፁ ማስረጃዎችን የተመለከተው ችሎቱ አቃቤ ህግ ምላሽ እንዲሰጥበት የጠየቀ ሲሆን አቃቤ ህግም ስማቸው ሌላ ቢሆንም በወንጀል ድርጊቱ የምንፈልጋቸው ግለሰብ ራሳቸው ናቸው ሲል ምላሽ ሰጥቶ ነበር፡፡
ችሎቱ ይህን ተከትሎ በወንጀል የሚፈለጉት ገለሰብ እራሳቸው ናቸው ካለ የስም ማሻሻያ እንዲያቀርብ ለአቃቤ ህግ ትዕዛዝ ሰጥቶ አቃቤ ህግም የስም ማሻሻያ ብቻ በማድረግ በክሱ ውስጥ በወንድ ፆታ የተገለፁትን የክስ ይዘት ግን እንዳለ አቅርቦ ነበር፡፡
ያንን ሁሉ ማስረጃ ለችሎቱ አቅርቤ አሁንም በዚህ ወንጀል ያውም በወንድ ፆታ መከሰሴ አግባብ አይደለም ያሉት ወ/ሮ ዘምዘም ነፍሰጡር መሆናቸውን ለችሎቱ በመግለፅ በተደጋጋሚ በማረምየ ቤት አብረዋቸው የታሰሩ ታራሚዎች ድብደባ እያደረሱባቸው እንደሆነ አቤቱታቸውን ለችሎቱ አቅርበዋል፡፡
ይሁን እንጂ ተከሳሽ አቤቱታቸውን በጠበቃቸው አማካኝነት በፅሁፍ እንዲያቀርቡ ነው ችሎቱ ትዕዛዝ የሰጠው፡፡
በዛሬው ችሎት በመዝገቡ የታከተቱ ነገር ግን በአድራሻቸው ፖሊስ ፈል ያጣቸው እና የጋዜጣ ጥሪ የተደረገባቸው 6 ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤቱ ባቀረበው ጥሪ መሰረት አለመቅረባቸው ከተረጋገጠ በኋላ የተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከ12 አመት በላይ የሚያስቀጣ በመሆኑ ጉዳያቸው በሌሉበት መታየት የሚችል መሆኑን በማስረዳት በሌሉበት ይታይ ሲል ወስኗል፡፡
በዚህ መዝገብ እስካሁን ከ47 ተከሳሾች 26ቱ በቁጥጥር ስር አልዋሉም፡፡