ENDF-FILE

ዋዜማ-በቅርቡ ለሶስተኛ ጊዜ ተሻሽሎ የፀደቀው  የአገር መከላከያ ሰራዊት አዋጅ የቀድሞ ሰራዊት አባላትን የጥቅማ ጥቅምና ጡረታ ጥያቄዎች አለመመለሱ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የቀድሞ ሰራዊት አባላት ለዋዜማ ተናግረዋል። 

የመንግስት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ ለሶስተኛ ጊዜ የተሻሻለው የአገር መከላከያ ሰራዊት  አዋጅ በ2011 ዓ.ም. የወጣውን የመከላከያ አዋጅ ቁጥር 1100 እና በ2013 ዓ.ም  እንደገና ተሻሽሎ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1232 አንድ በማድረግ ለሶስተኛ ጊዜ የተዘጋጀው የአገር መከላከያ አዋጅ የቀድሞ ሰራዊት አባላትን በተለይም ከ1983 ዓ.ም በፊት የነበሩ የሰራዊት አባላትን ያገለለና ያላካተተ ሲሉ አባላቱ ቅሬታ ሰንዝረዋል፡፡

በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በጸደቀው ይህ አዋጅ ላይ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተሻሽለዋል ተብለው ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል የጡረታ መውጫ እድሜ አወሳሰንና የጡረታ እድሜ ከማራዘም ጋር በተገናኘ ያሉ ጉዳዮች፣ የሠራዊት መብትና ጥቅማጥቅሞች ፤ የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ጦርነት ሲገጥም የሰራዊት አባል የነበሩትን መልሶ ከመቅጠር ጋር በተገናኘ ስለሚኖር አፈፃፀም፣ ስለብሔራዊ አገልግሎት፣ የሜዳይ አይነቶች የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የሚንስትሮች ምክርቤት ህዳር 3 ቀን 2015 ዓ.ም አጽድቆ ለፓላማው የተላከው ይህ አዋጅ በምክርቤቱ ከመጽደቁ በፊት የምክርቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከባለድርሻ አካለት ጋር ውይይት ለማድረግ በተጠራ ስብሰባ የቀድሞ የሰራዊት አባላት በአዋጁ እንዲካተቱ ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተው ነበር፡፡

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር  በመላው ኢትዮጵያ 295 ቅርንጫፍ ቢሮዎችና እና ወደ አንድ ሚሊዮን አባላት እንዳሉት ዋዜማ ከማህበሩ ያገኘቸው መረጃ ያመላክታል ፡፡ 

በዚህ በፓርላማው በተካሄደው የባለድርሻ አካለት ውይይት ከተነሱ ጭብጦች መካከል በዋናነት የትግል ተሳትፎ ሜዳይ አሰጣጥና ጡረታቸው ያልተጠበቀላቸው የቀድሞ የሰራዊት አባላት በአዋጁ እንዲታይ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

እንደገና ተሸሽሎ በቀረበው አዋጂ አንቀጽ 60 ላይ እንደተብራረው የትግል ተሳትፎ ሜዳይ ባለዘንባባ ሽልማት በኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን ከደርግ ወይንም የኢትዮጵያ ሠራተኞች መንግሥት ጋር ከ1967 እስከ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በነበሩት ጊዜያት በትጥቅ ትግሉ ከአሥር ዓመት ያላነሰ ተሳትፎ ላደረገ ታጋይ የሚሰጥ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ 

በተመሳሳይ የትግል ተሳትፎ ሜደይ ያለዘንባባ  በተመለከተ፤ የአዋጁ አንቀጽ 61 የትግል ተሳትፎ ሜደይ ያለዘንባባ ስለሚሰጥ ሽልማት የሚያብራራ ሲሆን ፣ በዚህ አንቀጽም ‹‹በኢትዮጵያ ሰላምና ዴሞክራሲን ለማስፈን ›› ከደርግ ወይንም የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ መንግሥት ጋር ከ1967 እስከ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. ድረስ በትጥቅ ትግሉ ከአሥር ዓመት በታች ተሳትፎ ላደረገ ታጋይ የሚሰጥ ሽልማት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በፓርላማው ተሻሽሎ በጸደቀው በዚህ አዋጅ ውስጥ ከቀድሞ ሰራዊት የተነሳው ቅሬታ ከሜዳይ ሽልማት ባላፈ በደርግ አገዛዝ ዘመን የደርግን አገዛዝ አስወገዶ ስልጣን የተቆናጠጠው የቀድሞው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ስልጣን በያዘ ማግስት ከስራ ያሰናበታቸው  የቀድሞ አገር መከላያ ሰራዊት ያለጡረታ እንዲሰናበቱ በመደረጋቸው አሁን ላይ እንደገና በተሻሻለው አዋጅ እንተዲካተቱና ለአገር በዋሉት ውለታ ልክ ጡረታቸው እንዲጠበቅ የሚል አንቀጽ አለመካተቱ ነው፡፡

ከወራት በፊት በረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት በተደረገበት ወቅት የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ አብን የፓርላማ አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሠራዊት ድጋፍና ልማት ማኅበር ተወካዮችና ሌሎችም በቀደሙት ጊዜያት በአራቱም አቅጣጫ የአገርን ድንበርን ያሰከበሩ የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላትን ግምት ውስጥ ያላስገባ አዋጂ በመሆኑ ረቂቁ እንደገና ታይቶ የቀድሞ ሰራዊቱ የሚካተቱበትና ጥቅማቸውም የሚጠበቅበት መንገድ እንዲፈጠር ጠይቀው ነበር፡፡ 

በወቅቱ በረቂቁ ላይ ማብራሪያ የሰጡት የመከላከያ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ማርታ ሉጂ ከ1967 እስከ 1983 በሚል የአንድ የመንግሥት ሥርዓትን ብቻ ያካተተ ሆኖ የቀረበው ረቂቅ በድጋሚ ታይቶ እንደሚሻሻል ተናግረው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻም ውይይት ተደርጎበት እና ማስተካከያ ተደርጎበት የመጣው አዋጅ የቀድሞ ሰራዊትን ጥያቄ አልመለሰም፡፡ 

ሚያዚያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በነበረው የምክርቤቱ መደበኛ ስብሰባ አቶ አበረ አዳሙ የተባሉ የምክርቤቱ አባላት ይህንኑን አዋጅ የቀድሞ ሰራዊት ጥያቄ ያልመለሰ መሆኑን በማንሳት የቀድሞ ሰራዊት አባላት የሶማሌ ወራሪ ሃይል 700 ኪሎሜተር ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ አገር በወረረበት ሰዓት ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ እንዲሁም ቤተሰባቸው የተበተነ የሰራዊት አባላትን እውቅና አለመስጠቱ  በጽኑ ሊታስበበት ይገባል ሲሉ አንስተዋል፡፡ አክለውም ይህን አዋጅ ምክርቤቱ አጽድቆ ከሄደ በታሪክ ተወቃሽ ይሆናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይሁን እንጂ በስተመጨረሻ አዋጁ የተነሳው ማስተካከያ ሳይገባበት በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡

ዋዜማ የተነሳውን ቅሬታ በተመለከተ ያነጋገረቻቸው የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት የድጋፍና ልማት ማህበር   ፕሬዚደንት አምሳ አለቃ ብርሃኑ አማረ፣ አዋጁ ሲወጣ እንደ ባለድርሻና እንደሚመለከተው አካል ተቋማቸው በደብዳቤ ተጠርቶ በረቂቁ ላይ ሁለት ጊዜ ውይይት መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም አዋጁ ጥሩና መልካም  እሳቤዎችን አካቶ የተዘጋጀ  ቢሆንም በአዋጁ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊትን ያላካተተ መሆኑ አባለቱን  እንዳስከፋቸው ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት ወደ ግንባር ሄደው የተዋጉ የሞቱና አካላቸው የጎደለ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ስለመኖራቸው የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ እነዚህ የሰራዊት አባላት በቀደሙት ዘመናት ለአገር የተዋጉ ነገር ግን አሁን ላይ ህክምና እና ጡረታ እንደማይቆረጥላቸው ገልጸዋል፡፡ 

‹‹ ኢትዮጵያ በፈጣሪም ዘንድ እንድታርፍና መሪዎቿ ስኬታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ የዚህ ሰራዊት እንባ መጠረግ እና መታበስ አለበት፤ የዚህን ሰራዊት አንባ አለማበስ ኢትዮጵያንም ሆነ መሪዎቿን ዋጋ ያስከፍላል›› ብለዋል፡፡

ወርሃዊ ጦረታ እንዲከበርላቸው የሚጠይቁት የቀድሞ ሰራዊት አባላት ለመንግስት አካላት ጥያቄ አቅርበው ከሆነ ዋዜማ የጠየቀቻቸው ፕሬዚዳንቱ ማህበሩ ከተቋቋመ ጀምሮ ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት፣ ለጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ፣ የመካላከያ ሚንስትርን ጨምሮ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ ቢጠየቁም የሚሰጠው መልስ ግን “ይታያል” የሚል ብቻ መሆኑን እንስተው መልስ ለማግኘት በትዕግስት እየተጠባበቁ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በተመሳሳይ ዋዜማ በስልክ ያነጋገራቸው የማህበሩ የስራ አስፈጻሚ አባል መቶ አለቃ ታሪኩ በቀለ፤ እንደባለድርሻ አካል በረቂቁ አዋጅ ውይይት ላይ ተሳትፈውና ተወያይተው የነበረ መሆኑን ገልጸው፤ ‹‹አሁን ላይ የሆነው ግን እኛን የለየ፤ ያገለለና የከፈልነውን ዋጋ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገባ ነው›› ብለዋል፡፡ [ዋዜማ]