የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ባለፉት ቀናት ባደረጉት ስብሰባ በግብርና፣ በውጪ ንግድ በተለይም ኢኮኖሚውን በማዘመን “የተሳካና ከፍያለ ውጤት አስመዝግበናል” ብለዋል። የፓርቲው ስኬት ተብሎ ከቀረበው ውስጥ በሀገሪቱ የተረጂዎችን ቁጥር ከ27ሚሊየን ወደ 3 ሚሊየን ዝቅ ማድረግ መቻሉ ነው። የመንግስታቱ ድርጅት የቅርብ ሪፖርት በበኩሉ በሀገሪቱ 22 ሚሊየን ተረጂዎች እንዳሉ ይናገራል። ዝርዝሩን አንብቡት

Adem Farah- Photo credit FMC

ዋዜማ- ገዥው ብልጽግና ፓርቲ፣ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የምግብ እርዳታ ተረጂዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን አስታውቋል።

ፓርቲው ይህን ያለው፣ የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ አስመልክቶ ያደረገውን ግምገማ እና ያሳለፋቸው ውሳኔዎች አስመልክተው የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው።

በ2013 ዓ፣ም በአገሪቱ የእለት ደራሽ የምግብ እርዳታ ተረጂ የነበሩ ሰዎች 27 ሚሊዮን እንደነበሩ የጠቀሱት አደም፣ ባሁኑ ወቅት የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ወደ 3 ሚሊዮን ገደማ ወርዷል ብለዋል።

አደም የምግብ እርዳታ ተረጂዎች ቁጥር ለመቀነሱ በዋናነት ሦስት ምክንያቶችን ዘርዝረዋል። አደም፣ የምግብ እርዳታ ተረጂዎች ቁጥር በዚህ ደረጃ እንዲቀንስ ያስቻለው አንዱ ምክንያት፣ የምግብ እርዳታ የማይገባቸውን ሰዎች የማጥራት ስራ ስለተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። ሆኖም የምግብ እርዳታ ሊያገኙ የማይገባቸው ተብለው ከእርዳታ ተቀባይነት የተቀነሱትን ሰዎች ብዛት አደም በማብራሪያቸው ላይ አልጠቀሱም።

አደም ለምግብ እርዳታ ተረጂዎች ቁጥር መቀነስ በሁለተኛ ደረጃ የጠቀሱት፣ ተረጂዎችን ከተለያዩ የልማት መርሃ ግብሮች ጋር በማስተሳሰር ጥሪት አፍርተው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ተችሏል የሚለውን ነው።

አደም በሦስተኛ ደረጃ፣ በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸው የምግብ እርዳታ ተረጂዎች ቁጥር እንዲቀንስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቅሰዋል። ሆኖም በየክልሉ ምን ያህል ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንደተመለሱና በዚህም ምክንያት ከምግብ እርዳታ ተቀባይነት እንደወጡ አደም አልገለጡም።

መንግሥት ሰብዓዊ ድጋፎችን በራሱ አቅም ለማቅረብ ጠንካራ ስራ እንደሰራም በዚህ ማብራሪያ ላይ ተገልጧል። መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት የምግብ እርዳታ ፈላጊው ሕዝብ በ86 በመቶ እንደቀነሰ ካሁን ቀደምም ገልጦ ነበር።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ይህን ይበሉ እንጅ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከጥቂት ወራት በፊት ባወጣው መረጃ ግን፣ 10 ሚሊዮን ሕዝብ ለርሃብና ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደተጋለጠና ከዚህ ውስጥ ሦስት ሚሊዮኑ በግጭትና በአየር ንብረት ለውጥ የተፈናቀሉ መሆናቸው ገልጦ እንደነበር አይዘነጋም።

በመላ አገሪቱ 4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ነፍሰ ጡሮች እና ጡት አጥቢ እናቶች የተመጣጠነ የምግብ ድጋፍ የሚፈልጉ መሆናቸውን ጭምር የጠቀሰው ድርጅቱ፣ ሆኖም በገንዘብ እጥረት ሳቢያ በአገሪቱ የምግብ እርዳታ ድጋፉን ሲያቀርብ የቆየው በዋናነት ለተፈናቃዮች እና ከፍተኛ የምግብ እጥረት ለገጠማቸው ሰዎች ብቻ እንደሆነ ገልጦ ነበር።

በትግራይ ክልል ብቻ እስከ ጥር ወር 2018 ዓ፣ም ድረስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የክልሉ ተረጅዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባለፈው ሐምሌ መግለጡ አይዘነጋም።

የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ የዓለም የጤና ድርጅትና ሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶች ሐምሌ ገደማ ባወጡት ሪፖርት ደሞ፣ በዓለም ላይ ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት የተጋለጠ በርካታ ሕዝብ አላቸው በማለት ከጠቀሷቸው አምስት አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያን ናት። ሪፖርቱ፣ ባሁኑ ወቅት 22 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ለከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጦት ተጋልጠው እንደሚገኙም ገልጧል።

ብልጽግና ፓርቲ፣ የአገሪቱን የሰብል ምርት ሁኔታ መገምገሙንም አደም በማብራሪያቸው ላይ ገልጸዋል። አገሪቱ በ2010 ዓ፣ም በዓመት ታመርተው የነበረው የሰብል ምርት 306 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር የጠቀሱት አደም፣ በ2017 ዓ፣ም ግን መንግሥት የአገሪቱን ዓመታዊ የሰብል ምርት ወደ 1 ነጥብ 57 ቢሊዮን ኩንታል ማሳደግ እንደቻለ ተናግረዋል።

ይህ የሰብል ምርት እድገት፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በአምስት እጥፍ ማደጉን እንደሚያሳይ እና የዚህ የሰብል ምርት እድገት ተጠቃሚ የሆኑት አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች መሆናቸውን አደም አውስተዋል።

መንግሥት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 480 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ታክስ መሰብሰቡን እና አገሪቱ በ2018 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለውጭ ገበያ ካቀረበቻቸው ሸቀጣ ሸቀጦች 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቷንም አደም ተናግረዋል።

አደም በዚሁ ማብራሪያቸው፣ ፓርቲው በሥነ ምግባር ጉድለት እና በሥራ አፈጻጸም ድክመት በገመገማቸው ከ8 ሺሕ 600 በላይ በሚሆኑ አባላቱ ላይ የተያዩ የዲስፕሊን ርምጃዎች መውሠዱንም ተናግረዋል። ፓርቲው በአባላቱ ላይ የወሰዳቸው እርምጃዎች፣ አመራሮችን ከኃላፊነት ማንሳትን ጀምሮ ወደ ተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ማሸጋሸግን ያካተተ መሆኑን አደም ተናግረዋል።

አደም፣ ፓርቲው፣ ላለፉት ሦስት ወራት ተቋማዊ አቅሙን የሚያጠናክሩ የውስጠ ፓርቲ ሥራዎችን መስራቱን ገልጸዋል። ይህንኑ ተከትሎ፣ የተለያዩ ክልሎች በርካታ የክልል ባለስልጣናትን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን ወይም ማሸጋሸጋቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። እስካሁን አመራሮችን ካነሱት እና ካሸጋሸጉት የክልል መንግሥታት መካከል፣ በተነሱ እና በተሸጋሸጉ አመራሮች ብዛት ቀዳሚውን ቦታ የያዘው በግጭት ውስጥ የሚገኘው አማራ ክልል ነው።

የአማራ ክልላዊ መንግሥት ርዕስ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ በአመራር ብቃታቸው፣ በሥራ ልምዳቸው፣ በትምህርት ዝግጅታቸው እና በመልካም ሥነ ምግባራቸው የተመረጡ 35 አዳዲስ የቢሮ ሃላፊዎችን የሾሙ ሲሆን፣ ነባር ሃላፊዎችን ደሞ ወደ ሌሎች የሥልጣንና ሃላፊነት ቦታዎች ማዛወራቸውን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥትም፣ የአመራር አሠጣጥ ውጤታማነትን፣ መልካም ሥነ ምግባርን እና የሥራ ዝግጁነትን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ 15 አዳዲስ አመራሮችን እንደሾመ እና እንዳሸጋሸገ አስታውቋል።

የጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት፣ 66 አመራሮችን የሾመ ወይም ያሸጋሸገ ሲሆን፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት በበከሉ በ11 የክልሉ ቢሮዎች ላይ አዲስ የአመራር ሹመት እና ሽግሽግ ማድረጉን ገልጧል። [ዋዜማ]