ዋዜማ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ አዲስ የገንዘብ ፖሊሲን መተግበር ጀምሬያለሁ ባለ በሁለተኛው ቀን ባደረገው የሰነዶች የጨረታ ጨረታ ሽያጭ(open market operation) 19.9 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው የሰነድ ሽያጭ ማድረጉን አስታወቀ።

በሰነድ ጨረታውም 16 ተሳታፊ ባንኮች የተካፈሉ ሲሆን ባንኩ ባቀረበው የ15 በመቶ ወለድ ሰነዶቹ መሸጣቸውን ማወቅ ተችሏል።የሰነዶቹ ማብቂያ ጊዜም 15 ቀን ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ማክሰኞ ሀምሌ 2 ቀን 2016 አ.ም ይፋ ባደረጉት ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ ላይ ፣ ብሄራዊ ባንኩ የገንዘብ ፖሊሲ ነክ ጨረታን ያካሂዳል ብለዋል። ይህም በባንክ ስርአቱ ውስጥ ያለ አግባብ የተከማቸ ገንዘብን ለመሰበሰብ ወይንም ወደ ባንክ ስርአቱ ተጨማሪ ገንዘብ ለመልቀቅ እንደሚጠቀምበት የማዕከላዊ ባንኩ ገዥ ተናግረዋል። እንዲህ አይነት በማዕከላዊ ባንኮች የሚደረጉ የሰነድ ጨረታዎች የዋጋ ንረት ሀገራትን ሲያስቸግር ገንዘብን ከገበያ ሰብስቦ ዋጋን ለማረጋጋት ፣በተቃራኒው የኢኮኖሚ መፋዘዝ ሲኖር ደግሞ ተጨማሪ ገንዘብን ወደ ገበያ በማስገባት ኢኮኖሚን ለማነቃቃት ያግዛሉ ተብሎ ይታመናል።

በዛሬው እለትም ብሄራዊ ባንክ ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ ያስችለኛል ያለውን የሰነድ ጨረታን በ15 በመቶ ወለድ በመሸጥ 19.9 ቢሊየን ብርን መሰብሰብ መቻሉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉት የገንዘብ ፖሊሲ ማዕከላዊ ባንኩን ከዚህ ቀደም ከነበረ ተግባሩ ይልቅ ይበልጥ ወደ አለም አቀፍ ተሞክሮ የሚያስጠጋው ነው በሚል በብዙዎች ዘንድ አስተያየት አሰጥቶታል። ባንኩ ለመጀመርያ ጊዜ በወለድ ተመን ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲን እከተላለሁ ማለቱ ነው በዋነኝነት ወደ አዲስ ምእራፍ ተሸጋገሯል ያስባለው።

ገዥው ማሞ ምህረቱ ለመጀመርያ ጊዜም የባንኩ ወለድ 15 በመቶ ይሆናልም ብለው ተናግረው ነበር።ማዕከላዊ ባንኩ ከዚህ ቀደም የዋጋ ንረትን ለመግታት በሚከተለው የገንዘብ ፖሊሲ ወለድ ተኮር የሆነ የገንዘብ ፖሊሲን ከመከተል ይልቅ የተለያዩ አሰራሮችን ሲተገብር ቆይቷል። ለአብነትም ባለፈው አመት ባንኩ የሀገሪቱ የዋጋ ንረት ከፍተኛ መሆኑን ሲያምን የሀገሪቱ ንግድ ባንኮች በ2016 አ.ም  የሚሰጡት ብድር 2015 አ.ም ከሰጡት ከ14 በመቶ በላይ እድገት እንዳይኖረው አዟል።

መንግሰትም ከብሄራዊ ባንክ የሚወስደው ቀጥታ ብድር 2015 አ.ም ላይ ከወሰደው አንድ ሶስተኛውን ብቻ እንዲሆን አድርጓል።በተመሳሳይም ባንኮች ገንዘብ ሲቸግራቸው ከብሔራዊ ባንክ የሚበደሩበትን የወለድ ምጣኔ ወደ ከ16 በመቶ ወደ 18 በመቶም አሳድጎት ነበር።

ማዕከላዊ ባንኩ በወቅቱ የወሰዳቸው እርምጃዎች ሲታዩም በወለድ ተመን ላይ ከተመሰረተ የገንዘብ ፖሊሲ ይልቅ ፣ የወለድ ተመንንም የተለያዩ ገደቦችን በማስቀመጥ ቅልቅል የሆነ የገንዘብ ፖሊሲን ይከተል ነበር። አሁን ብሔራዊ ባንኩ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ያግዘኛል ያላቸውን እርምጃዎች ለመውሰድ በወለድ ተመን ላይ በብዛት አተኩሯል።

በዚህ በባንክ ስርአቱ ውስጥ አለ ብሎ ያሰበውን ትርፍ ገንዘብ ለመሰብሰብ እና የዋጋ ንረት አንዱ ምክንያት እንደሆነ የሚጠቀስ የገንዘብ መብዛትን ለመቀነስ በዛሬው ዕለት ባወጣው የሰነዶች ጨረታ 19.9 ቢሊየን ብር ከ16 ባንኮች ሰብስቧል። ተሳታፊ ባንኮችም ለገዙት ቦንድ 15 በመቶ ወለድ ታስቦላቸው ሐምሌ 18 ቀን 2016 አ.ም ይመለስላቸውና ቀጣይ ደግሞ ሁለተኛው ጨረታ የሚወጣ ይሆናል።

አሁን ላይ የሰነዶቹ ጨረታ ለጊዜው ያተኮረው ትርፍ ብርን ከገበያ መሰብሰብ ላይ ነው።ባንኩ ዛሬ የጀመረው የሰነዶች ጨረታ(open market operation) ግን ትርፍ ገንዘብን ከገበያ መሰብሰብ ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን ኢኮኖሚውን ማነቃቃት ሲያስፈልግ ወደ ገበያው ተጨማሪ ብርን ማስገባትን የሚጨምርነው። ምናልባትም የሀገሪቱ የዋጋ ንረት አሁን ወርዷል ከተባለበት 19 በመቶ ምጣኔ በይበልጥ ከ10 በመቶ በታች ሆኖ ብሔራዊ ባንክ ኢላማዬ ነው ያለው እቅድ ላይ ሳይደርስ ገንዘብን ወደ ገበያ የመልቀቁ ጨረታ ላይታይ ቢችልም በሀገሪቱ ሊተገበር የሚችል የገንዘብ ፖሊሲ ሆኖ የሚጠበቅ ይሆናል።

ሆኖም ከሰሞኑ ይፋ የተደረገው የገንዘብ ፖሊሲ ብዙ ሀገራት የዋጋ ንረትን ከመቀነስ አንጻር ውጤታማ የሆኑበት መሆኑን ብዙ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ቢያምኑም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከፋይናንስ ስርአቱ ውጭ በርካታ ገንዘብ የሚንቀሳቀስባቸው ሀገራት ውስጥ የዚህ ፖሊሲ ውጤታማነት ጥርጣሬ ውስጥ እንደሚገባ አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የኢኮኖሚ ባለሙያ ለዋዜማ ተናግረዋል። ባለሙያው እንዳሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ከፋይናንስ ስርአቱ ውጭ የሆነ ገንዘብን ወደ ፋይናንስ ስርአቱ ይበልጥ ማስገባት ሲቻል ግን የፖሊሲውን ውጤታማነት ማየት ይቻላል ብለዋል። ለዚህም ይመስላል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ፖሊሲውን ይፋ ሲያደርጉ ፣ አዲሱ ፖሊሲ የሚያመጣው ለውጥ ዝግ ያለ ከሆነ ማዕከላዊ ባንኩ ነባሮቹን ፖሊሲዎች በአማራጭነት መጠቀም ይቀጥላል ያሉት። [ዋዜማ]