ዋዜማ ራዲዮ- በሀገሪቱ ያሉ የመንግስትና የግል የንግድ ባንኮች የተበላሸ የብድር ምጣኔ አምስት በመቶ እያለፈ በመምጣቱ ማናቸውንም በብድር የተያዘ ንብረትና መያዣ ለሀራጅ እንዳያቀርቡ ብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ መስጠቱን ለዋዜማ የደረሰ መረጃ ያመለክታል። ብሄራዊ ባንክ አዲስ የብድር ማራዘሚያ መመሪያ ሊያወጣ እየተዘጋጀ መሆኑም ተሰምቷል።
ቀደም ባለው ጊዜ የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከ15 በመቶ ማለፍ ሳይገባው 51.6 በመቶ ወይም ሀያ ቢሊየን ብር በመድረሱ የሀገሪቱን የፋይናንስ እንቅስቃሴ ቀውስ ውስጥ መክተቱ ይታወሳል።
አሁን የንግድ ባንኮች ላይ ያንዣበበው አደጋ ያሳሰበው መንግስት ሀራጅ ለማውጣት የተዘጋጃችሁት ንብረት ካለ ሀራጁን አቁሙት የሚል ትእዛዝ አስተላልፎላቸዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ጥቅምት 20 ለሁሉም ንግድ ባንኮች አንድ ደብዳቤን ጽፏል። ደብዳቤውም : ብሄራዊ ባንክ ከብድር ማራዘም ጋር በተያያዘ በስራ ላይ ያለውን መመሪያ የማሻሻል ሂደት ተጠናቆ የሚሻሻለው መመሪያ ለባንኮች እስኪደርስ በዋስትና የተያዙ ንብረቶች ላይ የተጀመረው የፎርክሎዠር ወይንም የሀራጅ ሂደት ካለ እንዲቋረጥ አሳስቧል።ደብዳቤው ሲቀጥልም ተለዋጭ መመሪያ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ እስኪመጣ ድረስ በተሻሻለው መመሪያ መሰረት ተግባራዊ እንዲደረግ አዟል ።
የዚህ አዲስ መመሪያ መውጣት ለተበዳሪዎች መልካም ቢሆንም የመመሪያው ይዘት ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ያሉበትን የተበላሸ ብድር ምጣኔ ከተቀመጠው የአምስት በመቶ ገደብ እያለፈ በመሆኑ ሳቢያ መመሪያው ማስፈለጉን ምክር የጠየቅናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ ።
በኢትዮጵያ የንግድ ባንኮች አሁን እየተጠቀሙበት ያለው የብድር አመላለስ መመሪያ ለተበዳሪዎች እጅግ አስቸጋሪና መዘዙም ለባንኮቹ እየተረፈ መጥቷል። እስካሁን ብሄራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች አውጥቶ ስራ ላይ ያለው መመሪያ አንድ ተበዳሪ ብድር ከወሰደ በሁዋላ ብድሩን መመለስ መጀመር ካለበት ጊዜ 90 ቀን ካለፈ የሶስት በመቶ የወለድ ቅጣት ይጥልበታል። ተበዳሪው በዚህ ቅጣት አልፎ ወደ ትክክለኛው የብድር አመላለስ አካሄድ ካልገባም በህጋዊ መንገድ ወደ ተበዳሪው ለብድሩ ማስያዣ ያደረገውን ንብረት ወደ ሀራጅ ወይንም ፎርክሎዠር ማውጣት ይመራል።
የብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘሙ ደግሞ ለተበዳሪዎች እጅግ አስጨናቂና በተለይ ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተበዳሪዎች የማይመጥን መሆኑ የሚታወቅ ነው።
አንድ ተበዳሪ ብድሩን መመለስ ከሚችልበት ቀን መመለስ አቅቶት 90 ቀናት ካለፈው የመጀመርያ ዙር ማራዘሚያን ማግኘት ከፈለገ በቅድሚያ የመጀመርያ ዙር የብድር ክፍያውን እስከነወለዱ ማጠናቀቅ መቻል አለበት።ይሄ ብድር መክፈል ላቃተው ተበዳሪ የክፍያ ማራዘሚያን የሚያገኝበትን መንገድ በእጅጉ ያጠበበ ነው።
ሁለተኛ የብድር ክፍያ ማራዘሚያን ለማግኘት ደግሞ ከዚህም የባሰ ከባድ መሆኑን ባለሀብቶች በተለያዩ መድረኮች ላይ እያነሱ ሲያማርሩ የሚሰማ ጉዳይ ነው።አንድ ተበዳሪ ሁለተኛ የብድር ማራዘሚያን ማግኘት ከፈለገ የቀሪ ብድሩን 20 በመቶ በቅድሚያ ለአበዳሪው ባንክ መመለስ ይጠበቅበታል። 100 ሚሊየን ብር ቀሪ ብድር ያለበት ተበዳሪ ብድሩ እንዲራዘምለት 20 ሚሊየን ብር መክፈል ይጠበቅበታ ።
ምርትን አምርቶና አገልግሎትን ሰጥቶ ብድርን ለመክፈል በቂ የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማይገኝበት ሀገር : ጥሬ እቃን ከውጭ ለማምጣት የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት በርካታ ወራት ወረፋ በሚጠበቅባት ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት የብድር መመሪያን ተግባራዊ ማድረግ እጅግ የማይቻል መሆኑ በተግባር መታየቱም ተነስቷል። በዚህ መመሪያ መሰረትም በርካታ የባንክ ተበዳሪዎች ችግር ውስጥ እየገቡ ብድራቸው ከተበላሹት ተርታ ውስጥ እየገባም ባንኮችም ወደ ሀራጅ የሚሄዱበትን እድል እያሰፋው ነው።
ኢትዮጵያ ላለፉት አመታት ባለፈችበት የፖሊቲካ ቀውስ ምክንያት በየስፍራው በርካታ አምራች ፋብሪካዎች መውደማቸው ይታወቃል።የወደሙት ፋብሪካዎች በብድር የተሰሩ እንደመሆናቸው ጫናው በፋይናንስ ስርአቱ ላይ ጎልቶ እንደታየ ማመላከቻዎች አሉ። የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ መስከረም ወር መጨረሻ ላይ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የአመቱን የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ባሰሙበት ንግግራቸው የባንኮችን የተበላሸ ብድር ምጣኔ ማስተካከል የመንግስት የዚህ አመት ትኩረት ነው ማለታቸው የሚታወቅ ነው። ይህም የሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ አደጋ ማመላከቻ ነው።
ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ያሉ የንግድ ባንኮች አብዛኞቹ የተበላሸ ብድር ምጣኔ በብሄራዊ ባንክ ከተቀመጠላቸው መስፈርት እያለፈ ነው። ብሄራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች የተበላሸ የብድር ምጣኔ ካበደሩት አጠቃላይ ገንዘብ ከአምስት በመቶ እንዳይበልጥ ያዛል። ለልማት ባንክም በተለየ ሁኔታ የተበላሸ ብድር ምጣኔው ከ15 በመቶ እንዳይበልጥ ተቀምጦለታል : ሆኖም የልማት ባንኩ የተበላሸ ብድር ምጣኔ 51.6 በመቶ መድረሱን ዋዜማ ራዲዮ በቅርቡ መዘገቧ ይታወቃል።
ከሰሞኑ ከሀገሪቱ ንግድ ባንኮች እየተሰማ ያለው ነገር ደግሞ የተበላሸ የብድር ምጣኔያቸው ከተቀመጠው የአምስት በመቶ ምጣኔ እያለፈ መምጣቱን ነው። ዋዜማ ራዲዮ እንዳረጋገጠችው በብድር አሰባሰቡ የተሻለ የተባለ አንድ ባንክ ራሱ የተበላሸ የብድር ምጣኔው አምስት በመቶን ተሻግሯል።
ብሄራዊ ባንኩ ሲጠቀምበት የነበረው መመሪያም ለዚሁ የተበላሸ ብድር ምጣኔ ማደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉም ታውቋል።ስለዚህም ነው ማእከላዊ ባንኩ አዲስ የብድር ማራዘሚያ መመሪያን አወጣለሁ ለመያዣነት የያዛችሁትን ንብረት ሀራጅ ልታወጡ ካሰባችሁም አቁሙ ሲል ለንግድ ባንኮች ትእዛዝን ያስተላለፈው።
አዲስ የሚወጣው መመሪያም ለተበዳሪዎች እፎይታን የሚሰጥ ሆኖ ከተገኘ የባንኮቹን የተበላሸ ብድር ምጣኔን የማስተካከል እድል የሚሰጥ ሊሆን ይችላል። ይህም መመሪያ በቅርቡ ለንግድ ባንኮች ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ ያሉ ንግድ ባንኮች በቀደሙት አመታት የተበላሸ ብድር ምጣኔያቸው በአማካይ ከሶስት በመቶ አያልፍም ነበር። ይህ የሆነው ግን ባንኮቹ የተሻለ አፈጻጸም ስላላቸው ሳይሆን የሚሰጡት ብድር ቶሎ ትርፋማ የሆኑ ዘርፎች ላይ ስለሚያተኩርም ነው። [ዋዜማ ራዲዮ]