ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የኢትዮጵያ ባንኮች በየወሩ መጨረሻ ከአስቀማጮች እየሰበሰቡ ለመጠባበቂያነት ብሄራዊ ባንክ ከሚያስቀምጡት ገንዘብ የተወሰነውን ቀንሰው ብድርን ማቅረብ እንዲችሉ ፈቀደ።
አዲሱ አሰራር ከሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን በብሄራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ የተፈረመ መመሪያ ለባንኮች መላኩን ዋዜማ ተመልክታለች።
በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ገዥ ሰለሞን ደስታ ለዋዜማ ራዲዮ እንደተናገሩትም እስካሁን ድረስ ንግድ ባንኮች ከሚሰበስቡት ቁጠባ በየወሩ መጨረሻ በአማካይ 10 በመቶውን ብሄራዊ ባንክ ለመጠባበቂያነት እንዲያስቀምጡ ይገደዱ ነበር።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት ግን ከሚሰበስቡት ቁጠባ በየወሩ መጨረሻ በብሄራዊ ባንክ እንዲያስቀምጡ የሚጠየቁት 7 በመቶውን ነው። ሶስት በመቶውን በመደበኛነት ከሚሰጡት ብድር በተጨማሪ ለገበያ ማቅረብ እንደሚችሉም ምክትል ገዥው አስረድተውናል ።
ንግድ ባንኮቹ ከመጠባበቂያቸው ላይ ለተጨማሪ ብድር ማዋል የሚችሉት ከዚህ በሁዋላ በሚሰበስቡት ቁጠባ ላይ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በየወሩ ከሰበሰቡት ቁጠባ 10 በመቶ ለመጠባበቂያነት ሲያስቀምጡ ከነበረው ውስጥ ሰባት በመቶውን በመተው ሶስት በመቶውን ለብድር ማዋል እንደሚችሉም ከምክትል ገዥው አቶ ሰለሞን መረዳት ችለናል።
በዚህ አሰራር ባንኮች ከፍ ያለ ገንዘብ ለብድር ገበያ ለማቅረብ ዕድል ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ብድሩም በጦርነትና ግጭቶች ሳቢያ ለወደሙ ተቋማት ቀርቦ ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ያግዛል ተብሎ ተስፋ እንደሚደረግ ምክትል ገዥው አቶ ሰለሞን ደስታ ለዋዜማ ራዲዮ ገልጸዋል።
ባለፈው አመት ነሀሴ ወር ላይ ነው ብሄራዊ ባንክ በኢኮኖሚው ውስጥ የተፈጠረውን አሳሳቢ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር በሚል ባንኮች በየወሩ ከሚሰበስቡት ቁጠባ በየወሩ መጨረሻ ብሄራዊ ባንክ በመጠባበቂያነት የሚያስቀምጡትን ገንዘብ ከ5 በመቶ ወደ 10 በመቶ ከፍ እንዲል ያደረገው።
በዚህም በብድር መልክ የሚሰራጨውን ገንዘብ መጠን በመቀነስ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ታቅዶ ነበር። ሆኖም በግጭት እና ድርቅ ሳቢያ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ስለበረታ የሚሰጥ ብድር ከፍ እንዲል እንደገና መመሪያው ተከልሶ ወጥቷል።
ብሄራዊ ባንክ ነሀሴ ወር ላይ የባንኮች መጠባበቂያ ተቀማጭ ከፍ እንዲል ሲያዝ ተመዝግቦ የነበረው የዋጋ ንረት 26 በመቶ ነበር። አሁን ደግሞ በየወሩ እየተመዘገበ ያለው የዋጋ ንረት 34 በመቶ አካባቢ ነው። የዋጋ ንረቱ ከፍ ባለ ጊዜ እንደገና ተጨማሪ ብድርን ወደ ገበያው ማሰራጨት ሌላ ዋጋ ንረት ፈጣሪ አይሆንም ወይ ስንል ለብሄራዊ ባንኩ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ጥያቄን አንስተን ነበር። እሳቸው ሲመልሱ “ውሳኔው የዋጋ ንረት ተጽእኖ አያመጣም ማለት አይቻልም።ነገር ግን የሚያመጣው ጥቅም ከጉዳቱ የተሻለ እንደሆነ እናምናለን። የተፈጠረው የዋጋ ንረት አለም አቀፍ ገጽታ ስላለው ኢኮኖሚው በብድር እንዲነቃቃ መደረጉ አለማቀፉ የዋጋ ንረት ሲረጋጋ ተጠቃሚ ያደርገናል።” ብለውናል።
የተቀማጭ ገንዘብ ጣሪያው እንዲወርድ መደረጉ ምናልባት ባንኮች እያጋጠማቸው ያለውን የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዲፈቱ ሊያግዛቸው ይችላል ተብሏል። በተለይ የግል ባንኮች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከፍተኛ መጠን ያለውን ብድር መፍቀድ ከመቸገራቸው በላይ በሚሊየን የሚቆጠር ብር ወጪ ለሚጠይቋቸው ደንበኞች ምላሽ ለመስጠት ቀናትን ሲያስጠብቁ ይስተዋላል።
በቅርቡ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የኢትዮጵያ ባንኮች የሰበሰቡት ቁጠባ ከአንድ ትሪሊየን በላይ እንዳለፈ ያሳያል።ብሄራዊ ባንክ በዚህ አመት ያወጣው የመጨረሻው ህትመት እና የበጀት አመቱ የመጀመርያ ሶስት ወራት የፋይናንስ ዘርፍን አፈጻጸም የሚሳየው ሪፖርት የሀገር ውስጥ ባንኮች በተጠቀሰው ጊዜ 81.7 ቢሊየን ብር ቁጠባ እንደሰበሰቡና 65.3 ቢሊየን ብር ብድር እንደሰጡ ያሳያሉ። [ዋዜማ ራዲዮ]