ዋዜማ ራዲዮ- የቴሌኮም አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ በሚል ስያሜ የተዘጋጀው ሰነድ ኢትዮጵያን በቴሌኮም ዘርፍ ለመሰማራት ለፈለገ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለ ሀብት ክፍት የማድረግን የመንግስትን ፍላጎት ይፋ አድርጓል። ረቂቅ አዋጁ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባለፈው አመት በቴሌኮም ዘርፉ እንዲተገበር ከወሰነው ሰፋ ባለሁኔታ ዘርፉን ለገበያ ክፍት የሚያደርግ ነው። ቀድሞ ተነግሮ የነበረው መንግስት የኢትዮ ቴሌኮምን አብላጫ ድርሻ ይዞ ቀሪውን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች ድርሻ የመሸጥ ነበር።
ዋዜማ ራዲዮ የተመለከተችው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያሳየው ግን ሀገሪቱ የቴሌኮም ዘርፏን ሰፋ አድርጋ ለገበያ እንደምትከፍት የሚያሳይ ነው ።በረቂቅ አዋጁም ላይ ፣ በሌላ ህግ የተደነገገ አዋጅ ወይንም ደንብ ቢኖርም ማንኛውም የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብት የቴሌኮም አገልግሎት ፣ የቴሌ ኮሚኒኬሽን ኦፕሬሽን እና የቴሌ ኮሚኒኬሽን ኔትወርክ ባለቤትነት ፍቃድ የማግኘት መብት እንዳለው ተደንግጓል። እስካሁን ለቴሌኮም ዘርፉ ግልጋሎት ላይ የዋሉ የቴሌኮም አዋጅ፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ እና የፖስታ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ህጎች እንዲሻሩም በረቂቅ አዋጁ ላይ ተቀምጧል።
የቴሌኮም ዘርፉን እንዲቆጣጠርም የኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን እንዲቋቋም የሚያደርግ ሰፊ አንቀጾችም በረቂቅ ህጉ ተካቷል።ዋዜማ ራዲዮ ከዚህ ቀደም የቴሌኮም አዋጁ እየተሻሻለ መሆኑን አስመልክቶ እንደዘገበችውም የሚቋቋመው ባለስልጣን ዳጎስ ያሉ ስልጣኖች የሚሰጠው ይሆናል።
በረቂቅ ህጉ መሰረት በርካታ የቴሌኮም ኩባንያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ በመሆኑ ካልተገቡ የገበያ ውድድሮች ከመቆጣጠር አንስቶ ፣የቴሌኮም አገልግሎት ፍቃድን መስጠትና በርካታ ስልጣኖች ተሰጥተውታል። የቴሌ ኮም ዘርፍ ቢሊየን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅሱ ኩባንያዎች ያሉበት በመሆኑ ባለስልጣኑ ጠንካራና ጥቅማ ጥቅሞቻቸው የተጠበቁላቸው ሰራተኞች ሊኖሩት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ረቂቅ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቆ ተግባራዊ ከሆነ የኢትዮጵያን የቴሌ ኮሚኒኬሽን ዘርፍ በብዙ መልኩ የሚያሻሽልና ለሀገሪቱም የውጭ ምንዛሬን በስፋት እንደሚያስገኝ እንዲሁም ነገሩ በጥንቃቄ ከተያዘ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚም መልካም መሆኑን መንግስት ያስረዳል።
አሁን በብቸኝነት አገልግሎት እየሰጠ ያለው ኢትዮ ቴሌኮምም ጠንካራ ውድድር ከፊቱ እንደሚመጣበት ይጠበቃል።
ይህን የመንግስት ውሳኔ አስተዋይነት ይጎድለዋል ሲሉ የሚተቹ ባለሙያዎችም አሉ።