Ethiopian coffee beans
Ethiopian coffee beans

(ዋዜማ ራዲዮ)- የኢትዮጵያን ቡና በዋነኛነት ይሸምታሉ ከሚባሉ ሀገራት መካከል አንዷ በሆነችው ጃፓን የቡና መጠጣት ባህል ባለፉት 40 ዓመታት በከፍተኛ ደረጃ እንዳደገ ይነገራል፡፡ የሻይ አፍቃሪዎችናቸውየሚባሉት ጃፓናውያን አሁን አሁን በሳምንት በነፍስ ወከፍ እስከ 11 ኩባያ ቡና የሚያጣጥሙ ሆነዋል፡፡ በጥራት ላይ ድርድር የማያውቁት ጃፓናውያን ከኢትዮጵያ በሚገዙት ቡና ላይቅሬታ ማቅረብ ከጀመሩ ሰነበቱ፡፡

 

ቻላቸው ታደሰ ቡና የገባበትን አለም አቀፍና ሀገራዊ ፈተና ተመልክቶ ያዘጋጀውን ዘገባ በድምፅ እነሆ፣ አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ።

 የኢትዮጵያ ቡና ጥራት ማሽቆልቆሉን ተከትሎ ሌሎች ገዥ ሀገሮችም በተደጋጋሚ ምሬታቸውን ቢያሰሙም እንደ ጃፓን ያመረረ የለም፡፡ ጃፓን ከስምንት ዓመት በፊት ቡና የተላከበት ጆንያዲዲቲበተሰኘው ፀረተባይ ኬሚካል ተበክሎ ካገኘች ወዲህ የምታስገባውን ምርት ቀንሳለች፡፡

በፈረንጆቹ ሚሊኒየም መባቻ 26,757 ሜትሪክ ቶን ቡና ከኢትዮጵያ ያስገባቸው ጃፓን .. 2011 መጠኑን ወደ 8,030 ሜትሪክ ቶን መቀነሷን ኦል ጃፓን ኮፊ አሶሴሽንየተገኘ መረጃያመለክታል፡፡ በአንጻሩ በቡና አምራችነቷ እምብዛም የማትታወቀው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ታንዛንያ በተመሳሳይ ወቅት ኢትዮጵያ ከላከችው የላቀ 11,067 ሜትሪክ ቶን ቡና ለጃፓን ገበያአቅርባለች፡፡

 የኢትዮጵያን ጉድለት በሌሎች ለማካካስ የሞከረችው ጃፓን የኢትዮጵያ ቡናን ጥራት ለማሻሻል እገዛ የምታደርግበትን መንገድ ማፈላለጓን አልተወችም፡፡ ባለፈው ወር አዲስ አበባበሚገኘው ኤምባሲዋ አማካኝነት የመጀመሪያውን ሀገር ዓቀፍ የቡና ጥራት ውድድር እንዲካሄድ አድርጋለች፡፡

ለጃፓን መንግስት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዋዜማ እንደጠቆሙት ጃፓን ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕም ሊያመጣ የሚችል እና ህዝቧ ከሚጠጣው ቡና ላይየሚጨመር የፋብሪካ ኬሚካል ማምረትን እንደ አንድ አማራጭ እያየችውነው፡፡

 በኢትዮጵያ ቡና ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ቡና አምራች ገበሬዎች እምብዛም የተባይ ማጥፊያ ኬሚካሎችንና ማዳበሪያ ስለማይጠቀሙ ቡናው ተፈጥሯዊ ጣዕሙንእንዲጠብቅ አስችለውታል፡፡ ይህ ግን የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን ማስከተሉ አልቀረም፡፡

 እንደ ጥናቶቹ ግኝት የቡና ምርትና ምርታማነት በሚያሽቆለቁልበት ጊዜ ኬሚካሎቹ ጥቅም ላይ አለመዋላቸው የሚያሳደረው አሉታዊ ተፅዕኖ ጎልቶ ይታያል፡፡ ይህም ቡና አምራቾችየቡናቸውን ተወዳጅ ተፈጥሯዊ ጣዕም ምርታማነትን ከማሳደግ ጋር እያጣጣሙ ለመጓዝ ዘዴ መቀየስ እንዳለባቸው ጠቋሚ ነው፡፡

 ምርታማነትን በእጥፍ መጨመር በሀገር ደረጃ የተያዘ ዕቅድ ነው፡፡ በጣሙን የተለጠጡ ዕቅዶችን በማውጣት የሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግስት በያዝነው ዓመት መገባደጃ ላይ የቡናወጭ ንግድን 260 ሺህ ቶን ለማድረስ ቆርጦ መነሳቱን ይገልፃል፡፡ ለቡና አምራቾች ብድር ማቅረብ፣ ተመራጩን አረቢካ ቡና በውጭ ገበያ በሰፊው ማስተዋወቅ እና የመሳሰሉትንማበረታቻዎች በመጠቀም ዕቅዱን ለማሳካት አልሟል፡፡

 ኢትዮጵያ 1/4 የሚሆነውን የወጭ ንግድ ገቢዋን የምታገኘው ከቡና ሽያጭ ቢሆንም ላለፉት አምስት ዓመታት ከዘርፉ የምታገኘው የውጭ ምንዛሬ አሽቆልቁሎ ነበር፡፡ ሀገሪቱ ..2014/15 ከቡና ወጭ ንግዷ 900 ሚሊዮን ዶላር አስገብታለች፡፡

 ከንግድ ሚንስቴር የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ጀርመን፣ ሳኡዲዓረቢያ፣ ጃፓንና ስዊድን ዋና ዋናዎቹ የኢትዮጵያ ቡና ገዥ ደንበኞች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ቡና 18 በመቶውን የጀርመንየቡና ገበያ እና 16 በመቶውን የሳዑዲ ዓረቢያ የቡና ገበያ መቆጣጠሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 ኢትዮጵያ 2014/15 ያስገባቸው ገቢ ከዚያ ቀደም ከነበረው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 25 በመቶ የጨመረ ቢሆንም ዕድገቱ የተመዘገበው የደቡብ አሜሪካ በተለይም የብራዚል ቡና ምርትበድርቅ ሳቢያ ቅናሽ በማሳየቱ ነው፡፡ እንደ ብራዚል ዓይነት ድርቅን ተክትሎ ከፍ እና ዝቅ የሚለው የዓለም ዓቀፍ የቡና ዋጋ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡

 በዓለም ዓቀፍ የቡና ገበያ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ቡና አምራች ሀገሮች ዋጋ የመተመን አቅማቸው አናሳ መሆኑ ሌላው ችግር ነው፡፡ ዋና ዋና ቡና አምራቾች የሚባሉ ሀገሮች ድሃመሆናቸው እና አምራቾቹ አነስተኛ ገበሬዎች መሆናቸው ሌላው የሚጠቀስ ማነቆ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከምታመርተው ቡና ውስጥ 95 በመቶ የሆነው የሚሸፈነው በአነስተኛ ቡና አምራቾችነው፡፡

 እነዚሁ አነስተኛ አምራቾች የጫካ፣ የጓሮና ከፊል ጫካ ቡና የሚያመርቱ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ የመንግስት ፖሊሲ የግል ባለሃብቶችን የሚያበረታታ ቢሆንም ምርቱን ለገበያ ለማቅረብከአምስት አመት በላይ ስለሚወስድ በግሉ ዘርፍ የተያዙት ሰፋፊ እርሻዎች ምርት ድርሻ ከአምስት በመቶ ንቅንቅ ሊል አልቻለም፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ከገበሬ ማሳ እስከ ዓለም  ዓቀፍ ገበያ ያለው ሰንሰለት የተንዛዛ መሆኑ በዘርፉ ያለ ተጨማሪ ችግር እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ህግ መሰረትከሰፋፊ ቡና አምራቾች ውጭ ያሉት አነስተኛ አምራቾች ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡትን ቡና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት (ETHIOPIAN COMMODITY  EXCHANGE-ECX) ወይምበህጋዊ ህብረት ስራ ማህበራት በኩል እንዲሸጡ ይገደዳሉ፡፡

 አሰራሩ ዓለም ዓቀፍ ቡና ነጋዴ ድርጅቶች ከአነስተኛ ቡና አቀነባባሪዎች ጋር ያደርጉት የነበረውን ቀጥተኛ ንግድ ቆርጦታል፡፡ ኢንተለጀንሲያ የተሰኘው የአሜሪካ ቡና ነጋዴ ድርጅትበበኩሉ “አሰራሩ ሁሉንም የቡና ዝርያዎች እንዲቀላቀሉ ስላደረጋቸው ቡናው የተመረተበትን ትክክለኛ ቦታ ለመለየት አስቸጋሪ አድርጎታልበማለት ያማርራል፡፡

 የቡና ገበያ ሰንሰለቱ በአነስተኛ አምራቾች ገቢ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በቡና  አምራች ጎረቤት ሀገሮችም ጭምር ነው፡፡ የኬንያ አነስተኛ ቡና አምራቾችም በገበያውውስጥ የወሳኝነት ሚና የላቸውም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ምርታቸውን ቡና ለመፈልፈል ህጋዊ ፍቃድ ላላቸው ህብረት ስራ ማህበራት እንዲያስረክቡ ህግ ያስገድዳቸዋል፡፡

 ከአራት ጋሻ  በታች የቡና ማሳ ያላቸው አነስተኛ ገበሬዎችም የቡና መፈልፈያ ፋብሪካ ማቋቁም አይችሉም፡፡ በጠቅላላው በኢትዮጵያም ሆነ በኬንያ ለደላሎች ወይም ወኪሎችየሚከፈለውን ወጭ ጨምሮ የምርት ሂደቱ ብዙ ተወናዮችንና ወጭዎችን ስለሚጠይቅ አነስተኛ ገበሬዎች የልፋታቸውን ዋጋ አያገኙም፡፡

በበለፀጉት ሀገሮች አንድ ስኒ ቡና እስከ አራት ዶላር ድረስ ይሸጣል፡፡ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የሁለት በመቶ ቅናሽ ቢያሳይም ባለፈው መጋቢት ወር ኒውዮርክ ገበያ ላይአንድ ፓውንድ የኢትዮጵያ አረቢካ ቡና አንድ ነጥብ አምስት ዶላር ተሽጧል፡፡ አብዛኛው ኢትዮጵያዊው ቡና አምራች ገበሬ ግን ጠቅላላ የዕለት ገቢው ከአንድ ዶላር በታች ነው፡፡

ከቡና ከሚገኘው ትርፍ ውስጥ ወደ ቡና አምራቾች ኪስ የሚገባው አስር በመቶው ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለዚህም ነው ቡና አምራቾች በዓለም ዓቀፍ ቡና ዋጋ ላይ መደራደርእንዲችሉና ፍትሃዊ የንግድ ስርዓት እንዲሰፍን የነዳጅ አምራች ሀገሮች ድርጅት እንደሆነውኦፔክ” ዓይነት የጋራ ድርጅት እንዲፈጥሩ ተደጋጋሚ ጥሪ የሚቀርበው፡፡

ከሀገራት ባሻገር በቡና ላኪ ድርጅቶች መካከል ስምምነት መጥፋቱና የላኪዎች ማህበራት ደካማ መሆን ለኢፍትሃዊ የንግድ ስርዓት እንደሚያጋልጥ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡በጠቅላላው ፍትሃዊነት የሌለው የዓለም ቡና ንግድ ሰንሰለት ብዙ ቢወራበትም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ጥረው ግረው የሚያመርቱትን አነስተኛ ገበሬዎች ተስፋ የሚያለመልምአዎንታዊ ዓለም ዓቀፍ እርምጃ ግን ጠብ  ሲል አይታይም፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ገበሬዎች የቡና ማሳቸውን ወደ ጫት ማሳ እንዲቀይሩ እንዳስገደዳቸው በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በዓመት ብዙ ጊዜ ምርትየሚሰጠው፣ ከውስብስብ ንግድ ሰንሰለት ነፃ የሆነው አነቃቂው ጫት የበርካታ አነስተኛ ገበሬዎችን ትኩረት መሳብ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

Ethiopian coffee cherry
Ethiopian coffee cherry

በኢትዮጵያ የወጭ ንግድም ላይም ጫት ቡናን መገዳደሩ እንግዳ መሆኑ አብቅቷል፡፡ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት የግማሽ ያህሉ ድርሻ የሚሸፈነው በቡና ቢሆንም በዓለም አቀፍ ገበያያለውን ደረጃ ግን እያጣ መጥቷል፡፡  

 ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መገባደጃ ላይ ለውጭ ገበያ ባቀረበችው ቡና ከዓለም ዘጠነኛ  ደረጃ  ላይ የነበረች ሲሆን በአፍሪካ የነበራትን የመሪነት ቦታ ሰባተኛነትንበተቆናጠጠችው ኡጋንዳ ተነጥቃለች፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብን ዘግይተው በተቀላቀሉት ቬትናምን በመሳሰሉ ሀገሮችም መበለጥ ከጀመረች ቆየች፡፡

 የኢኮኖሚ ዋልታዬነው የምትለው የቡና አቅርቦቷ እንዲህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከነበረበት ሲንሸራተት ሀገሪቱ በሌሎች ምርቶች እንኳ መደገፍ አልቻለችም፡፡ ይባስ ብሎ የዚህ ዓመት አጠቃላይየወጭ ንግዷ አያያዝ አመርቂ እንዳልሆነ በይፋ አውጃለች፡፡  

 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ለፓርላማው ባቀረቡት የስድስት ወራት ስራ  አፈፀፀም ሪፖርትበዚህ የበጀት ዓመት የሀገሪቱ ወጭ ንግድ መቀነሱንናየሀገሪቱ ዕድገትም ዝቅ እንደሚልአስታውቀው ነበር፡፡  በቅርቡ ደግሞ የዓለም ገንዘብ ድርጀት ዓመታዊ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ወደ 4.5 በመቶ ዝቅ እንደሚል አስታውቋል፡፡