• በሁለት ወራት ውስጥ መንግስት በመልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ አዲስ በጀት አዘጋጅቶ ያቀርባል

ዋዜማ ራዲዮ- በመንግስትና በሕወሓት አማፅያን መካከል ከአንድ ዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የሚረዳ የመጀመሪያ ዙር አዲስ በጀት እየተዘጋጀ መሆኑን የገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ ይፋ አደረጉ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ትላንት በተሰናዳውና “ህልውናን መጠበቅ እድገትን ማዝለቅ” የሚል ስያሜ ባገኘው የአዲስ ወግ ተከታታይ መርሀ ግብር ላይ እንዳሉት በጦርነቱ ሳቢያ የደረሱ ውድመቶችን በዝርዝር የሚያጠና ቡድን ከተለያዩ መስሪያ ቤቶች በተውጣጡ ሙያተኞች መቋቋሙን እና በቡድኑ ጥናት መነሻነት መንግስት ምላሽ እንደሚሰጥ አንስተዋል።


እንደ መነሻ ግን የጦርነቱን ተፈናቃዮች መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ ንብትና መሰረተ ልማቶችን ለመተካት የተለያዩ ማእቀፎች ተዘጋጅተዋልም ብለዋል ። የመጀመሪያው የድጋፍ ማዕቀፍ 750 ሚሊየን ዶላር ወይም 34 ቢሊየን ብር ያህል ተይዞለታል።

አንዱ ማእቀፍ የ400 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያለው ሲሆን በአለም ባንክ ድጋፍ የሚተገበር ነው። ሌላኛው የ350 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የመልሶ ማቋቋሚያ መርሀ ግብር ደግሞ በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የሚከናወን እንደሆነ ያነሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በቀጣይም ከተለያዩ ሀገራትና ተቋማት ለዚሁ መልሶ ማቋቋሚያ ገንዘብ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አንስተዋል።

በአጋማሽ አመት ላይ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በሚጸድቀው የተጨማሪ በጀትም ዋና ትኩረቱ ይኸው በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ማቋቋምና : የመሰረተ ልማት መልሶ መገንባት መሆኑን ገልጸዋል። የተጨማሪ በጀቱ በሚኒስትር መስሪያ ቤታቸው መዘጋጀቱን ያነሱት አቶ አህመድ መጠኑን ግን አልገለጹም።


ከቅርብ ወራት ወዲህ የተደረገው ጦርነት ያደረሰውን ጉዳት የገንዘብ ሚኒስትሩ ሲገልጹት ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ሰብአዊ እርዳታዎችን ለማቅረብ 10 ቢሊየን ብር የወሰደ መሆኑን እንዲሁም መልሶ ማቋቋሙ ከሶስት እስከ አምስት የረዘመ አመታትን ሊፈጅ እንደሚችልም ፍንጭን ሰጥተዋል።

በጦርነቱ ሳቢያ በዚህ አመት የደረሰው ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍ ሊል እንደሚችል ያነሱት ሚኒስትሩ ባለፈው አመት ሀገሪቱ በተመሳሳይ ጦርነት ውስጥ ያሳለፈች ቢሆንም ስድስት በመቶ የአመታዊ አጠቃላይ ምርት እድገት መገኘቱን ገልጸው በዚህ አመት ግን ከባድ ኢኮኖሚያዊ ጫና እንደደረሰ ጠቁመዋል።

መንግስት ኢኮኖሚውን ከጦርነቱ ተፅዕኖ ለማላቀቅ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግም ፍንጭ ሰጥተዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]