ዋዜማ ራዲዮ- በአማራ ክልል ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ እንደ ሙቀት መለኪያ (ቴርሞ ሜትር) ተደርጋ የምትወሰደው ጎንደር አንዴ ጋል ሌላ ጊዜ በረድ በሚል ተቃውሞ እና አለመረጋጋት ስትናጥ ቆይታለች፡፡ በከተማዋ ለተነሳው ተቃውሞ ዋና መንስኤ የሆነው የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጉዳይም ቁርጡ አልለይ ብሎ በትናንትናው ዕለት ለገነፈለው ሌላ ዙር የተኩስ ልውውጥ ምክንያት ሆኗል፡፡
ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት አንዱ የሆኑት ኮሎኔል ደመቀ ጎንደር በሚገኝ እስር ቤት ከታሰሩ ጀምሮ “ወደ አዲስ አበባ ወይም ሌላ ቦታ ሊወሰዱ ይችላል” የሚል ስጋት ደጋፊዎቹን ሲያስጨንቃቸው ቆይቷል፡፡ የኮሎኔሉን መዛወር የተመለከቱ መልዕክቶች በተደጋጋሚ ሲሰራጩ ቆይተዋል፡፡ ትናንት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ጀምሮ በከተማው ተመሳሳይ ወሬ ሲናፈስ መቆየቱን የጎንደር ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
በኢንተርኔት መቆራረጥ ምክንያት በማህበራዊ ድረ ገጾች የሚለተላለፉ መረጃዎችን እንደልብ ማግኘት የሚያስቸግረው የከተማዋ ነዋሪ ከወሬው መናፈስ በኋላ በስልክ እና መሰል ዘዴዎች መረጃዎችን በመለዋወጥ የኮሎኔሉን ነገር ነቅቶ መጠበቅ እንደያዘ ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ ነገሮች ገንፍለው ወደ ተኩስ የተገባው ግን ምሽት ላይ እንደነበር ያብራራሉ፡፡
አንገረብ ወንዝ አጠገብ ከሚገኘው እና ኮሎኔል ደመቀ ከታሰረበት እስር ቤት አካባቢ “የወታደር ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች ታይተዋል” እና “ኮሎኔሉን አሳልፈን አንሰጥም ያሉ ታራሚዎች አምጸዋል” በሚል በከተማይቱ የተሰራጨው መረጃ በርካታ ነዋሪዎችን ወደ ቦታው እንዲሄዱ እንዳደረጋቸው የዓይን እማኞች ይናገራሉ፡፡ በእስር ቤቱ ታሳሪ የቤተሰብ አባል ያላቸው እና በአቅራቢያ ያሉ ነዋሪዎች በቦታው ለመድረስ ቀዳሚ እንደነበሩ ይገልጻሉ፡፡ በወቅቱም የተኩስ ልውውጥ ይሰማ እንደነበርም ያስረዳሉ፡፡
ተኩሱ ከቆይታ በኋላ ቢረግብም ጎንደርን ቀን እስካሁንም ድረስ ውጥረት ውስጥ እንደከተታት ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ ይህንን ሁኔታ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ገዱ አንዳርጋቸውም ይጋሩታል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “በማህበራዊ ድረ ገጽ እና በጸረ ሰላም ኃይሎች” ተነዛ ባሉት ወሬ በጎንደር “ከፍተኛ ውጥረት” ተፈጥሮ እንደነበር አምነዋል፡፡
“ግለሰቡን ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር ቢፈለግ ኖሮ በህግ ጥላ ስር ከዋለበት ቀን ጀምሮ መፈጸም ይቻል ነበር” ሲሉ ለጋዜጠኞች የተናገሩት አቶ ገዱ “ሆኖም ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች አክብሮት በመስጠት በዚሁ ጉዳይ ላይ ከህዝቡ ጋር ለመወያየትና ለመግባባት መንግስት ወስኗል” ማለታቸውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡
እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በዛሬው ዕለት በጎንደር ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች “ኮሎኔል ደመቀ ብቻውን ሊታሰር አይገባም፤ እንዳይወሰድ ልንጠብቀው ይገባል” በሚል በእስር ቤቱ በሚገኝ ገላጣ ቦታ ተሰብስበው አብረውት እንደዋሉ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
የትናንትናው ተኩስ ልውውጥ ከመቀስቀሱ በፊት ጎንደር ለሁለተኛ ጊዜ በተጠራ የ“ቤት ውስጥ የመቆየት አድማ” ጭር ብላ ነበር የዋለችው፡፡ ለሶስት ቀናት እንደሚቆይ የተነገረለት አድማ የከተማይቱን እንቅስቃሴ እንዳሽመደመደው ከቦታው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አልፎ አልፎ ውር ውር ከሚሉ የመንግስት እና የቤት መኪኖች እንደዚሁም ወታደሮች ከጫኑ ፒካፖች ውጭ ትናንትንም ሆነ ዛሬ የጎንደር ጎዳናዎች ባዶ ሆነው መዋላቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡
የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት እና እንደ ሆቴል ያሉ አገልግሎት መስጫ ድርጅቶች ተዘግተው መዋላቸውን ይገልጻሉ፡፡ በመጀመሪያው የአድማ ጥሪ ወቅት በከተማይቱ ከታዩ ችግሮች የተነሳ በሚመስል ሁኔታ እንደ ዳቦ ቤት፣ ክሊኒክ፣ ፋርማሲ እና ጤና ጣቢያ ያሉ የህዝብ መገልገያዎች ተከፍተው እንደሚታዩ ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ የአድማውን ጥሪ ተከትሎ የከተማው አስተዳደር ሹሞች ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ዕለት የከተማውን ነዋሪ በየአከባቢው ሰብስበው ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ እና በማግስቱ ሰው ወደ ስራ እንዲገባ ሲገፋፉ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡
“አሉባልታ ትታችሁ ስራችሁን ስሩ ይሉ ነበር” ትላለች ለዋዜማ አስተያየቷን የሰጠች አንዲት የከተማይቱ ነዋሪ፡፡ ስራ የሚያቆሙ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ፍቃድ እንደሚነጠቅ ለተሰብሳቢዎች ሲነገር እንደነበረም ትናገራለች፡፡ ይህ ማስጠንቀቂያ በትናንትናው ዕለት ተደጋግሞ በፋና ጎንደር ኤፍ ኤም ሲቀርብ መስማቷንም ትገልጻለች፡፡
ቤት ውስጥ የመቆየት አድማው በማን እና እንዴት እንደተጠራ ባይታወቅም የከተማው ሰው እርስ በእርስ መረጃ እየተለዋወጠ እና አንዱ አንዱን እየተከተለ እንደሚተገብረው ለዋዜማ አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ እንደ ጎንደር ሁሉ በትናንትናው ዕለት በፍኖተ ሰላም እና ሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች የአደባባይ ተቃውሞዎች ተካሄደው እንደነበር ሪፖርቶች አመልከተዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በዛሬው መግለጫቸው በተለያዩ አካባቢዎች “እየተፈጠረ ያለው ሁከትና ግጭት ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መንግስት እንደማይፈቅድ ”መናገራቸን ሬድዮ ፋና ዘግቧል፡፡
“ይህን ችግር ከዚህ በላይ እንዲቀጥል መፍቀድ ችግሩን የበለጠ ማወሳሰብና በህብረተሰቡና በክልሉ ላይ እየተፈጠረ ያለውን ሰላም የሚያደፈርስ፤ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችንም ማባባስ በመሆኑ ክልሉ ይህን የሚያስተካክል እርምጃ ይወስዳል” ሲሉ ማስጠንቀቃቸውንም ጨምሮ ገልጿል፡፡