ዋዜማ ራዲዮ- ከሁለት ሳምንት በፊት ድንገት በተቀሰቀሰ ግጭት ውጥረት ላይ የሰነበተችው ጎንደር በዛሬው ዕለት እሁድ ሐምሌ 24 ቀን 2008 ሺህዎች የተሳተፉበት ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አስተናግዳለች፡፡ በትንሹ ለሶስት ሰዓት ያህል የቆየው ሰልፍ ቀትር ላይ በሰላም መጠናቀቁን የከተማይቱ ነዋሪዎች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ነዋሪ በክልሉ መንግስት በኩል ይደረግ የነበረውን ተከታታይ ማስጠንቀቂያ ችላ በማለት ሰላማዊ ሰልፉ ሊደረግ ወደታቀደበት ፒያሳ ወደተሰኘው የከተማይቱ ክፍል መትመም የጀመረው ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ እንደነበር ነዋሪዎች ይናገራሉ። በቡድን በቡድን እየሆነ ወደ ሰላማዊ ሰልፉ ያመራው ነዋሪ ከቀናት አስቀድሞ በ”ፌስ ቡክ” አማካኝነት የተሰራጩትን እና የተለያየ መፈክር የተጻፈባቸውን ባነሮች እና አረንጏዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ልሙጥ ባንዲራዎችን አንግቦ ነበር።
መፈክሮቹ የዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ ከተጠራበት ዋና የተቃውሞ መነሻ ተሻግረው የወቅቱን የሀገሪቱን አንገብጋቢ ጉዳዮች ያነሱ ነበሩ። ሰላማዊ ሰልፉ በዋናነት የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን እስር በመቃወም የተጠራ ቢሆንም በኦሮሚያ አሁንም ድረስ ከቀጠለው ተቃውሞ እስከ “ድምፃችን ይሰማ” የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ድረስ ያለ አጋርነት የተገለፀበት ነበር።
እንደ በቀለ ገርባ እና ሀብታሙ አያሌው ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የእስር እና የህክምና መከልከል ሁኔታም ተነስቷል። ከወልቃይት ኮሚቴ አባላት አንዱ የሆነውን እና አሁን በጎንደር በእስር ላይ የሚገኘው የኮሎኔል ደመቀ ዘውዱን ፎቶ በቲ-ሸርት አሳትመው በሰልፉ ላይ የተሳተፉ ነበሩ።
ሰልፈኞቹ በሀገሪቱ ላይ ነግሷል ያሉትን “የአንድ ፓርቲ አገዛዝ” ህወሓትን በመፈክር ላይ በመጥቀስ ጭምር ያወገዙ ሲሆን እንደ ስብሃት ነጋ ያሉ የፓርቲውን ቁልፍ ሰዎች ሲያጣጥሉ ታይተዋል። ተቃውሟቸውን ከትግራይ ብሔር ጋር ሊያይዙ ለሚሞክሩ ወገኖችም ምላሽ ሰጥተዋል። የወልቃይት ጥያቄ የአሽባሪነት ሳይሆን የማንነት ጥያቄ እንደሆነም ለማስረዳት ሞክረዋል።
በጎንደር ተፈጥሮ የነበረውን ሁነት እንደ ሽብር ድርጊት ሲዘግቡ የነበሩትን መንግስታዊውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን እና መንግስት ዘመም የሆነውን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ኮንነዋል። ሁለቱ ሚዲያዎች የወልቃይት ጥያቄ አስተባባሪዎች “የሻዕቢያ ተላላኪዎች ናቸው” በሚል ላሰራጩት ዘገባም “ተላላኪው ህወሓት እንጂ ወልቃይት አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በጎንደር ዛሬ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ፍጹም ሰላማዊ ይሁን እንጂ ተቃውሞው ወደ ግጭት ያመራል በሚል ከፍተኛ ስጋት በነዋሪዎች ላይ አንዣብቦ ነበር። ሰልፈኞቹ ላይ በመንግስት በኩል አንዳች እርምጃ ቢወሰድ የሚከላከል መሳሪያ የታጠቀ የአካባቢው ነዋሪ ለዛሬው ዕለት ተዘጋጅቶ እንደነበር ምንጮች ለዋዜማ ገልፀዋል።
በትንሹ የ12 ሰዎች ህይወት ከጠፋበት የሰሞኑ ግጭት በሁዋላ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የክልሉ መንግስት እንዲህ አይነቱን ውጥረት ለማብረድ ከከተማይቱ ነዋሪዎች ጋር ስብሰባ ተቀምጦ ነበር። በየደረጃው ካሉ የክልል እና ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር በችግሩ መንስኤ ላይ ሲወያዩ የሰነበቱት ነዋሪዎች ከስምምነት ላይ መድረስ አለመቻላቸውን ከቦታው የሚወጡ ዘገባዎች አመልክተው ነበር።
ውይይቱ በመካሄድ ላይ እያለ በማህበራዊ ድረ ገጾች አማካኝነት ለዛሬ ሐምሌ 24 በጎንደር እና ሌሎችን የአማራ ክልል ከተሞች ህዝቡ ተቃውሞውን ለማሳየት ወደ አደባባይ እንዲወጣ ጥሪዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ጥሪዎቹን ተከትሎ የክልሉ መንግስት ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ “በከተሞቹ ሰሞኑን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የጠየቀም፤ ከመንግስት ፈቃድ የተሰጠውም ወገን የለም” ሲል የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አሳውቆ ነበር።
“ሰላማዊ ሰልፍ በሚል ሰበብ ህብረተሰቡን ከሰላማዊ ህይወቱ ለማናጋት የሚደረግን እንቅስቃሴ የክልሉ መንግስት እንደማይታገስም” የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በኩል አስጠንቅቀው ነበር።
ይህን ተከትሎ በጎንደር ከተማ በአማራ ፖሊስ እና መከላከያ ሰራዊት አማካኝነት ጥብቅ የፀጥታ ቁጥጥር ሲደረግ መቆየቱን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከትናንት ቅዳሜ 11 ስዓት ጀምሮ ወደ ጎንደር የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይም እገዳ ተጥሎ እንደነበር ያስረዳሉ። እገዳው ከመተላለፉ በፊት ግን በሁለት አውቶብሶች የተጫኑ የአቅራቢያ ከተሞች እና ወረዳዎች ነዋሪዎች በሰላማዊ ሰልፉ ለመሳተፍ ወደ ጎንደር ገብተው እንደነበር የዓይን እማኞች ለዋዜማ ገልፀዋል።
የህዝቡ ስሜት ያሰጋቸው የጸጥታ ኃይሎች ትላንት ወደ ጎንደር ከተማ ይገቡ የነበሩ መኪኖችን በየቦታው እያስቆሙ ይፈትሹ እንደነበር ድርጊቱን በቦታው ሆኖ የታዘበ አንድ ነዋሪ ይገልጻል።
የአማራ ክልል መስተዳድር የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማምሻውን በኢቢሲ ቀርበው እንደተናገሩት በሰላማዊ ሰልፉ የተነሱት ጥያቄዎች በመልካም አስተዳደር ችግር የመጡ እንደሆነ እና እነሱንም ለመፍታት የክልሉ መንግስት ጥረት ያደርጋል ብለዋል። ሰልፉን “ሰላማዊ” ሲሉ የገለጹት ቢሆንም በወቅቱ ሰልፈኞቹ ይዘውት በነበረው ባንዲራ ግን “ኢ-ህገመንግስታዊ ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።