One of the malnourished children in Oromia region-WAZEMA
One of the malnourished children in Oromia region-WAZEMA

(ዋዜማ ራዲዮ)- ድርቅ ባስከተለው ችግር የተጎዱ ኢትዮጵያውያን ተረጂዎች ቁጥር ከ10.2 ሚሊዮን ወደ 20 ሚሊዮን መድረሱን የዋዜማ ምንጮች ገለጹ።

ከሁለት ሳምንት በኋላ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው የእርዳታ ሰነድ ላይ በሚካተተው የተረጂዎች ቁጥር ላይ የኢትዮጵያ መንግስትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድርድር ይዘዋል። ከድርድሮቹ አንደኛው  ረቡዕ መጋቢት 14 እንደተካሄደ ምንጮች ይገልጻሉ።

በሴፍቲ ኔት መርሃ ግብር የታቀፉ እና የምግብ እጥረት ያለባቸው 8 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን እንዳሉ የሚያስታውሱት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድርቁ ባስከተለባቸው ችግር እነዚህኞቹም ከዋነኞቹ ተረጂዎች ጋር መደመር ይገባቸዋል የሚል ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል። ከችግሩ ስፋት እና ጥልቀት አንጻር ሁለት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በተጨማሪነት በተረጂዎች ቁጥር ሊካተቱ እንደሚገባም ይከራከራሉ።

“የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ነገሮችን ያጋንናሉ” ብሎ የሚ ያምነው የኢትዮጵያ መንግስት በሰነድ ከመፅደቁ በፊት በቁጥሮች ላይ በብርቱ ሲሟገት ይስተዋላል። የሚመጣውን እርዳታ ቢፈልግም የቁጥሮቹ መናር የሚያስከትልበትን ፖለቲካዊ ጫና ለመሸሽ በኦፊሴል የሚወጡ የተረጂዎች እና የእርዳታ ቁጥሮች አነስተኛ እንዲሆኑ ይጥራል። በአሁኑ ድርድርም የሚስተዋለው ይህ እንደሆነ የዋዜማ ምንጮች ያስረዳሉ።

“መንግስት በተቻለ መጠን ቁጥሮቹን ዝቅተኛ ለማድረግ ይጥራል። በዚህም ምክንያት በርካታ ድርድሮች እንድናደርግ እንገዳደለን” ይላሉ በግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩ ምዕራባዊ የዋዜማ ምንጭ። “በአሁኑ ግን 20 ሚሊዮን የሚለውን ቁጥር ከመቀበል ውጭ ምርጫ ያለው አይመስለኝም” ሲሉ መንግስት የገባበትን አጣብቂኝ ያስረዳሉ።

ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የጠረጴዛ ድርድር ላይ ያሉት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በጎን የ90 ቀናት የአስቸኳይ እርዳታ ዘመቻ ጀምረዋል። ረቡዕ ይፋ የተደረገው ዘመቻ አሁን ሀገሪቱ እጅ በገባው እና በሚፈለገው እርዳታ መካከል ያለውን ክፍተት ለመድፈን ያለመ ነው። ኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት ያጋጠማትን ችግር ለመመከት 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብትጠይቅም እስካሁን ያገኘችው ግማሽ ያህሉን ብቻ ነው።

[በጉዳዩ ላይ በስፋት ያደረግነውን ውይይት እዚህ ያድምጡት]-http://wazemaradio.com/?p=1948