ዋዜማ- ዩቲዩብ አልያም ቲክቶክን የመሳሰሉ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የተለያዩ ይዘቶችን በማቅረብ ገንዘብ የሚያገኙ ግለሰቦችና ተቋማት አሉ። በእነዚህ መተግበሪያዎች ከይዘት ያለፈ የንግድ ልውውጥም ይደረጋል። የኢትዮጵያ መንግስት አዲስ ባዘጋጀው መመሪያ መሰረት፣ ፊልም ሙዚቃና የሚዲያ አገልግሎቶችን ጨምሮ ፖድካስትና የድረገጽ መጽሃፍትን ጭምር ታክስ ለማድረግ መዘጋጀቱን ዋዜማ ተመልክታለች።በድረገጽና በመተግበሪያ የሚቀርቡና ገቢ የሚያገኙ አዲሱ የተጨማሪ እሴት ታክስ ይመለከታቸዋል። ዝርዝሩን ያንብቡት

በክፍያ የሚቀርቡ አልያም በሚያቀርቡት አገልግሎት ገንዘብ ከሚያገኙ የድረ ገጽና የመተግበሪያ ውጤቶች ላይ መንግስት ታክስ ሊሰበስብ መዘጋጀቱን አስራሩን ለመተግበር ከወጣው የመንግስት ሰነድ ዋዜማ ተመልክታለች።

በድረገጽ የሚቀርቡ የሚዲያ አገግሎቶች ፖድካስት፣ ፊልሞችና ሙዚቃን ጨምሮ በሚቀርቡ አገልግሎቶች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ ወይም ቫት ይጣልባቸዋል።

በደንበኝነት ምዝገባ ላይ የተመሰረተ የሚዲያ አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ የሚያስገድደው አሠራር፣ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ በሚቀርብ የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ በተመሳሳይ ሁኔታ በተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲካተት አድርጓል።

በባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ የጸደቀውን “የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ” ለማስፈጸም የወጣው “የሚንስትሮች ምክር ቤት የተጨማሪ እሴት ታክስ” የተሰኘው ደንብ በ13 ክፍሎች እና በ66 አንቀጾች የተከፋፈለ ነው። የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ እንዲታወጅ ካስፈለገባቸው ምክንያቶች ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን እና በዓለማቀፍ ደረጃም ተቀባይነት ያገኙ አዳዲስ እሳቤዎችን በአገሪቱ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በማካተት ታክሱ ለኢኮኖሚው እድገት እገዛ እንዲያደርግ ማስቻል የሚለው ይገኝበታል።

በዚህ መሠረት ከዚህ ቀደም ተጨማሪ እሴት ታክስ ውስጥ ያልተካተቱ በኤሌክትሮኒክ ዘዴ የሚቀርቡ እና የደንበኝነት ምዝገባ በመጠቀም የሚተላለፉ ሚዲያዎች፣ መጽሔቶች፣ ጋዜጦች፣ የቴሌቭዥን ፕሮግራሞች እና ሙዚቃዎች ተጨማሪ እሴት ታክስ ተጥሎባቸዋል።

አዋጁን ለማስፈጸም የወጣው የተጨማሪ እሴት ታክስ ደንብ በይነ መረብን በመጠቀም የሚተላለፉ ፖድካስቶች፣ ብሎጎች እና ጆርናሎች ለመንግስት ታክስ መክፈል እንዳለባቸው ያስገድዳል። ዋዜማ የተመለከተችው ደንብ የማኅበራዊ ትስስር አገልግሎት፣ ድር ጣቢያ ወይም ዌብሳይት እና የድር መተግበሪያዎችን ማቅረብ ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚታሰብባቸው አገልግሎቶች መሆናቸውን ያትታል።

በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ከሚቀርቡና ታክስ በሚከፈልባቸው አቅርቦቶች ከተካተቱ ሌሎች አገልግሎቶች ውስጥ፣ በበይነመረብ ላይ የተመሰረተ የጨረታ አገልግሎት መስጫ አቅርቦት፣ የማንኛውም ዲጂታል ይዘት ያለው መጽሐፍ ወይም ሕትመትን ጨምሮ የኤሌክትሮኒክ መጽሐፍ አቅርቦት የሚሉት ይገኝበታል። በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ የሚጫኑ ዲጂታል ይዘት ያላቸው መተግበሪያዎች እና ፊልሞችም በታክሱ ተካተዋል። የሙዚቃ አቅርቦት፣ የቀጥታ ስርጭት አገልግሎት፣ የስልክ ጥሪ ድምጽ፣ ለቀጥታ ዝግጅቶች፣ ቲያትሮች እና ምግብ ቤቶች የሚውሉ ትኬቶችን በኢንተርኔት በኩል መሸጥ፣ በአዋጁ መሰረት የተጨማሪ እሴት ታክስ አገልግሎት የሚከፈልባቸው ሆነዋል።

ደንቡ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በዲጂታል መንገዶች የሚሰጥ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅርቦት በተጨማሪ እሴት ታክስ ውስጥ ተካትቷል። የመንገደኞችን የትራንስፖርት አገልግሎት በማመቻቸት በኤሌክትሮኒክ ዘዴ መንገደኞችን ከትራንስፖርት አቅራቢዎች ጋር የሚያገናኝ ማንኛውም ሰው ተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ መሆኑም በደንቡ ላይ ተብራርቷል።

“የፕላትፎርም ወይም በዲጂታል መንገዶች የሚሰጥ የትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ፣ ማናቸውንም ክፍያዎችን እና ኮሚሽኖችን ጨምሮ ሌሎች ተሳፋሪው ከሚከፍላቸው ጠቅላላ ክፍያዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስን መሰብሰብ አለበት” ሲል ደንቡ ያዛል። አክሎም “የፕላትፎርም አቅራቢው በየእለቱ መጨረሻ ለመንገደኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪው የተጨማሪ እሴት ታክስ ደረሰኝ መስጠት እንዳለበትም” ይሄው ደንብ ያብራራል። [ዋዜማ]