ዋዜማ- በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ትዕዛዝ የተሠጣቸው የታጠቁ ኃይሎች፣ በደቡባዊ ትግራይ የራያ አካባቢ አስተዳደራዊ መዋቅሮችን በኃይል ለመቆጣጠር መንቀሳቀሳቸውን ተከትሎ፣ ባካባቢው ግጭት መፈጠሩን ዋዜማ ሠምታለች፡፡
በርካታ የታጠቁ ኃይሎች ማክሰኞ፣ ሐምሌ 15፣ 2017 ዓ፣ም ወደ ደቡብ ትግራይ የራያ ወረዳዎች በመግባት፣ የአካባቢውን አስተዳደር ቢሮዎች መቆጣጠራቸውን የአካባቢው ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።
የትግራይ ፖሊስ መለዮ የለበሱ ናቸው የተባሉ የታጠቁ ኃይሎች፣ ወደ ማይጨው፣ መሆኒ እና ጨርጨር ከተሞች እና ሌሎች የራያ አካባቢዎች በብዛት ገብተዋል ተብሏል፡፡ “የአስተዳደር ለውጥ” እንዲያደርግ ወደ አካባቢው ተልኳል የተባለው ኃይል በኃይል ቢሮዎችን መቆጣጠር መጀመሩን ተከትሎ፣ በአብዛኛዎቹ የራያ አካባቢዎች ውጥረት ነግሷል፡፡
ውጥረቱ የተፈጠረው የራያ አካባቢዎችን በሚያስተዳድረው የቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ አጋር በሆነው መዋቅር እና የፕሬዝዳንት ጀኔራል ታደሠ ወረደ ጊዜያዊ አስተዳደር ስምሪት በሰጣቸው የታጠቁ ኃይሎች መካከል ነው።
ወደ አካባቢው ከተሞች የገቡት የታጠቁ ኃይሎች፣ የደቡብ ትግራይ ዞን መቀመጫ የሆነችውን ማይጨው ከተማን በኃይል መቆጣጠራቸውን ምንጮች ገልጸውልናል፡፡ ከመቀሌ ትዕዛዝ የተሰጣቸው የጸጥታ ኃይሎች፣ የማይጨው ከንቲባ ጽሕፈት ቤትን በመቆጣጠር፣ በከባድ መሳሪያ ዙሪያውን እየጠበቁ መሆኑን አካባቢው ምንጮች ተናግረዋል፡፡
እንደ ጨርጨር፣ መሆኒ እና አዘቦ ያሉ አካባቢዎች ላይ ደሞ፣ የአካባቢውን ሚሊሻዎች እያሳደዱ የግል ትጥቅ እያስፈቱ ነው ተብሏል፡፡
እነዚሁ ኃይሎች ከከተማ እሰከ ገጠር በየመንገዱ ያገኙትን ሚሊሻ ትጥቅ ማስፈታት መጀመራቸውን ተከትሎ፣ አላጄ ላይ ልዩ ስሙ “አይባ” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የተኩስ ልውውጥ እንደተካሄደ ምንጮች ጠቁመዋል።
የተኩስ ለውውጥ የተካሄደው በኃይል “የአስተዳደር ለውጥ” ለማድረግ በተንቀሳቀሱት ኃይሎች እና በአካባቢው ሚሊሻዎች መካከል ነው፡፡ ኃይል የታከለበት እርምጃ በድንገት መጀመሩን ተከትሎ፣ የግል ትጥቃቸውን የተቀሙ ሚሊሻዎች መኖራቸውንም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ በአላማጣ ከተማ የትግራይ ፖሊስ ዩኒፎርም የለበሱ የታጠቁ ኃይሎች በብዛት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ ማክሰኞ ረፋዱ ላይ የአስተዳደሩን ማኽተም አስረክቡ አናስረክብም ግርግር ተፈጥሮ እንደነበርም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የታጠቁት የትግራይ ኃይሎች፣ በአላማጣ ከተማ የሰፈረው የፌደራል ፖሊስ ካምፑን ለቆ እንዲወጣ መጠየቃቸውንም ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ ፌደራል ፖሊስ በካምፑ አካባቢ የተጠናከረ የጥበቃ እንቅስቃሴ ማድረግ መጀመሩን ተከትሎ፣ የትግራይ ኃይሎች ከተጠጉ በኋላ ወደ ኋላ አፈግፍገዋል ተብሏል።
ይህንኑ ተከትሎ በመከላከያና ፌደራል ፖሊስ ኮማንድ ፖስት በምትተዳደረው አላማጣ ከተማ ውጥረት መፈጠሩን የዋዜም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ደቡባዊ ዞን አስተዳደር የአመራር ለውጥ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ማክሰኞ ሐምሌ 15፣ 2017 ዓ፣ም በጽሕፈት ቤታቸው በሠጡት መግለጫ፣ በደቡባዊ ትግራይ ዞን አስተዳደር የአመራር ለውጥ ለማድረግ የክልሉን ጸጥታ ኃይል ባካባቢው እንዳሰማሩ ተናግረዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ በዞኑ የሚያካሂደውን የአመራር ለውጥ እንዲያስተባብሩ ኃላፊነት የተሠጣቸው አስመላሽ ረዳ እና የዞኑ የጸጥታ ኃላፊ ንጉሤ አበጀ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ጀኔራል ታደሠ፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የአመራር ለውጥ ለማድረግ ይህን ርምጃ የወሰደው ዞኑን ለማወክ እንዳልሆነ መታወቅ እንዳለበት ተናግረዋል። የሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል በደቡባዊ ትግራይ ዞን የአመራር ለውጥ ማድረግ እንደሚፈልጉ ሲገልጹ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ የአካባቢው አስተዳደር አካላትና የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ሕወሃት በኃይል የአመራር ለውጥ ለማድረግ እንዳይሞክር ማስጠንቅቃቸው አይዘነጋም።
ባለፈው ሚያዝያ ወር፣ ሕዝቡ የሕወሓትን እቅድ በመቃወም በማይጨውና አላማጣ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ አድርጓል።
የቀድሞው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንትና የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ፣ ጀኔራል ታደሠ የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ ዞኖች በወታደራዊ ዘመቻ ሥልጣን በኃይል ለመያዝ ሙከራ አድርጓል ሲሉ ሰኞ’ለት በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ በጻፉት መልዕክት ከሰዋል።
ጌታቸው በክረምቱ ወቅት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ጥረቶች በሰላም ላይ መስራት መሆን ሲገባቸው፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ግን በሕዝቡ ላይ ጦርነት መክፈትን መርጧል በማለት ወንጅለዋል። የሕወሓት አመራሮች ከኤርትራ መንግሥት ጋር ያልተቀደሰ ጥምረት መስርተው እየሠሩ ይገኛሉ ያሉት ጌታቸው፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ድርጊት ዳግም በሕዝባችን ላይ ጦርነት እንደማወጅ ይቆጠራል በማለት ኮንነዋል።
ጌታቸው፣ ለዚህ አጥፊ ድርጊት ተጠያቂዎቹ፣ በሕወሃት ውስጥ የመሸገው አድሃሪ ቡድን፣ የትግራይ ጸጥታ ኃይል ከፍተኛ አዛዦችና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጀኔራል ታደሠ ይሆናሉ ብለዋል።
ጌታቸው አያይዘውም፣ በሕወሃትና በትግራይ ጸጥታ ኃይሎች ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ አካላትና በኤርትራ መንግሥት መካከል የተፈጠረው ትብብር፣ ትግራይን የጦርነት አውድማ በማድረግ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የህሊና ሰላም ከማስገኘት ውጪ አንዳችም ተጨባጭ ግብ የለውም በማለትም ተችተዋል።
ትግራይ ውስጥ ያሉ አድሃሪ ኃይሎች ትዕዛዝ የሚቀበሉት ከኤርትራ አለቆቻቸው ነው በማለት ጌታቸው የከሰሱ ሲሆን፣ ለምሳሌ የፋኖ ታጣቂዎችን ላለመተናኮስ ሲሉ የወልቃይት አካባቢን በኃይል ለመያዝ ሙከራ አላደረጉም፤ ትግራይም ራሷን የቻለች አገር እንድትሆን አጀንዳ አድርገው አልተወያዩም ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ፣ ለሕወሃት መሪዎች መስዕዋትነት መክፈል እንደማይፈልጉ ለዲፕሎማቶች ነግረዋቸዋል ያሉት ጌታቸው፣ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በርግጥም ትክክለኛውን ውሳኔ እንደወሰኑ ጠቁመዋል። [ዋዜማ]