• በአባይ ተፋሰስ ሀገራት ተከታታይ ድርቅ ቢከሰት ኢትዮጵያ ከግድቡ የመጀመርያ ሙሌት በላይ ያለውን ውሀ በሙሉ ትልቀቅ እስከማለት ተደርሷል

ዋዜማ ራዲዮ- ኢትዮጵያ ; ግብጽና ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሀ አሞላልና በተፋሰሱ ሀገራት ለተከታታይ አመታት ድርቅ ቢከሰት እንዴት መቋቋም ይቻላል የሚለውን አሰራር የሚወስነው መመሪያ ላይ ተወያይቶ ከስምምነት ለመድረስ ከትላንት ጀምሮ በዋሽንግተን እየመከሩ ነው።ምክክሩ ዛሬም ቀጥሏል።

በዚህ ውይይት ላይ የአሜሪካው የገንዘብ ሚኒስትር ስቴፈን ሙኒሽን እና የአለም ባንኩ ፕሬዚዳንት ዴቪድ ማልፓስም ተገኝተዋል።ሶስቱ ሀገራት በውሀና ውጭ ጉዳይ ሚኒስተሮቻቸው እና ልኡካቸው የተወከሉ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገዱ አንዳርጋቸውና የውሀ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ የኢትዮጵያን ልኡክ መርተዋል።


ዋዜማ ራዲዮ ውይይቱ ከሚደረግበት ዋሽንግተን ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው ; አሜሪካ ; የአለም ባንክ ከግብጽ ጋር በመሆን ግልጽ የሆነ ጫናን ኢትዮጵያ ላይ የመፍጠር ስራን እየሰሩ ነው።ቀድሞም የአለም ባንክና አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ላይ ታዛቢነታቸው ላይ ጥርጣሬ ሲነሳ የቆየ ቢሆንም አሁን ላይ ጫና ለመፍጠር እያደረጉ ያለው ጥረት ግን ግልጽ የወጣ እንደሆነ መረዳት ችለናል።


ዋዜማ ራዲዮ ከድርድሩ ስፍራ እንደሰማችው በአባይ ተፋሰስ ሀገራት ለተከታታይ አመታት ድርቅ ቢከሰት ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ የምትለቀው ውሀ በአስገዳጅ የመቶኛ ቁጥሮች እንዲሆን በአሜሪካ ; በግብጽና አለም ባንክ ውትወታ ተደርጎባታል።


የአለም ባንክ ; አሜሪካና ግብጽ መጀመርያ አቅርበውት የነበረው የድርቅ ማካካሻ እቅድ ; በተፋሰሱ ሀገራት ለተከታታይ አመታት ማለትም ለሁለትና ሶስት ተከታታይ አመታት ድርቅ ቢከሰት ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ ከባህር ጠለል በላይ 595 ሜትር ድረስ ያለውን ውሀ ትይዝና ከዚያ በላይ ያለውን ሙሉ ለሙሉ ትልቀቅ የሚል ነበር።

የህዳሴው ግድብ ውሀ ከባህር ጠለል በላይ 595 ሜትር ላይ ሲሆን ማለት 18 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ ብቻ ሲይዝ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር የመጀመርያ ደረጃ ሙሌት ተብሎ ለሁለት አመታት የሚሞላው ማለት ነው።ይህ በቂ ኤሌክትሪክ ሀይል ለማመንጨት የሚሆን የውሀ መጠን አይደለም።ይህን የድርቅ መቋቋሚያ እቅድ በኢትዮጵያ በኩል ለመቀበል የዳዳቸው የተወሰኑ የድርድሩ ቡድን አባላት ቢኖሩም እርስ በርስ በተደረገ ብርቱ ክርክር ግን ውድቅ መሆኑን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።


የዚህን እቅድ ውድቅ መሆን ተከትሎ ግብጽ ከአሜሪካና አለም ባንክ ጋር በመሆን ሁለተኛ ሀሳብ አምጥተው ነበር።ይህም ሁለተኛ ሀሳብ ; ለተከታታይ አመታት ድርቅ ቢከሰት ኢትዮዮጵ ከህዳሴ ግድብ የውሀ ሙሌት ከባህር ጠለል 595 ሜትር በላይ ያለውን ግማሹን ውሀ ትልቀቅ የሚለው ነው።ይህ ማለት ግድቡ 50 ቢሊየን ሜትር ኩብ ውሀ ይዞ ድርቅ ቢከሰት እስከ ባህር ጠለል በላይ 595 ሜትር ያለው 18 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ በቋሚነት ይያዝና ከቀሪው 32 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሀ 16 ቢሊየን ሜትር ኪዩቡ ውሃ ይለቀቅ እንደማለት ነው።በሁለቱም መንገድ መስማማት ተገቢ እንዳልሆነ ነው ከምንጫችን የሰማነው።


በመጀመርያ እየቀረበ ያለው እቅድ ግልጽ የሆነ የውሀ ክፍፍል እንጂ ከዚህ ቀደም ሲባል እንደነበረው የትብብር ፍላጎት አይደለም።በውሀ ላይ ቁጥር ነክ ስምምነት ማድረግም ኢትዮጵያን ወደ ሁዋላ የሚመልስና ከፍተኛ ወጭ ካወጣችበት ግድብ ተገቢውን ጥቅም እንዳታገኝ የሚያደርግ ነው።በሌላ በኩል በግብጽ በኩል ድርቅ ላይ ነን ብለው የሚያቀርቡት መረጃ ታማኝነት ጥያቄ የሚነሳበት በመሆኑ በዚህ ላይ መስማማት ተገቢ አስቸጋሪ ይሆናል።

ድርቅ ማለት የውሀ እጥረት ተብሎ ስለሚተረጎም ; ግብጽ ደግሞ ዝናብ የሌላት ሀገር በመሆኗ አስዋን ግድቧ ላይ ያከማቸችውን ውሀ እንደከዚህ ቀደሙ ወደ ሌላ ግድቧቿ እየለቀቀች ድርቅ ላይ ነኝ ልትል ትችላለች። በዚህም ሳቢያ ሁሌም ተጨማሪ ውሀን እንድትጠይቅ ህጋዊ መሰረት ይሰጣለል።በዚህ ምክንያትም ተቀባይነት ሊኖራቸው አይገባም።ድርቅ መታየት ካለበትም በኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ያለው ሳይሆን በኢትዮጵያ ሊከሰት ከሚችለው ነው የተሻለ ግምት ሊሰጥ ነው የሚገባው ብለውናል ምንጮቻችን።[ዋዜማ ራዲዮ]