ዋዜማ- በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ10 በላይ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ዋዜማ ተረድታለች።
ጥቃቱን የፈጸመው ራሱን “የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት” ብሎ በሚጠራውና በመንግሥት “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድን መሆኑን ዋዜማ ያነጋገርናቸው የወረዳው ነዋሪዎች ገልጠዋል።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን መስከረም 20/2016 ዓ.ም ብሔርን መሰረት ያደረገ ጥቃት መፈጸሙን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመው ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ግጭት በሚፈጠርባቸው በወረዳው የገጠር ቀበሌዎች ነው።
በመጀመሪያው ቀን ግጭት ግንደ በርበሬ፣ ቆሮ፣ ራቾ የሚባሉ የገጠር ቀበሌዎች፣ እንዲሁም በሁለተኛው ቀን መስከረም 21/2016 ደግሞ ሰለልኩላና ሳላይሽ የተባሉ የቀበሌ ከተሞች ግጭት የተካሄደው ቦታዎች ናቸው።
በመጀመሪያ ቀን ጥቃት በሰዎች ላይ ከደረሰው ሞትና ጉዳት በተጨማሪ፣ ተሽከርካሪዎች፣ ቤቶችና የአርሶ አደር ንብረቶች ተቃጥለዋል ተብሏል።
ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ቀበሌዎች መካከል ሳላይሽ በመባል የሚጠራው ቀበሌ አንዱ ሲሆን፣ በአካባቢው በነበረው ግጭት አንድ የአእምሮ ታማሚን ጨምሮ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን ከቀበሌው ነዋሪዎች ሰምተናል።
እንዲሁም ሰለልኩላ በሚባለው አካባቢ አራት ሰላማዊ ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ ጥቃት መገደላቸውንና ሁለት ሰዎች ቆስለው መጎዳታቸውን የዋዜማ ምንጮች ጠቁመዋል።
በጥቅሉ ከ10 በላይ ሰዎች መገደላቸው የተገለጠ ሲሆን፣ በግጭቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ዋዜማ ከምንጮቿ ተረድታለች።
በተፈጠረው ግጭት ከሞቱ ሰዎች በላይ የተጎዱት ቁጥር እንደሚጨምርና ተጎጅዎችን በህክምና መርዳት አለመቻሉን በጉንደ መስቀሉ ከተማ በአንድ የግል ጤና ተቋም የሚሰራ ሀኪም ለዋዜማ ተናግሯል።
ግጭቱ የተፈጠረባቸው የገጠር ቀበሌዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ፣ ተጎጅዎችን ወደ ህክምና ተቋም ማድረስም ይሁን የህክምና ባለሙያዎችን ወደ ቦታው መላክ አስቸጋሪ ሆኗል ተብሏል።
ግጭቱ የተፈጠረባቸውን ቀበሌዎች ከወረዳው ከተማ ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ በመሆናቸው፤ አብዛኛዎቹ ተጎጅዎች ህክምና ለማግኘት መቸገራቸውንም ተናግረዋል።
መረጃውን ለዋዜማ አስከደረሰበት ስዓት ድረስ አንድ ተጎጅ መጥቶለት ማከሙን የገለጠው በአንድ የግል ጤና ማዕከል የሚሰራ ሀኪም፣ ተጎጅዎች ህክምና የሚያገኙበት ሁኔታ በመንግሥት በኩል በአስቸኳይ እንዲመቻች ጦሪ አቅርቧል።
የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን ከሰፈረበት አካባቢ ወጥቶ ጥቃት በጀመረ በሁለተኛው ቀን፣ በተለይ ሰለልኩላ አካባቢ የፋኖ ታጣቂዎች ናቸው ከተባሉ ኃይሎች ጋር መዋጋቱንም የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል።
ሁለቱ “ታጣቂ ቡድኖች” ውጊያ ከገጠሙ በኋላ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ጋብ ብሎ እንደነበር ዋዜማ ከነዋሪዎቹ ተረድታለች። ለሰዓታት በዘለቀ የቡድኖቹ ውጊያ ከሁለቱም ወገኖች ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ታጣቂዎች መገደላቸው ታውቋል።
ትላንት መስከረም 21/2016 ዓ.ም ረፉድ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው መመለሳቸውን ተከትሎ ግጭቱ መቆሙን ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በወረዳው ዋና ከተማ ጉንደ መስቀል የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ክልል መደበኛ የፀጥታ ኃይሎች ቢኖሩም፣ ግጭቱ እስቆመበት ስዓት ድረስ በታጣቂዎቹ ላይ እርምጃ አለመውሰዳቸው ተመልክቷል።
የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አዋሳኝ የሆነው አወዛጋቢው ደራ ወረዳ በተደጋጋሚ ግጭቶች የሚፈጠሩበትና ሰዎች የሚገደሉበት አካባቢ ነው።
ወረዳው የሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ በመሆኑ የአማራ እና ኦሮሞ ተወላጆች በጋራ የሚኖሩበት ሲሆን፣ እልባት ባልተሰጠው ውዝግብ ግጭት የማያጣው አካባቢ ሆኖ ቀጥሏል። [ዋዜማ]