Photo-FILE

ዋዜማ- ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ መንገደኞችን ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ የሚደረገው ክልከላ ዳግም ተጀምሯል። ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው  ክልከላው በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና በህዝቡ አቤቱታ እንዲቀር ተደርጎ የነበረ ቢሆንም አሁን ድጋሚ ክልከላ እየተደረገ መሆኑን የዋዜማ ሪፖርተር በስፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል።

አማራ ክልሉ የፋኖ ታጣቂዎች እና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ግጭት  ከተቀሰቀሰ በኋላ፣ ክልከላው  ቀስ በቀስ ዳግም አገርሽቶ አሁን ላይ ተጓዦች ከመንገድ ላይ እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ተመልክተናል 

የሰሜኑን የኢትዮጵያ ክፍል ከአዲስ አበባ ጋር የሚያገናኘው የደብረ ብረሃን አዲስ አበባ መንገድ የሚያቋርጡ ተጓዞች፣ ሸኖን አልፈው እንዳይሄዱና ወደመጡበት እንዲመለሱ ሲገደዱ በስፍራው የነበረው ሪፖርተራችን ተመልክቷል፡፡ 

ተሸከርካሪዎችን አስቁመው ከተጓዦች መካከል የአማራ ክልል መታወቂ ያላቸውን ተጓዦች ለይተው ወደመጡበት እንዲመለሱ የሚያስገድት፣ የቀድሞው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መለዮ የለበሱ የጸጥታ ኃይሎችና የታጠቁ ሚሊሺያዎች ናቸው፡፡

ወደ አዲስ አበባ አታልፉም ተብለው ከተሳፈሩበት ተሸከርካሪ ተለይተው ከሚቀሩ ሰዎች መካከል፣ የተወሰኑት በቦታው ላይ ሲጉላሉና ቀሪዎቹ ደግሞ ለሸኖ ቅርብ ወደሆነችው ደብረ ብርሃን ባገኙት የትራንፖርት አማራጭ ሲመለሱ ታዝበናል፡፡

አዲስ አበባ እንገባለን ብለው ካለዕቅዳቸው ከመንገድ ላይ “ተመለሱ”  የተባሉ አንዳንድ ተጓዦች ወደ መጡበት እንኳን የሚመለሱበት ገንዘብ እጃቸው ላይ እንደሌላቸው ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ ተጓዦቹ የተጠረጠሩበት ነገር ካለ ሙሉ መረጃቸው ተመዝገቦ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ፣ በቦታው ላይ ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ተማፅኖ ቢያቀርቡም ተቀባይነት ባለማግኘቱ የተሳፈሩበት መኪና ጉዞውን ሲቀጥል እነሱ በመንገድ ላይ ለመቀረት ተገደዋል፡፡

እንደ ማንኛውም ዜጋ ሕጋዊ መታወቂያ አሳይተውና ተፈትሸው ያለምንም ግልጽ ምክንያት ከጉዟቸው የተስተጓጎሉ ሰዎች ወደመጡት እንዲመለሱ ከሚገደዱባቸው የፍተሻ ጣቢያዎች መካከል አንዱ በሆነው የሸኖ ፍተሸ ጣቢያ ተገኝቶ ሁኔታውን በአካል የተመለከተው የዋዜማ ዘጋቢ፣ ከጉዟቸው የተስተጓጎሉ ሰዎችን አነጋግሯል፡፡

ከጉዟቸው ከተስተጓጎሉ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነ መነሻውን ደሴ ከተማ ያደረገ ወጣት፣ አዲስ አበባ የምትኖር እህቱን እንደታመመች ተነግሮት እየተጓዘ ባለት ሁኔታ እንዳያልፍ መከልከሉን ተናግሯል፡፡

ሙሉ ተሳፋሪው በተለያዩ ፍተሻ ጣቢያዎች እየተፈተሸ አልፎ ሸኖ ላይ ሲደርስ አሱና አብረውት የተጓዙ ሰዎች፣ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ እንደ ማለፊያ የሚያገለግለውን መንጃ ፈቃድና ሕጋዊ የታደሰ የአማራ ክልል መታወቂያ ለፈታሾች ቢያሳዩም ማለፍ አለመቻላቸውን ገልጧል፡፡

ሌላኛው የዚሁ ችግር ሰለባ የሆነ ወጣት የህክምና ቀጠሮ ያላት አህቱን ይዞ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ላይ ሳለ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ ተከልክሎ ታማሚ እህቱን ይዞ ለመመለስ መገደዱን ጠቁሟል፡፡

በፍተሻ ጣቢያው ላይ የሚገኙ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተጓዦችን ወደ መጡበት እንዲመለሱ የሚያስገድዱት “በዘፈቀደ መርጠው ነው” ይላሉ የችግሩ ሰላባ የሆኑ ሰዎች፡፡

የዩኒቨርስቲ ተማሪ ወንድሙ የጉዞ ክልከላ ሰለባ የሆነበት ነዋሪነቱን አዲስ አበባ ከተማ ያደረገ  ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ ግለሰብ፣ ወደሚማሩበት ዩኒቨርስቲ የሚያቀኑ ተማሪዎች ጭምር የክልከላው ሰለባ መሆናቸውን ተናግሯል፡፡ 

የዩኒቨርስቲ ተማሪ ወንድሙ ወደሚማርበት ዩኒቨርስቲ ለማቅናት የሚጠቀመው መስመር አዲስ አበባን የሚያቋርጥ እንደሆነ የገለጸው ግለሰቡ፣ ወንድሙን በአውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ለማጓጓዝ መደዱን ጠቁሟል፡፡

ከዚህ ቀደም ክልከላዎች ይበረቱበት የነበረው የጎጃም አዲስ አበባ የጉዞ መስመር የአማራ ክልሉ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጎሉን ዋዜማ ባደረገችው ማጣራት ተረድታለች፡፡ 

ከአዲስ አበባ ወደ አማራ ክልል፣ እንዲሁም ከተለያዩ የጎጃም አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ሰዎችን ከሁለቱም በኩል ተቀብለው ከጎሃ ጺዮን እስከ ደጀን በከፍተኛ ክፍያ መንገደኞችን የሚያሻጋግሩ አካላት ተፈጥረዋል ተብሏል፡፡ 

መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የአማራ ክልል መታወቂያ የሚጠቀሙ ሰዎች ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ በጣላቸው ክልከላዎች፣ የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እየገደበ ነው የሚል ብርቱ ትችት ሲያስተናግድ ነበር፡፡

ስለ መዘዋወር ነጻነት በሚደነግገው በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 32 መሰረት፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው በማንኛውም የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና ንብረት የማፍራት መብት ተሰጥቶታል፡፡ 

እንደ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ያሉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋማት፣ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ በመጥቀስ መንግሥት የዜጎችን የመንቀሳቀስ መብት እንዲያከብርና አንዲያስከብር ሲወተውቱ ነበር፡፡

የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮምኒኬሽንና የኦሮሚያ ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ላቀረብንላቸው ጥያቄ ተባባሪ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

መንግሥት በየወቅቱ ለሚጥላቸው ክልከላዎች ከዚህ ቀደም በሰጠው ምላሽ፣ የጸጥታ ችግር ስጋቶችን ለክልከላው እንደ ምክንያት ማስቀመጡ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ክልከላዎቹ መንግሥት የጸጥታ ስጋት ፈጠረውብኛል ያላቸው አካላትን ያለየና የህክምና ክትትል ያላቸውን ተጓዦች ጭምር በጅምላ መከልከሉን የሰብዓዊ መብት ተቋማቱ ማረጋገጣቸው የሚታወስ ነው፡፡ [ዋዜማ]

To contact Wazema editors, please write on wazemaradio@gmail.com