ዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር የተቀሰቀሰው ግጭት ዛሬ ከሰዓት ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ጋብ ማለቱን የአካባቢው ምንጮች ለዋዜማ ገለፁ። ከተለያዩ ምንጮች የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው የኢትዮጵያ ወታደሮች በኤርትራውያን ተይዝው የነበሩ ቁልፍ ቦታዎችን ተቆጣጥረዋል። ዋዜማ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ባይችልም በድንበር አካባቢ ባሉ ነዋሪዎች ዘንድ የፃረና በኢትዮጵያ እጅ መውደቅ በስፋት እየተናፈሰ ነው። እንደ አንድ ምንጭ ገለጻ ከሆነ ፃረና በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር የገባችው ዛሬ ንጋት ላይ ነው።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተኩስ ልውውጥ የተጀመረው ከትናንት ወዲያ ከለሊቱ አስር ሰዓት ግድም እንደነበር የሚናገሩት ምንጮች በከባድ መሳሪያ በመታገዝ እስከ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ድረስ መቀጠሉን ያስረዳሉ። ከኤርትራ በኩል የተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች በድንበር አቅራቢያ ባሉ አነስተኛ ከተሞች ቢደርሱም ምንም ጉዳት አለማድረሳቸውን የአካባቢው ምንጮች ያብራራሉ። እሁድ እና ዛሬ ጠዋት ከኤርትራ የተወነጨፉ ተተኳሾች ማርያም ኪሃ ቤተክርስቲያን አቅራቢያ እና ጎሮሰናይ መግቢያ ላይ በሚገኘው “ሃውልቲ” (የሰማዕታት ሀውልት) አጠገብ መውደቃቸውን ምንጮች ለዋዜማ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከኤርትራ ለተሰነዘረብኝ ጥቃት ወስጃለሁ፣ ቀጣዩ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከኤርትራ በኩል በሚኖረው አፀፋ የሚወሰን ይሆናል ሲል መገለጫ አውጥቷል። ኤርትራ በበኩሏ በኢትዮጵያ ወረራ ተፈፅሞብኛል ስትል ትከሳለች።