ዋዜማ ራዲዮ- በመላው ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም የትምሀርት ዘመን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰተ የጸጥታ ችግር፣ድርቅና ተያያዥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያው ጉዳዮች ምክንያት 5.2 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የትምህርት ሚንስቴር ገለጸ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ሐሙስ መጋቢት 29 ቀን 2014 ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባ የትምህርት ሚንስቴርን የ 8 ወር የእቅድ አፈጻጸም ገምግሟል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ለምክርቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት በጦርነት እና በድርቅ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ ከሆኑት 5.2 ሚሊዮን ተማዎች በተጨማሪ ከሃምሌ በ2014 የትምህርት ዘመን ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች በአማካኝ ከሁለት ወር እስከ ስድስት ወራት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በጦርነት ምክንያት ብቻ በአማራ 1 ሺህ 86፣ በአፋር 65፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 55፣ በኦሮሚያ 165፣ በደቡብ ክልል 22 ትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ1393 ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ጉዳት ደርሶባቸዋል እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ 3 ሺህ 82፣ በአፋር 415፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 335፣ በኦሮሚያ 919፣ በደቡብ 131 በድምሩ 4 ሺህ 882 ትምህርት ቤቶች በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
ሚንስትሩ በትምህርት ዘመኑ በጦርነትና ድርቅ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት ‹‹ትኩርት የሚሻ ጉዳይ ነው›› ሲሉ ለምክርቤቱ አሳስበዋል፡፡
የትምህርት ሚንስቴሩ እንደገለጹት የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለመገንባት ከሚያስፈልገው 50 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከግል ባለሃብቶችና በጎ ፈቃደኞች 3.2 ቢሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የትምህርት ጥረቱ አሳሳቢ ደረጃ በመድረሱ ዘርፉ ከፖለቲካ ነጻ እንዲሆን ፓርላማውን የጠየቁት ሚንስትሩ በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ ካሉ 47ሽህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 89 በመቶ የሚሆኑት ከሚጠበቀው ደረጃ በታች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡[ዋዜማ ራዲዮ]