Mosque in Addis Ababa
Mosque in Addis Ababa

(ዋዜማ ራዲዮ)-በኢትዮዽያ የሀይማኖት ግጭት ስጋት አለ ወይ? ስጋቱ ካለስ ምን ያህል አሳሳቢ ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ቢያንስ ወደ እውነታው የሚቀርብ ምላሽ ለማግኘት የመጀመሪያው እርምጃ ነው። መንግስት “እኔ ባልቆጣጠረውና ስርዓት ባልስይዘው በኢትዮዽያ የከፋ የሀይማኖት ግጭት ይከስት ነበረ” ሲል ይከራከራል። ከሰሞኑ በኢትዮዽያ በሀይማኖትና በመንግስት መካከል ስላለው ግንኙነት አንድ ሰፋ ያለ ሪፖርት ወጥቷል።

መዝገቡ ሀይሉ ሪፖርቱን ተመልክቶ ያዘጋጀውን ዘገባ አንብቡ/ አድምጡ።

 

 

በዓለም ዙሪያ ባሉ የግጭት መንስዔዎችና ውጥረቶች ላይ ጥናት በማድረግ የሚታወቀው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የተባለ ድርጅት፥ በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግስትና በሐይማኖት ተቁዋማት መካከል ያለውን ውጥረት የተመለከተ ሪፖርት አውጥቷል።

Governing the Faithful ወይም አማኞችን ማስተዳደር በሚል ርዕስ የወጣው ይኸው ሪፖርት ዋነኛውን ትኩረቱን ያደረገው የእስልምና እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ና በመንግስት መካከል በተፈጠረው ውጥረት ላይ ነው። ጥናቱ በአጠቃላይ ድምዳሜው እንዳስቀመጠውም ̀መንግስታት እምነትን መሰረት ያደረጉ ነውጠኛ ጽንፈኝነትንና ግጭትን ለማስወገድ ለሚያደርጉት ትግልና ይህንንም ለማስፈጸም ለሚያወጧቸው ፖሊሲዎችና አፈጻጸሞቻቸው ኢትዮጵያ ምሳሌ ትሆናለች ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግስት በእምነት ተቋማት ውስጥ የሚከሰቱ ክፍፍሎችንና ውጥረቶችን ከመዳኘት አልፎ የእምነት ነጻነትን የሚገድብ ጣልቃ ገብነት ከማድረጉ የተነሳ በእምነት ተቋማትና በመንግስት መካከል የተከሰቱት ውጥረቶች ወደግጭት እንዳመሩም ሪፖርቱ ይጠቁማል። ሪፖርቱ ከዚሁም ጋር አያይዞ የመንግስት ተቃዋሚዎች ይህንኑ የመንግስት ጣልቃ ገብነት ተጠቅመው የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ሙከራ አድርገዋል ብሏል። መንግስትን ጨምሮም የተለያዩ የፖለቲካ አካላት የእምነት ተቋማትን የፖለቲካ መጠቀሚያ የማድረግ ሙከራም እየጨመረ መምጣቱንም ዘግቧል።

ይኸው ሪፖርት ጨምሮ እንደሚገልጸው በተለያዩ የእምነት ተቋማት መካከል አልፎ አልፎ ይከሰቱ የነበሩት ግጭቶች እየከሰሙ በመምጣታቸው ምክንያት በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በኖረው የመቻቻል ባሕል ላይ አደጋ ሊያስከትልበት አልቻለም። ከዚህ በፊት በሐይማኖቶች ማካከል ይከሰቱ የነበሩ ና ባብዛኛው የእምነት ቦታዎች የይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ወደ ግጭት ሲያመሩ የነበሩ ጉዳዮች አሁን በመንግስትና በሐይማኖት ተቋማቱ መካከል በተፈጠሩት ግጭቶች ምክንያት እየከሰሙ መጥተዋል። የሁለቱም ዋነኛ ሐይማኖቶች ተከታዮች መንግስት በየእምነት ተቋሞቻው ውስጥ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንደሚኮንኑትም ሪፖርቱ ጨምሮ ገልጿል።

መንግስት ራሱን ገለልተኛ እንደኾነ አድርጎ ቢያቀርብም የሚወስዳቸውን ጣልቃ ገብ የኾኑ ርምጃዎቹ የሐይማኖት ተቋማቱ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይኾኑ ለመከላከል እንደኾነ ቢናገርም፥ ርምጃዎቹ ከሕገ መንግስቱ ጋር የሚጋጩ ናቸው። በሐይማኖት ተቋማቱ ውስጥ የሚፈጠሩትን ግጭቶች በሚዳኝበትም ወቅት ብዙውን ጊዜ የአንዱን ወገን ሲደግፍም እንደሚታይ በሪፖርቱ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ በሐይማኖትና በብሔር መካከል ያለው ግንኙንት እርስ በርሱ የተሳሰረ እንደኾነ የሚጠቁመው ይኸው ሪፖርት የሐይማኖት ልዩነትን የብሔር አንድነት እንደሚያስተሳስረውና በተመሳሳይም ኹኔታ የብሔር ልዩነት በሐይማኖት አንድነት እንደሚዛመድ ይጠቁማል። ይህም በመኾኑ የይስሙላ ዲሞክራሲ ባለበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ፖለቲካዊ ቅሬታዎች በሐይማኖትና በብሔር መካከል ለሚነሱ ግጭቶች መንስዔ ኾኖ እንደሚገለጥም ይጠቁማል።

መንግስት ጣልቃ የገባበትን በእስልምና እምነት ውስጥ የሚፈጠረውንም ግጭት አስመልክቶ ሪፖርቱ እንደዘገበው፥ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የራሳቸው የኾነ የነገረ መለኮት አተረጉዋጎም ሲከተሉ የኖሩና በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክም የሱፊ እስልምና ትልቅ ስፍራ ይዞ እንደኖረ ይጠቁማል። በቅርብ አስርት ዓመታት ውስጥ ግን በዚሁ በኖረ የእስልምና ስርዓት ላይ ተሐድሶ እንዲመጣ የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች እያደጉ መምጣታቸውን የሚጠቁመው ይኸው ሪፖርት ለነዚህ የለውጥ አራማጅ እንቅስቃሴዎች ምሳሌ ናቸው ያላቸውን እንደነ ጀመኣት ተብሊቅ፥ የሰለፊና ምሑራውያን (intellectualist) ሲል የገለጻቸውን ቡድኖች ጠቅሷል። ሪፖርቱ በነዚህ አዲስ ጅምር እንቅስቃሴዎችና በነባሩ የየሱፊ ስርዓት ተከታዮች መካከል ግጭቶች ይፈጠሩ እንደነበረም ይገልጻል።

ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያለውን ውጥረት በዳሰሰበት ዘገባው፥ በማኅበረ ቅዱሳንና በቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ መካከል ያለውን ውጥረት እንደ ዋነኛ የግጭት መንስዔ አድርጎ አቅርቦታል።

በአብዛኛው ወጣት አባላትን የያዘውን ማኅበረ ቅዱሳንን፥ የቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ የትውልድ ክፍተትን ለማስፋት እንደሚተጋና ከዚህም በተጨማሪ በመንግስትና በቤተ ክርስቲያኒቱ መካከል ግጭት እንዲፈጠር እያረገ ነው በሚል እንደሚነቅፈው ሪፖርቱ ያትታል። የኢትዮጵያ መንግስትም ማኅበረ ቅዱሳን ባለው ሰፊ አውታር ምክንያት በስጋት እንደሚመለከተውና በአክራሪነት እንደሚከሰው አንዳንዴም ከእስልምናው የሰለፊ እንቅስቃሴ ጋር እንደሚያመሳስለው ሪፖርቱ ይገልጻል።

በመንግስትና በእምነት ተቋማቱ መካከል ያለውን ግጭት በተመለከተ በሰፈረበት የሪፖርቱ ክፍልም፥ መንግስት በኢትዮጵያ እየጨመረ የመጣውን እምነትን በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ አክርሮ የማሳየት ኹኔታ እንደ ችግር ይመለከተዋል ብሏል። መንግስት በሁለቱም የሐይማኖት ተቋማት ውስጥ ለሚነሱ ችግሮች የሚሰጠው ምላሽ በጣም ጠንካራ መኾኑም ከሁለቱም እምነት ተከታዮች ጋር እንዲጋጭ ምክንያት ኾኖበታል የሚል ድምዳሜም ያቀርባል።

ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግስት የሐይማኖት ተቋማቱን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ካለው ፍላጎት የተነሳ ከሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ይልቅ በሐይማኖት ተቋማቱ ውስጥ የሚፈጠረውን ውጥረት መፍትሔ ለመስጠት በመሞከሩ ምክንያት ግጭት ውስጥ እንደሚገባ የሚያሳይ ድምዳሜ አለው።

እንደሪፖርቱ ዘገባ መንግስት በእስልምና ሐይማኖት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ የተገደደው በነባሩ የእስልምና ስርዓትና በቅርቡ ከውጪ አገር ተምረው በመጡ በተለይም የሰለፊ ስርዓት አራማጆች መካከል በተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭት ምክንያት ነው። ይህ ችግር መንግስት አሕባሽ የሚባለውን የእስልምና አይነት ለችግሩ መፍትሔ እንደሚያመጣ በማሰብ በማስገደድም ጭምር በእምነቱ ተከታዮችና ምሑራን ላይ እንደጫነውም ይጠቁማል።

ይሁንና ይህ አሕባሽ የተባለው ስርዓት ከሺአ ስርዓት ጋር ባለው መመሳሰል የተነሳ ተቃውሞ እንደገጠመው ይገልጻል። የመጅሊሱንም አመራር በተመሳሳይ ኹኔታ ለመተካት የተደረገውም ሙከራ ጉዳዩን እንዳካረረው ሪፖርቱ ይናገራል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሚያደርገውም ጣልቃ ገብነት ተመሳሳይ ምክንያት ተሰጥቶታል። በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ የሚፈጠረውን ችግር ለመፍታት ብቻ ጣልቃ እንደሚገባ የሚያትተው ትኸው ሪፖርት በሁለቱም የእምነት ተቋማት ውስጥ ተፈጥሯል የሚባለው የእርስብርስ ግጭት ከመፈጠሩ አስቀድሞ የነበረውን የመንግስት ጣልቃ ገብነት በአብዛኛው ችላ ያለው ይመስላል።

የእምነትንና የፖለቲካን ድንበር አጥፍቶ የሐይማኖት መሪዎች እንደ ካድሬ የመንግስትን ፖሊሲ በሚሰብኩባት በኢትዮጵያ፥ መንግስት ተገዶ ብቻ በሕይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገባ ተደርጎ መቅረቡ የሪፖርቱ ደካማ ጎን ኾኖ ይታያል።