ዋዜማ- በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ከተማ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 26/2016 ዓ.ም አሮሬቲ እና ቶርበን ኦቦ ቀበሌዎች በነዋሪዎች ከተቀሰቀሰ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ ከመንግሥት ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት፣ የ 7 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ዋዜማ ሰምታለች።

ተቃውሞው በነዋሪዎቹ የተቀሰቀሰው የከተማ አሥተዳደሩ በቀበሌዎቹ የሚገኙ 1 ሺህ 500 ደገማ ቤቶችን ሕገ ወጥ ብሎ የማፍረስ ሥራ ሲጀምር መሆኑን ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጣለች።

ነዋሪዎቹ መሬቱን በአካባቢው ካሉ አርሶ አደሮች የገዙ መሆናቸውና ከ 2005 ዓ.ም አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ላለፉት 11 ዓመታት በሕጋዊ መንገድ ለአዳማ ከተማ መሥተዳድር ግብር ሲገብሩበት መቆየታቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

ሆኖም ቀደም ብሎ ይፈርሳሉ የተባሉትን ቤቶች እየዞሩ ቀለም ሲቀቡ መቆየታቸውንና ዛሬ ጠዋት ላይ ዶዘርና ሌሎች ማፍረሻ ማሽኖችን ይዘው ወደ ስፍራው መምጣታቸውን ተከትሎ አመጹ መቀስቀሱን አናግረዋል።

በዚህም ሳቢያ የሰባት ሰዎች ሕይወት ወዲያው ማለፉን፣ ቀጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች መቁሰላቸውንና ከሟቾች መካከልም አንዲት ነፍሰጡር ሴት እንደምትገኝበት ገልጸዋል።

ነዋሪዎቹ ባለፉት ጊዜያት ለጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ጭምር ቤቶቹ እንዳይፈርሱባቸው ግብር የከፈሉበትን ሕጋዊ ደረሰኝ በማቅረብ መጠየቃቸውንና ጽ/ቤቱም ቤቱ እንዳይፈርስና ጉዳያቸው በይደር እንዲታይ ወስኖ እንደነበር ዋዜማ ተረድታለች።

ይህ ዘገባ እየተጠናቀረ እስካለበት ሰዓት ድረስ ተቃውሞው መቀጠሉንና ድባቡም አስፈሪ መሆኑን ዋዜማ የሰማች ሲሆን፣ በጉዳዩ ላይ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስ እና የኦሮሚያ ሚሊሻ ተሳታፊዎች መሆናቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የከተማ አሥተዳደሩን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ያደረገችው ጥረት ባለመሳካቱ ህሳባቸውን ማካተት አልተቻለም። [ዋዜማ]