ዋዜማ ራዲዮ-በአዲስ አበባ ይደረጋል ተብሎ የታቀደው የተቃውሞ ሰልፍ ዛሬ መካሄድ አልቻለም። ከፍተኛ የመንግስት የፀጥታ ቁጥጥርና ማስፈራሪያ ጭምር የተደረገበት የአዲስ አበባ ነዋሪ ወደ መስቀል አደባባይ ዝር ሳይል ቀርቷል።
በሁለት አካባቢዎች ስልፍ ለመውጣት ሙከራ ያደረጉ ላይ በወታደሮች እርምጃ ተወስዷል።
ከጦር ሀይሎች በታች በሚገኘው ቤቴል አካባቢ የወጣው ህዝብ ለ10 ደቂቃ ያህል ተቃውሞውን እያሰማ ሳለ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በተሽከርካሪ በመድረስ ሰልፈኛውን የበተኑ ሲሆን የተወሰኑ ሰዎችንም በተሽከርካሪ ጭነው ሲወስዱ ታይተዋል።
ካራቆሬ አካባቢ ከመኖሪያ ሰፈር ተሰባስበው ለመውጣት የሞከሩ ወጣቶችም ዋና መንገድ ከመድረሳቸው በፊት በወታደሮች ታፍሰዋል።
የተቃውሞ ሰልፉ አለመሳካት ለገዥው ፓርቲ የልብ ልብ የሚሰጥና የእስካሁኑ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ሲሉ ለዋዜማ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ተናግረዋል።
ከሳምንት በፊት በማህበራዊ ድረ ገፃች ቀጠሮ የተጠራበት የአ.አን የተቃውሞ ሰልፍ በባለቤትነት የጠራ የፓለቲካ ፓርቲ ያለመኖሩ በመንግስት ከተነገረው ማስፈራሪያና ዛቻ በተጨማሪ የተቃውሞ ሰልፉ ለመቅረቱ ምክንያት መሆኑንም ፓለቲከኞቹ ገልፀዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የኦሮሞ መብት ጠያቂ ሰልፈኞች በመስቀል አደባባይ ስልፍ የወጡ ሲሆን በፀጥታ ሀይሎች ከፍተኛ ድብደባ ተበትነዋል።
ከወር ገደማ በፊት በአማራ ክልል የተደረገውን ሰልፍ በሀላፊነት ከጠራ በኃላ መንግስት የሀይል እርምጃ ሊወስድ መዘጋጀቱን በተመለከተ መረጃ ስለደረሰኝ ህዝቡን አደጋ ውስጥ መክተት አልፈልግም ብሎ ከተቃውሞ ቀኑ ከ፫ቀናት በፊት ሰልፉን መሰረዙን ቢናገርም በተጠራው ሰልፍ ምክንያት ለሞቱትና ለቆሰሉ እንዲሁም ለወደመው ንብረት መንግስት ሰማያዊ ፓርቲን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወሳል።
መንግስት ሰልፉን ለማስቀረት ያደረገውን ተከታታይ እርምጃ በሌሎቹ የዋዜማ ዘገባዎች ላይ ይመልከቱ http://wazemaradio.com/?p=2687