ዋዜማ – የአዲስ አበባ መስተዳድር ወሳኝ ኩነት ምዝግባና መረጃ ኤጀንሲ ለኗሪዎች አዲስ መታወቂያ መስጠትና እድሳትን ያቆምኩት በሰራተኞቼ ብልሹ አሰራር ምክንያት ነው ብሏል፡፡
ይህን ብልሹ አስራር ለማረምና ተጠያቂዎችን ለመለየት ኤጀንሲው የምርመራ ስራ ላይ መሆኑን የአዲስ አበባ መስተዳድር ወሳኝ ኩነት ምዝግባና መረጃ ኤጀንሲ በምክትል ዋና ዳይሬክተር ማዕረግ የኤጀንሲው አማካሪ ከሆኑት አቶ መላክ መኮንን ሰምተናል፡፡
በጥቅማ ጥቅምና በተለያዩ ምክንያቶች የኤጀንሲው ሰራተኞች መታወቂያውን ሕግ ለማይፈቅድላቸው ግለሰቦች ማደላቸውን እጅ ከፍንጅ ሁሉ ይዘናል ያሉት የኤጀንሲው አማካሪ የሀገሪቱ የጸጥታ ሁኔታም ለመታወቂያ እድሳትና እደላ መታገድ ምክንያት እንደሆነም ነግረውናል፡፡
በአሁኑ ስዓት ህጋዊ በሆነ መንገድ አዲስ መታወቂያ ማግኘትም ይሁን ነባሩን ማደስ ባለመቻሉ ከእንቅስቃሴና አገልግሎቶችን ከማግኘት ጋር ተያይዞ የቀበሌ መታወቂያ ግድ የሆነባቸው ቦታዎች ላይ ለተገልጋዮች ሁኔታው አዳጋች እንደሆነባቸው ይታወቃል፡፡ ይሁንና ለአስቸኳይ ጉዳዮች ኤጀንሲው የአሰራር ስልቶችን አዘጋጅቻለሁ ብሏል፡፡
እጅግ አስቸኳይ የሆነ የጤናና የጉዞ ጉዳዮች ላለባቸውና ከፍርድ ቤት ጋር ለተያያዙ ጥያቄዎች አሁንም በከንቲባ ፅህፈት ቤት በኩል ተጣርቶ መታወቂያ የሚሰጥ ሲሆን አሰራሩ ግን የሚፈለገውን ያህል ፈጣን አለመሆኑን ሀላፊዎቹ ነግረውናል።
ኤጀንሲው እስካሁን ከአገልግሎት ጋር የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተ ኦዲት በማድርግ ላይ ሲሆን የምርመራ ውጤቱ ስር የሰደደ የሙስና አሰራር እንደነበር የሚያመለክት ነው፡፡ ይህን መሰረት በማድረግም ተጠያቂ መሆን የሚገባቸውና አሁንም ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት የደረሱ እንዳሉ ተገንዝበናል፡፡
እያንዳንዱ ከኤጀንሲው በመለያ ቁጥር የወጣው መታወቂያ በኤጀንሲው የሚታወቅ ሲሆን መዳረሻቸው አግባብ ለሆነ የህብረተሰብ ክፍል መሆን አለመሆናቸው የሚያሳየው የምርመራ ውጤት በቅርቡ ይፋ ሲሆን ሕገወጥ በሆነ መንገድ መታወቂያ የወሰዱትን መለየትና እርምጃ መውሰድ እንደሚቻል ኤጀንሲው ተስፋ አድርጓል።፡፡
የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ እያዘጋጀና እያደለ የነበረውና አሁን ለጊዜው የታገደው የነዋሪዎች መታወቂያ ማንም መደበኛ ባልሆነ በተጭበረበረ ወይንም ፎርጅድ በሚባለው መንገድ ማዘጋጀት ባይችልም ከእጀንሲው ውጭ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ግን ትክክለኛውን ከተጭበረበረው መታወቂያ መለዬት አይችሉም፡፡
ይህን በተመለከተ ኤጄንሲው የተለያዩ አጋዠ የቴክኖሎጅ መሰረተ ልማቶችን በማጥነት አሁን ሌሎች ድርጅቶች በኢንተርኔት አማካኝነት የሚለዩባቸውን መንገዶች በማመቻቸት ላይ መሆናቸውን አቶ መላክ መኮንን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ሆቴሎች፣ ባንኮች፣ ውልና ማስረጃና የመሳሰሉት አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች መታዎቂያዎቹን የሚያጣሩባቸውን አሰራሮች እስከ ጥር 2015 ዓም ድረስ አሰራሩ እንደሚዘረጋ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ]