ዋዜማ ራዲዮ- ጥር 24 ቀን 2012 አ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5፣ ሀያ ሁለት አካባቢ ከቅዱስ ገብርኤል ሆስፒታል ፊትለፊት ልዩ ስሙ 24 ተብሎ በሚታወቀው ስፍራ ሌሊቱን ህግን እናስከብራለን ያሉ የጸጥታ ሀይሎች በከፈቱት ተኩስ ሁለት ወጣቶች (ምዕመናን) ሲገደሉ በርካቶችም ቆስለዋል። ጽላትን ጨምሮ በርካታ ንዋየ ቅድሳት እንደተወሰዱባትም ቤተክርስቲያን ገልጻለች።ነገሩም ትልቅ ውዝግብን ያስነሳ ሆኖ ሰንብቷል። ዋዜማ ራዲዮ ይህ እጅግ አሳዛኝ ድርጊት የተፈጸመበት ቦታን አስመልክቶ ሰፊ መረጃ የማሰባሰብ ስራን ሰርታለች።
መረጃውን ለማግኘት የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳዎችን፣ የከተማ አስተዳደሩን የመሬት አስተዳደርና ፕላን ኮሚሽን ምንጮቻችንን ያናገርን ሲሆን ፣ ችግር የተፈጠረበት መሬት ሲጀመር ባለቤትነቱ የማነው? እንዴት የዕምነት ተቋም የውዝግቡ አካል ሆነ ? የሚሉትን ጉዳዮች ለመረዳት ሞክረናል።
የመሬቱ ባለቤትነት
አሁን ችግር የተፈጠረበት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 ላይ ያለው መሬት 17 ሺህ 115 ካሬ ስፋት ያለው ሲሆን መለያ ቁጥሩ A – 7357 ፣ የቦታው አገልግሎትም የድርጅት መሆኑን ይጠቁማል። የዚህ ቦታ ህጋዊ ሰነድ ያላቸው ግለሰብም አቶ ሪያድ ደማጅ እንደሚባሉ ለመረዳት ችለናል። ከቦሌ ክፍለ ከተማ ፣ ሁለቱ ወረዳዎች እና ከከተማ አስተዳደሩ የመሬት አስተዳደርና ፕላን ኮሚሽን ምንጮቻችን መረዳት እንደቻልነው አሁንም በህይወት ያሉት አቶ ሪያድ ደማጅ ባለቤት ከመሆናቸው በፊት መሬቱ አስቀድሞ በሌሎች ግለሰቦች ባለቤትነት ስር የነበረ ሲሆን ሁለት ጊዜ ተሽጦ ነው አቶ ሪያድ በ1985 አ.ም የገዙት። በደርግ ጊዜ የተሰራው ካርታም እጃቸው ላይ አለ ። ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደሩ ያሉ ቢሮዎች ይህ መረጃ አላቸው።
እንደ አስተዳደሩ ባለሙያዎች ማብራሪያ ከሆነ የደርግ ካርታ አሁንም ህጋዊነቱን ያላጣ ሲሆን የካርታው ባለቤት ስፍራው ላይ ግንባታ ማከናወን ፈልጎ ማመልከቻ ካስገባ ነው እንዲቀይር የሚጠይቀው። አቶ ሪያድም መሬቱን መግዛታቸውንና ባለቤት መሆናቸው በፍርድ ቤት ተረጋግጦላቸዋል ፣ የሽማግሌዎች ውልም አላቸው ። ሰነድ አልባ በሚለው ቢወሰድም የይዞታው ባለቤት መሆናቸውን አያጡም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የማምለኪያ ቦታ በስፍራው ተሰርቶ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ችግር ከመነሳቱም በፊት አቶ ሪያድ በስፍራው ላይ መጋዘን እና ሁለት የቅርብ ሰዎቻቸውን የሚያኖሩበት ቤት አላቸው። ታድያ ይህ ሰፊ መሬት እስካሁን ሙሉ ለሙሉ ጥቅም ላይ ሳይውል ለዚህ አሳዛኝ ነገር መፈጠሪያነት እንዴት በቃ?
ዋዜማ ራዲዮ ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው በቦሌ ክፍለ ከተማ ያለው መሬት ባለቤት እንዳለው በመንግስት ቢታወቅም ቦታው እጅግ ተፈላጊ ስፍራ ላይ ያለ በመሆኑ ብዙ ፈላጊ ነበረው። ሆኖም አቶ ሪያድ ቦታውን ለማልማት ካርታ ተለውጦ እንዲሰራላቸው ጥያቄ ቢያቀርቡም በወቅቱ የነበሩ የመንግስት ባለስልጣናት ከባለሀብቶች ጋር በመመሳጠር ቦታውን እንዲለቁ ያግባቡዋቸው ነበር ።
ቦታውን ሪል ስቴቶች በተለይ አጥብቀው ይፈልጉት ነበር። መስኪድ እንዲሰራበትም ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። ሆኖም አቶ ሪያድ ደማጅ ራሳቸው በንግድ ስራ የተሰማሩ በመሆናቸው ቦታውን ለማልማት አቅም እንዳላቸው በመጥቀስ ጥያቄ ያቀርባሉ። በወቅቱም የቦሌ ክፍለ ከተማ ለአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደር ካርታ እንዲሰራላቸው ደብዳቤም ጽፎ ነበር። ሆኖም ከ2000 አ.ም በሁዋላ ለቅይጥ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውል ተለይቶ የነበረው ቦታ የአረንጓዴ ልማት ቦታ ነው ተብሎ ፕላኑ እንዲቀየር ይደረጋል።
ምንጮቻችን እንደነገሩን መሬቱን ለአረንጓዴ ልማት ይሁን ተብሎ ፕላኑ እንዲቀየር የተፈለገው እውነት አረንጓዴ ልማት እንዲሰራበት ተፈልጎ ሳይሆን የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በሚሊየን የሚቆጠር ብር ሙስና ጠይቀውበት እምቢ ስለተባሉ የመሬቱን ባለቤት አቶ ሪያድን መሬቱን ለማስለቀቅ በማሰብ ነው።
በዚሁ መሀልም የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ካርታ እንዲያወጣበት ይደረጋል። የአካባቢ ጥበቃ ቢሮው ካርታ እንዲያወጣ የተደረገበት መንገድ ራሱ ፍጹም ህገ ወጥ እና መሬቱ ከማን ተወስዶ አዲስ ካርታ እንደወጣበት ራሱ እውቅና ባልተሰጠበት ሁኔታ ነው። ካገኘናቸው መረጃዎች እንደተረዳነውም መሬቱ ጥቅም ላይ እንዳይውል የሆነውም የቦታው ህጋዊ ባለቤት ውሳኔውን ለማስቀልበስ ባደረጉት ትግልና መሬቱን ለመቀራመት በቀድሞ የመንግስት ባለስልጣናት በተሰራ ውስብስብ ስራ ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜም የቦታው ባለቤትነት ጉዳይ ተንጠልጥሎ የቆየ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክክርስቲያን በዚህ ቦታ ላይ ቤተክርስቲያን ለመስራት ከ1988 አ.ም ጀምሮ ጥያቄን ስታቀርብ እንደነበር ጉዳዩን እየተከታተሉ ያሉ ተወካዮች ይናገራሉ። ቦታው ህጋዊ ባለቤት እንዳለው ግን እንደማያውቁ ፣ ቤተ ክርስቲያንም ቦታው ላይ ጥያቄ ስታቀርብ የቆየችውም እንደማንኛውም ፍላጎት እንዳለው አካል መሆኑንም ይገልጻሉ።
የፓስተር ዮናታን ጉዳይ
የቦሌ ክፍለከተማው መሬት ህጋዊ ባለቤት ጉዳይ ባልተቋጨበት እንዲሁም ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ጥያቄዋን አቅርባ ምላሽ ባላገኘችበት ሁኔታ የማርሲል ቲቪ ባለቤት ፓስተር ዮናታን አክሊሉ በቦታው ላይ የመልካም ወጣት ማእከል ለመገንባት ጥያቄ በዚህ አመት ታህሳስ ወር ላይ ጥያቄን ያቀርባል። ፓስተር ዮናታን ጥያቄውን ባቀረበ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ቦታው እንደተፈቀደለት ዋዜማ ራዲዮ አረጋግጣለች።
ለፓስተር ዮናታን የመሬቱ ካርታ ጉዳይ እንዲያልቅለት የቦሌ ክፍለከተማ እና የአዲስ አበባ ከተማ መሬት አስተዳደር ደብዳቤ እንደተጻጻፉም ማወቅ ችለናል። ለፓስተር ዮናታን የመልካም ወጣት ማእከል ግንባታ ቦታው የተፈቀደበት መንገድ ብዙ ጥያቄ የሚያጭሩ ነገሮች ነበሩበት ። አንዱ ለ27 አመት ሲጓተት የነበረው የአንድ መሬት ጉዳይ ታህሳስ 2012 ዓ. ም በቀረበ ጥያቄ ወር በማይሞላ ጊዜ ምላሽ ማግኘቱ ብዙ ጥያቄ ያጭራል። እንዲሁም ለመልካም ወጣት ማእከል ቦታው ይሰጥ እስኪባል ድረስ መሬቱ ለአረንጓዴ ልማት ይሁን ተብሎ ከአመታት በፊት በተወሰነው ውሳኔ የተቀመጠ ነው ( ምንም እንኳ ይህም ውሳኔ ህገወጥ ቢሆንም) ።
የፓስተር ዮናታን ጥያቄን ተከትሎ ታድያ ቦታው ከአረንጓዴ ልማትነት ወደ ቅይጥ አገልግሎት እንዲቀየር ተደረገ። ይህ እጅግ ሊመረመር እና ተጠያቂነትን ማስከተል ያለበት ውስብስብ ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል። ነገሩ በካቢኒ አለመወሰኑን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማም ነገሩን እንደማያውቁት መገለጹ ይታወሳል። ለመልካም ወጣት ማእከል ግንባታ ቦታው መፈቀዱ ውስጥ ለውስጥ ሲሰማ ታድያ የኦሮቶዶክስ ቤተክርስቲያን ቦታው ላይ ቤተክርስቲያን በመስራት ለምእመናን አገልግሎት መስጠት ትጀምራለች። የዚህም መነሻ ለበርካታ አመታት ጥያቄ ቀርቦ ሳለ ለቅርብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለምን ተሰጠ በሚል ነው።
በይዞታው ላይ ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ ሲደረግ የመሬቱ ህጋዊ ባለቤት አቶ ሪያድ በቦታው ላይ ያለውን እንቅቃሴ በፍርድ ቤት ሊጠይቁ እንቅስቃሴ ላይ ነበሩ።በዚህ መሀል ከጥቂት ሳምንታት በፊት በሌሊት ህግ እናስከብራለን ባሉ የጸጥታ አካላት በተተኮሰ ጥይት ሁለት ወጣቶች ህይወታቸው አልፏል፣ በርካቶችም ቆስለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አሁን ወጣቶች የተገደሉበት ቦታ ቤተክርስቲያን እንዲሰራበት በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ጥያቄን አቅርባለች። ዋዜማ ራዲዮ ግን መሬቱ ህጋዊ ባለቤት ናቸው ለተባሉት አቶ ሪያድ ደማጅ እንዲሰጥ የመጨረሻ ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ሰምታለች። [ዋዜማ ራዲዮ]
To contact Wazema editors you can write wazemaradio@gmail.com