ዋዜማ- የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ፣ በመኪና ሻጮች ላይ ከፍተኛ የገቢ ግብር መጣሉን እና ነጋዴዎች መክፈል ባለመቻላቸው የብዙዎችን የባንክ አካውንታቸውን ማሳገዱን ዋዜማ ሰምታለች።
ነጋዴዎቹ ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ ዓመታዊ የገቢ መጠናቸውን ለማሳወቅ ወደ ወደ ገቢዎች ጽህፈት ቤት ሲያመሩ፣ ቢሮው ለኹሉም የተሽከርካሪ ዓይነቶች የራሱን መሸጫ ዋጋ እንዳስቀመጠ እና በዚያ መሰረት ግብር መክፈል እንዳለባቸው እንዳሳወቃቸው ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት አሁን 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚሸጥን አውቶሞቢል ቢሮው 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የተመነው ሲሆን፣ ገበያ ላይ በስፋት ያለችውን እና በ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር አማካኝ ዋጋ እየተሸጠች ያለች BYD የተሰኘች መኪና ቢሮው 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ተመን አውጥቶላታል።
11 ሚሊዮን ብር የሚሸጠው ቶዮታ አውቶሞቢልም በገቢዎች የተቆረጠለት ዋጋ 16 ሚሊዮን ሆኗል።
ስለሆነም ነጋዴዎች 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በደረሰኝ ለሸጡት መኪና ግብር የሚታሰብባቸው 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እንደሸጡት ተደርጎ ነው።
ይህ መመሪያ በነጋዴዎች ውይይት ያልተደረገበት፣ ለሕዝብም ይፋ ያልተደረገ ከመሆኑ በላይ፣ ነጋዴዎች ስለመመሪያው የሰሙት ግብር ለመክፈል ወደ ገቢዎች ቢሮ ባቀኑበት ወቅት ነው።
መመሪያው የአዲስ አበባ ንግድ ፈቃድ ያላቸውን የመኪና ሻጮች ብቻ የሚመለከት ሲሆን፣ ከክልሎች ፈቃድ አውጥተው አዲስ አበባ ውስጥ መኪና የሚሸጡትን እና በፌደራል የተመዘገቡ ሻጮችን አይመለከትም።
100 ሚሊዮን ብር ግብር የተጠየቁ ነጋዴዎች አሉ ያሉን አንድ የመኪና ሻጭ፣ ከዚህ ቀደም ግብር የምንከፍለው ከአንድ መኪና ትርፍ ከ12 እስከ 15 በመቶ ነበር ሲሉ ገልጸው፣ አሁን የተጣለው ግብር ሶስት እጥፍ ገደማ ጨምሮ ወደ 35 በመቶ ማደጉን ነግረውናል።
ሌላ ነጋዴ ደግሞ፣ አሁን የተጣለብን ግብር ከአጠቃላዩ የመኪናው ሽያጭ 45 በመቶ የሚሆን ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ ለምሳሌ አንድ መኪና 10 ሚሊዮን ብር ብሸጥ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለገቢዎች እከፍላለሁ ብለዋል።
ነጋዴዎች እንደሚሉት ይህ መመሪያ የመኪና ገዥዎች ላይም ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል። 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መኪና የገዛ አንድ ግለሰብ ስም ለማዛወር ወደ መንገድ ትራንስፖርት ሲያቀና፣ የሚጠበቅበትን 2 በመቶ ክፍያ የሚከፍለው መኪናውን 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር እንደገዛው ተቆጥሮ ነው። መንገድ ትራንስፖርት ከገቢዎች ቢሮ ነው ትዕዛዝ የደረሰኝ የሚል ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፣ ገዥዎች ደግሞ መኪናውን ወደ ሸጠላቸው ነጋዴ ተመልሰው ብር መልሱልን እንደሚሉ ነጋዴዎች ነግረውናል። ሆኖም ደረሰኝ የተቆረጠ በመሆኑ ገንዘባቸውን ማስመለስ አይችሉም።
ያናገርናቸው ሶስተኛው ነጋዴ፣ የቢሮውን ኃላፊዎች ስንጠይቃቸው “መንግስት ገቢውን ለማሳደግ ነው ያወጣው እቅድ ነው” ይሉናል ሲሉ አንስተው መመሪያው የተዘጋጀውም፣ ነጋዴዎች በጥቁር ገበያ ሽያጭ ያከናውናሉ በማለት እንደሆነ ገልጸዋል። እንዲሁም የወቅቱን የዋጋ ግሽበት ከግምት ያስገባ ዋጋ ገቢዎች ማዘጋጀቱን ለነጋዴዎች እንደተነገራቸው ነግረውናል።
ነጋዴዎች የተጣለብንን ከፍተኛ ግብር መክፈል አንችልም በማለታችን የባንክ አካውንታችን ያለምንም ማስጠንቀቂያ ታግዷል ሲሉ ገልጸው፣ በዚህ የተነሳ ወደብ ላይ ያሉ መኪኖችን ማስገባት አልቻልንም፣ የሰራተኛ ደሞዝ መክፈል፣ ጉምሩክ ላይ የተያዙ ዕቃዎቻችን መረክብ እና መሰል ስራዎችን መከወን አልቻልንም ብለዋል።
ነጋዴዎቹ መመሪያው በፍትህ ሚንስቴር ያልጸደቀ በመሆኑ በፍርድ ቤት እንዲታገድ ብናደርግም፣ የገቢዎች ቢሮው “ዕግዱን አልቀበልም” ብሏል ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።
ነጋዴዎቹ ለተጣለባቸው የተጋነነ ግብር መንግስት እልባት እንዲሰጣቸው ጠይቀው፣ መመሪያው የአዲስ አበባ ንግድ ፈቃድ ባላቸው ላይ ብቻ መተግበሩ የበለጠ ግራ አጋብቶናል ይላሉ።
ቢሮው ከከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ ያወጡ የመኪና ሻጮችን በሙሉ ኦዲት ለማድረግ ጥሪ ማቅረቡንም ዋዜማ ተረድታለች። አሁን ላይ ተግባራዊ መደረግ የተጀመረው መመሪያው ሚያዚያ 2015 ዓ.ም የወጣ ነው።
ዋዜማ የተመለከተችው ይሄው መመሪያ፣ በከተማዋ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው የአዳዲስ ተሽከርካሪ ሞዴሎች ሽያጭ ዋጋ ተብሎ በግብር ከፋዮች ዘንድ የሚቀርበው ደረሰኝ ከወቅታዊ ትክክለኛ ዋጋው እጅግ አነስተኛ በመሆኑ መንግሥት ከዘርፉ የሚያገኘውን ገቢ እያጣ መሆኑን በጥናት እንደተረጋገጠ ይገልጻል።
በዚህም መመሪያው የመዲናዋን የመኪና ሽያጭ ወቅታዊ የገበያ ዋጋ ለመወሰን የሚያስችል የቢሮውን ስሌት/አሰራር የያዘ መሆኑ መሆኑ ተገልጿል። [ዋዜማ ]