ዋዜማ ራዲዮ- ከያዝነው ሳምንት መጀመርያ አንስቶ ባለፉት ሦስት ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ሴተኛ አዳሪዎች በፖሊስ እየታፈሱ ነው፡፡ አፈሳው ከ28ኛው የአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ጋር በተያያዘ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
ትናንት በከፊል እንዲሁም ከትናንት በስቲያ በብዛት የፖሊስ አፈሳ እንደነበር የተናገሩ የአይን እማኞች በመኪና ተጭነው የተወሰዱ ሴተኛ አዳሪዎች ቁጥር ከሁለት መቶ እንደሚልቅ ይገምታሉ፡፡ በተለይም የአህጉሪቱ ርዕሳነ ብሔሮችና አጀቦቻቸው ያርፉባቸዋል ተብሎ በሚገመቱ ባለኮከብ ሆቴሎች ዙርያ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ሴተኛ አዳሪዎች በአቅራቢያቸው ወደሚገኙ የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በፖሊስ መኪና ተጭነው ተወስደዋል፡፡
በአትላስ አካባቢ አዲስ የተገነባው አዛማር ሆቴል ደጅ ላይ የቆሙ 15 የሚኾኑ ሴቶች በፖሊስ መኪና ሲጫኑ መመልከቱን ለዋዜማ ዘጋቢ የተናገረ አንድ የባህል ምግብ ቤት የጥበቃ ሠራተኛ ጥቂቶቹ ሌሊት ላይ ተለቀው መጥተዋል፣ ሌሎች ሴተኛ አዳሪዎች ደግሞ ከሌሊቱ አጋማሽ ጀምሮ በአካባቢው መታየት መጀመራቸውን አብራርቷል፡፡ ” ማታ እዚህ ገባ ብሎ ዉስጥ ዉስጡን ብዙ ሴቶች ቆመው ነበር” ይላል ቦታዎችን በአገጩ እያመላከተ፡፡
ከአትላስ ሆቴል እስከ ዮሊ ሆቴል ባለው መስመር በጀብሎ ሥራ የሚተዳደር ሌላ ወጣት በበኩሉ ብዙዎቹ የታፈሱት ሴተኛ አዳሪዎችን እንደሚያውቃቸውና አንዳንዶቹም ደንበኞቹ እንደሆኑ ከገለጸ በኋላ የተወሰዱትም ካራማራ ፖሊስ ጣቢያ እንደሆነ መስክሯል፡፡ “እዛ አሳድረዋቸው ጧት ላይ እያስፈረሙ ለቀዋቸዋል” ሲል ለዋዜማ ሪፖርተር ነግሮታል፡፡ ካራማራ ፖሊስ ጣቢያ በሚኪሊላንድ ጎዳና ከስሪዴይ ሆቴል ፊትለፊት የሚገኝ ነው፡፡
እፎይ ሬስቶራንት በር ላይ በማስተናበር የሚተዳደር ወጣት በበኩሉ ትናንት በፖሊስ ፒካፕ መኪና ከአትላስ የጫኗቸውን ሴቶች ገርጂ ሜዳ ላይ ጥለዋቸው ነው የመጡት ይላል፡፡ መረጃውንም ከራሳቸው ከሴቶቹ እንደሰማና የላዳ ሾፌሮችም ጨምረው እንደነገሩት ተናግሯል፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ያደሩት በቁጥር ትንሽ ናቸው የሚለው ወጣቱ ፖሊስ ጣቢያ ካደሩት መሐልም ልጅ ያላቸውንና ልጃቸውን ጧት ትምህርት ቤት ማድረስ እንዳለባቸው የተናገሩትን ቶሎ ፈተዋቸዋል ይላል፡፡
ይህ ወጣት ጨምሮ እንደሚለው ብዙዎቹ እዚያ ሰፈር የሚቆሙ ሴቶች በደላሎች እስከሚደወልላቸው ድረስ ነው እንጂ በየመንገድ ጥግ የሚቆሙት ሥራ አጥተው እንዳልሆነ ያብራራል፡፡ ምሽት ላይ ብዙ ደንበኞቻቸው ይመጣሉ፣ ይደወልላቸዋል ይላል፡፡
ከዋሺንግተን ሆቴልና ከአውሮፓ ኅብረት ጽሕፈት ቤት አንስቶ ሲያንሲቲ ሆቴልን አልፎ ቺቺንያ ሚኪሊላንድ ጎዳና ድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሴተኛ አዳሪዎች ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ ዋናውን መንገድ ይዘው መቆማቸው የተለመደ ነው፡፡ ከአትላስ ወደ ቦሌ መድኃኒዓለም የሚወስደው ጎዳና ግራና ቀኝ ዘወትር ምሽት በሴተኛ አዳሪዎች የሚዘወተር ሲኾን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በካዛንቺስ የጁፒተርና የራዲሰን ሆቴሎች መግቢያ፣ የኢንተርኮንቲነንታል አዲስና የኢሊሌ ሆቴሎች ዙርያ አልፎ አልፎ ሴተኛ አዳሪዎች እልፍ አልፍ ብለው የሚቆሙባቸው ቦታዎች እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የዋናውን የአፍሪካ ጎዳናን መንገድ ይዞ ወደ ቦሌ መድኃኒአለም የሚያስገቡ ቂያሶችም በሴተኛ እዳሪዎች ይዘወተራሉ፡፡ በተለይም በራማዳ አዲስ፣ በሚሊንየም አዳራሽ ጀርባ፣ ብራስ ሆስፒታል አካባቢ፣ ጎልደን ቱሊፕ ሆቴልና አካባቢው፣ ሳርቤት አደባባይ አካባቢ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት የሴተኛ አዳሪዎች ቁጥር በርክቶባቸዋል፡፡
ከአፍሪካ ኅብረት የ28ኛው መደበኛ ጉባኤ ጋር ተያይዞ የአገር ገጽታን እንዳያበላሹ በሚል ፖሊስ በሴተኛ አዳሪዎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ባለፉት ዓመታትም በተመሳሳይ መልኩ መስተዋሉ አይዘነጋም፡፡ የመሪዎች ጉባኤ የፊታችን ሰኞ በይፋ ይከፈታል፡፡ በጉባኤው ለመታደም አራት ሺህ እንግዶች ወደ መዲናዋ እንደገቡ ተነግሯል፡፡ ከነዚህ ዉስጥ 37 የሚኾኑት የአገር መሪዎች ሲኾኑ 49 የሚኾኑ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ናቸው፡፡ ከኅብረቱ አባል አገራት ልዑካን ዉጭ ደግሞ የ35 አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የ25 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎች ጉባኤውን እንደሚታደሙ የኢትዮጰያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ባሳለፈውነው ሳምንት ለዜና ሰዎች ተናግረዋል፡፡