- የተመስገን ደሳለኝና የሙሉጌታ ሉሌ መፅሀፍት የጥቃቱ ዋና ዒላማ ናቸው
- እስካሁን ስድስት አዟሪዎች ታስረዋል የበርካቶች መፅሀፍ ተወርሷል
ዋዜማ ራዲዮ-በኦሮሚያና አማራ ክልል የተነሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ መንግሥት ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው መጻሕፍት ስርጭትን ለመግታት እየሰራ ይገኛል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ ከሰኞ ቀትር ጅምሮ ፖሊሶች መጽሐፍ አዙዋሪዎችን በማዋከብ የተወሰኑትን በማሰር ላይ ይገኛሉ፡፡ እስከ ዛሬ ምሽት (ማክሰኞ) ድረስ 8 የሚሆኑ አዙዋሪዎች ሙሉ መጽሐፎቻቸው ተወርሰውባቸው መታወቂያ አድራሻቸው ተመዝግቦ የተለቀቁ ሲሆን ሌሎች በአራዳና በአምቼ አካባቢ በሚገኙ ማረፊያ ቤቶች ታስረዋል፡፡
‹‹መጽሐፍ መሸጥ ወንጀል ከሆነ በሬዲዮ ይነገረንና ሥራ እንቀይር፡፡ አንድ ሚስኪን አዙዋሪ፣ኑሮዉን ለማሸነፍ መጽሐፍ በቸረቸረ የሚገረፍ ከሆነ በውነት ያሳዝናል፡፡›› ይላል ለአዝዋሪዎች መጽሐፍ በዱቤ በማከፋፈል የሚተዳደር ብሔራዊ አካባቢ የሚገኝ ወጣት፡፡ ከሰኞ ጀምሮ አንድም መጻሐፍ አዙዋሪ የፖለቲካ መጽሐፍ ለመያዝ ፍቃደኛ እንዳልሆነ የገለጸው ይህ አከፋፋይ በዋናነት የሙሉጌታ ሉሌ ስብስብ ሥራ የሆነውን ‹‹ሰው ስንፈልግ ባጀን›› የተሰኘ መጽሐፍ ለደንበኞቹ ጦስ እንደሆነባቸው ይናገራል፡፡
ማክሰኞ ቀን ላይ 3 ጓደኞቹ ኡራኤል አካባቢ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ታስረውበት እንደነበር የተናገረ ሌላ አዙዋሪ ጓደኞቹ ‹‹ምንም አትሆኑም ትፈታላችሁ›› መባላቸውን እንደነገሩት ለዋዜማ ገልጧል፡፡ መጽሐፎቻቸውን የያዙ ቦርሳዎቻቸው ግን ለምርመራ በሚል በፖሊስ ተወስደውባቸዋል ሲል ጨምሮ ተናግሯል፡፡
ዋዜማ ያነጋገራቸው አንዳንድ አዙዋሪዎች ፖሊሶች ትኩረት ያደረጉት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከቀናት በፊት በተጻፈው ‹‹የፈራ ይመለስ›› የተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንደሆነ ቢናገሩም ሌሎች ግን ወከባው የተመስገን መጽሐፍ ከመውጣቱ በፊት እንደጀመረ ያወሳሉ፡፡ ‹‹ቦሌ ፊላሚንጎ አካባቢ አንድ ፖሊስ ለምን እንዲህ አይነት ነገር ትሸጣለህ ብሎ በጥፊ መቶኝ ሄደ›› ያለ ሌላ አዙዋሪ በበኩሉ ምንም መጽሐፍ አልወሰደብኝም›› ሲል መስክሯል፡፡ ለጥፊ የዳረገው መጽሐፍ ምን እንደሆነ ተጠይቆ በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የተጻፈውን ‹‹የኦሮሞ እና የአማራነት የዘር ሐረግ ›› እንደሆነ ለዋዜማ ሪፖርተር አሳይቷል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘውግ ላይ ያተኮሩ በርከት ያሉ አዳዲስ መጻሕፍት ወደ ገበያ የገቡ ሲሆን አንዳንዶቹም ወቅቱ የሚፈልጋቸው በመሆናቸው በድጋሚ የታተሙ ናቸው፡፡ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ‹‹የክህደት ቁልቁለት›› እና ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› የተሰኙት መጻሕፍት በዚህ ረገድ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› 35ሺ ኮፒ ተሸጦ የነበረ ሲሆን በገበያ ፍላጎት ከወራት በፊት በድጋሚ ታትሞ ለገበያ የቀረበ ነው፡፡
ፖሊስ በመጽሐፍ አዙዋሪዎች ላይ የጀመረው ወከባ በማን ትዕዛዝ እየተፈጸመ እንዳለ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ኾኖም ሁኔታው ሲታይ አንድ የዕዝ ሰንሰለትን ይዞ የመጣ ዉሳኔ አይመስልም፡፡ ይኸውም በርከት ያሉ አዙዋሪዎች ላለፉት ቀናት ምንም የተለየ የገጠማቸው ችግር እንደሌለ የተናገሩ ሲሆን ሌሎች ‹‹ጓደኞቻችን በፖለቲካ መጽሐፍ ምክንያት ታስረውብናል›› የሚሉት ግን የሚያሰጓቸውን መጻሕፍት በጀርባቸው እየሸጎጡ መሸጥን መርጠዋል፡፡ የዋዜማ ሪፖርተር በተዘዋወረባቸው አራት ኪሎ፣ ጉርድ ሾላና ፒያሳ አካባቢ የተጠቀሱትን መጽሐፎቹ በግላጭ እየሸጡ የሚገኙ ነጋዴዎችን በስፋት ለመመልከትም ችሏል፡፡
ስማቸው ከዚህ ዜና በተያያዘ እንዲነሳ ያልፈቀዱ ቀደምት የመጽሐፍት ነጋዴ ‹‹እኔ መንግሥት በዚህ ደረጃ ያብዳል ብዬ አላስብም›› ሲሉ ተናግረው ምናልባት ከዚህ ቀደም ከ97 ምርጫ በኋላ ተከስቶ እንደነበረው አይነት ጊዝያዊ እቀባ ሊሆን እንደሚችል ገምተዋል፡፡ ምርጫ 97ን ተከትሎ ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቶ የነበረ ሲሆን አሁን በመንግሥት አጅ ላይ የወደቁት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የጻፉት ‹‹ነጻነትን የማያውቁ ነጻ አውጪ››፣ ዶክተር ነገደ ጎበዜ የጻፉት ‹‹ ሕገ-መንግሥት፣ ምርጫና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ›› እንዲሁም የዶክተር ብርሃኑ ነጋ ‹‹የነጻነት ጎህ ሲቀድ›› አንዳንዴ በግላጭ ብዙዉን ጊዜ በድብቅ ይሸጡ ነበር፡፡
በኦሮሚያ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ መጻሕፍት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ገበያ መግባታቸውና በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ቁጣ ጋር ተያይዞ ሌላ የስጋት ምንጭ ፈጥሮ ሊሆን እንደሚቸል የጠረጠሩም አልጠፉም፡፡ ለምሳሌ ‹‹የኦሮሞ ታሪክ›› በአለቃ አጽሜ፣ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ታሪክ›› በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ‹‹የኦሮሞ የማንነት ታሪክ››- በድሪቢ ደምሴ ቦኩ (የመጫ ቱለማ ማኅበር ፕሬዚደንት የነበሩ)፣ ‹‹ኦሮሚያን በፈረቃ››- በሞቲ ቢያ በቅርብ ጊዜ የሕትመት ብርሃን ያገኙ መጽሐፍት ናቸው፡፡ ከነዚህ ባሻገር መንግሥትን አብዝተው የሚኮንኑና በታሰሩ ጋዜጠኞች የተጻፉ መጻሕፍትም ገበያውን በቅርቡ የተቀላቀሉ ሲሆን የቀድሞው የአውራምባ ታይምስ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዉብሸት ታዬ የጻፈው ‹‹ሞጋች እውነቶች- የግዞት ወጎች›› እንዲሁም በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የተጻፈው ‹‹ የፈራ ይመለስ›› በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ፡፡
በአዲስ አበባና አካባቢዋ መጽሐፍት ወደ አንባቢ የሚያደርሱ 300 የሚጠጉ መጻሕፍት አዝዋሪዎች የሚገኙ ሲሆን በሥራው ላይ የተሰማሩት ብዙዎቹ ከባሕርዳርና አካባቢው የመጡ የአንድ አገር ልጆች ናቸው፡፡