PHOTO Credit-UNICEF

ዋዜማ- በአማራ ክልል ለ2017 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ይመዘገባሉ ተብሎ ከታቀደው 7 ሚሊዮን ተማሪዎች ውስጥ እስካሁን የተመዘገቡት 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው። 

ክልሉ የ2017 የትምህርት ዘመንን መስከረም 7 ቀን አስጀምሯል። ሆኖም ለዘንድሮው የትምህርት ዘመን እስካሁን የተመዘገቡት 21 በመቶ ገደማ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል።

ዋዜማ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ባደረገችው ማጣራት በ2016 የትምህርት ዘመን ተዘግተው የከረሙ በርካታ ትምህርት ቤቶች ለዘንድሮው የትምህርት ዘመንም እስካሁን ምዝገባ አላከናወኑም።

በክልሉ ምዕራብ እና ምስራቅ ዞኖች በወረዳ ከተሞች ከሚገኙ የአንደኛ እና የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውጪ በገጠር ያሉ ትምህርት ቤቶች ምዝገባ አልተካሄደባቸውም።

በደቡብ ጎንደር ዞን እንዲሁም በዞኑ መቀመጫ ደብረታቦር ከተማ ውጭ ባሉ ወረዳዎች ባብዛኛው የተማሪዎች ምዝገባ አልተከናወነም። 

በሰሜን ጎንደር፣ ማዕከላዊ ጎንደር እና ምዕራብ ጎንደር ዞኖችም ቢሆን ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ተማሪዎች አልተመዘገቡም። 

በሰሜን ወሎ እና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ሰሜን ሸዋ ዞኖችም በገጠር የሚገኙ በርካታ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እስካሁን ምዝገባ አላከናወኑም። 

የአንዳንድ ወረዳ የትምህርት ጽህፈት ቤቶች፣ በገጠር ያሉ ትምህርት ቤቶችን ለማስጀመር ማህበረሰቡ የፋኖ ታጣቂዎችን እንዲያስፈቅድ መጠየቃቸውንም ዋዜማ ተረድታለች። 

የክልሉ መንግሥት በገጠር የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን ለማስጀመር ፈተና የሆነበት መምህራን ስለሚታገቱ ነው ተብሏል። 

በጎጃም በሚገኙ አንዳንድ የገጠር ትምህርት ቤቶች መምህራን በጸጥታ ኃይሎች ታጅበው ምዝገባ ለማከናወን ሙከራ አድርገዋል። 

ሆኖም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክም ሆነ መምህራን ሥራቸውን ለመጀመር የሚያስችል የጸጥታ ሁኔታ አለመኖሩን ዋዜማ ተገንዝባለች። 

የክልሉ መንግሥት መምህራን ወደየገጠር ትምህርት ቤቶች ወርደው ምዝገባ እንዲያከናውኑ ባደረገባቸው አካባቢዎች፣ የተደበደቡ እና ለዕገታ የተዳረጉ መምህራን መኖራቸውንም ሰምተናል። 

በአንጻሩ ምዝገባ በተካሄደባቸው በዞን ከተሞች እና በአንጻራዊ ሰላም ባለባቸው የተወሰኑ የወረዳ ከተሞች ትምህርት መጀመሩን ተገንዝበናል።  

ምዝገባ የተካሄደባቸው በርከት ያሉ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደግሞ ምዝገባ ቢካሄድም ትምህርት ላይጀመር ይችላል በሚል ከዚህ ቀደም ለመመዝገቢያ ያስከፍሉ የነበረውን ገንዘብ አልጠየቁም። 

ዋዜማ ከነዋሪዎች እንደተረዳችው፣ የፋኖ ታጣቂዎች በክልሉ “ትምህርት የምናስጀምረው እኛ ነን” በሚል መምህራን ተማሪዎችን ለመመዝገብም ሆነ ለማስተማር እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። 

በአንጻሩ የክልሉ መንግሥት ለመምህራን የቀን አበል በመክፈል እና የሚያጅባቸው የጸጥታ ኃይል በመመደብ ምዝገባ እንዲከናወን ጥረት ሲያደርግ እንደቆየም ተረድተናል። 

ሆኖም አሁንም ድረስ በክልሉ የወታደሮች እና የታጣቂዎች ማረፊያ የሆኑ ትምህርት ቤቶች ብዙ ናቸው። በግጭቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶችም እስካሁን ጥገና አልተደረገላቸውም። 

በአንዳንድ አካባቢዎች ተማሪዎችን ለማስተማር ወደፊት ምቹ ሁኔታዎች ከተፈጠሩ ምዝገባዎች እንደሚከናወኑ ዋዜማ ተገንዝባለች።

ክልሉ ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ባለፈው ዓመት የትምህርት ዘመን ከ4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ሙሉ ዓመቱን ሳይማሩ አሳልፈዋል። [ዋዜማ]