Photo-File

ዋዜማ- ግጭት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ለሁለት ወገን ግብር እንዲከፍሉ የተገደዱ አርሶ አደሮች “ግብር ካልከፈላችሁ ማዳበሪያ አታገኙም” መባላቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮች የግብርና ማዳበሪያ ለማግኘት ግብር መክፈል እንደግዴታ በመቀመጡና ግብር እንክፈል ሲሉ የሚሰበስብ አካል በመጥፋቱ የአዝመራው ወቅት ሊያልፋቸው መሆኑንም ያስረዳሉ።


አርሶ አደሮቹ በተለይ የፋኖ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ታጣቂዎቹ አስቀድመው ግብር እየሰበሰቡ መቆየታቸውን ገልፀው፣ ድጋሚ ለመንግስት ግብር ከፍለው ማዳበሪያ ለማግኘት የጠየቁ አርሶ አደሮች ግብር የሚሰበስብ አካል አለማግኘታቸውን ነግረውናል።


“አርሶ አደሩ ማዳበሪያ እንዲቀርብለት በድጋሚ ግብር ለመክፈል ቢስማማም…..ማን ሰብስቦ ማን ያድረስው? ” ሲሉ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አርሶ አደሮች በዘር ወቅት ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልጠዋል፡፡
በአንዳንድ ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ ቀድሞ የማዳበሪያ መግዣ ገንዘብ ሰብስቦ ከላከ በኋላ አቅርቦት በትንሹ ተጀምሮ ነበር።


በመንግሥት በኩል ማዳበሪያ ሳይቀርብላቸው የዘር ወቅት የደረሰባቸው አርሶ አደሮች አቅርቦት ካላቸው አጎራባች አካባቢዎች ከነጋዴ በውድ ዋጋ እየገዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመንግስት በኩል 4ሺህ ሁለት መቶ ብር የሚሸጠውን ማዳበሪያ ከግለሰብ ነጋዴዎች በስምንት ሺህ ስምንት መቶ ብር ለመግዛት እንደተገደዱ አርሶ አደሮቹ ይናገራሉ።

በዘንድሮው አመት የአማራ ክልል ስምንት ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ቢገዛም ወደ ክልሉ የደረሰው አራት ሚሊየን ስምንት መቶ ሺህ ኩንታል ብቻ ነው። ከዚህም ወስጥ የተወሰነው በግለሰብ ነጋዴ እጅ መግባቱ ለአርሶ አደሩ ችግሩን አወሳስቦበታል።


ዋዜማ የአርሶ አደሮቹን ጥያቄ ይዛ የክልሉን ግብርና ቢሮ ጠይቃለች፡፡
የቀረቡት ችግሮች ክልሉ ካለበት ሁኔታ አንጻር በተለያዩ ክፍተቶች የተፈጠሩ መሆናቸውን የክልሉ ግብርና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምሳሉ ጎባው ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ የፋኖ ታጣቂዎች ወጣ ገባ በሚሉባቸውና በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች አርሶ አደሩ ገጥሞኛል ላለው ግብርን እንደ መያዣ አድርጎ ማዳበሪያ አለማቅረብ “እንደዚያ ሊገጥም ይችላል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለዚሁ ችግር “አመራር ሁሉ አንድ አይደለም” በማለት የየአካባቢውን አመራር ተጠያቂ ያደረጉት ቃል አቀባዩ፣ አርሶ አደሩ ግብር ካልከፈልክ ማዳበሪያ አታገኝም መባሉ ስተት ነው ብለዋል፡፡


ቢሮው “ግብረናንን ተንተርሶ ግብር፣ የስፖርት፣ የቀይ መስቀል” የሚባሉ ክፍያዎችን ማዳበሪያን እንደ መያዣ አድርጎ መሰብሰብ አይቻልም የሚል መመሪያ መስጠቱን ገልጠዋል፡፡ ችግሩ የተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ችግሩን ለግብርና ቢሮ ሪፖርት ማድረግ እንደሚችሉም ጠቁመዋል፡፡

ከአቅርቦት እጥረት ጋር በተያያዘ የቀረበውን ቅሬታ “እንኳንም ክልሉ በቀውስ ውስጥ ሆኖ በማንኛውም ሁኔታ ይከሰታል” በማለት አርሶ አደሮች ያነሱት እጥረት አምነዋል፡፡

ቃል አቀባዩ ማዳበሪያ በነጋዴ እጅ ስለመግባቱ በሰጡት ምላሽ “በወሬ ደረጃ ይባላል” በማለት ለቀረበው ቅሬታ የጸጥታ አካሉን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡ ስለ ሁኔታው ሲስረዱም “ግብርና እጃችን ላይ ያለው እስኪብርቶና ወረቀት ነው፣ ሕግ የምናስከበርበት አቅም የለንም” ብለዋል፡፡ ግብርና ቢሮ ዋና ሚናው አቀርቦት መሆኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ ቢሮው ያቀረበው ማዳበሪያ “አቅርቦቱን ሕገ ወጥ ሲወስደው ፖሊስ የት አለ?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ [ዋዜማ]